ጂማ፡ – የጂማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ባህልና ቋንቋን የተመለከቱ ዘርፈ ብዙ ጥናቶችን በማካሄድ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የኦሮሞ የጥናት ማዕከል ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ ።
በጂማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ ኤጌሬ የኦሮሞ ሕዝብ በአፍሪካ ቀንድ ባሉ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳና በመሳሰሉት አገራት የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ የጥናት ተቋሙ አቅሙን አሳድጎ በሁሉም የኦሮሞ ሕዝብ መገኛ ሥፍራ ተደራሽ ለመሆን ታትሮ ለመሥራት እንደተዘጋጀ ገልፀዋል።
“የኦሮሞ ጥናት በኢትዮጵያ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በአጎራባች አገራት ካሉ የኦሮሞ ሕዝቦች ጋር ጥብቅ ትስስር ማድረግ ያስፈልጋል “ያሉት ዳይሬክተሩ ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ወጉንና ሥርዓቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኦሮሞ ጥናት ላይ ሰፋፊ ሥራዎችን በመሥራት ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ታዋቂ የምርምር ማዕከል በመሆን ስለኦሮሞ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ እውቀት ማግኘት ለሚፈልግ አካል በቂ መረጃ ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንዲኖረው ታስቦ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሁለት አስር ዓመታት በኦሮምኛ ቋንቋ የስነ ጽሑፍ፣ የባህልንና የስነ ቃልን እውቀት የጨበጡ በርካታ ምሁራንን እንዳፈራ ያብራሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ወደፊት ለሚደረገው ዘርፍ ብዙ ጥናት ትልቅ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሌላው የዚህ ፕሮግራም አካል የሆነውና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የኦሮሞ ኔትውርከ ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር ግዛው ታሲሳ በበኩላቸው፣ የኦሮሞ ሕዝብ ካለው ሰፊና ጥልቅ ታሪክ አንፃር ባህሉና ቋንቋውን በዓለም እንዲታወቅ እና ርዕስ በርዕስም ያለው ትስስር ጠንካራ እንዲሆን የተጀመረው ተቋማዊ ጥናት በምሁራን መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
ቀደም ሲል በነበረው የፖለቲካ ተጽዕኖ ምክንያት የኦሮሞ ጥናት ኔትወርክ በለንደን መመሥረቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ አሁን ያለው ምቹ ሁኔታ የበለጠ ለመሥራት እንደሚያስችል ገልፀዋል። ከጂማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናት ተቋም ጋር በቅርበት እንደሚሠሩና ይህም ኮንፈረንስ በሁለቱ የጋራ ትብብር መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
ከስብሰባው ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ በአሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የጅማ ዩኒቨርሲቲን መሠረት በማድረግ አጋዥ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው፣ የጥናት ወረቀቶች ብቻ ከሚቀርቡ ትላልቅ ሰዎችም ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ መድረክ ቢመቻችላቸው፣ እንዲሁም ወጣቶች ለገዳ ሥርዓት ትኩረት ቢሰጡ የሚሉት ሐሳቦች አንስተዋል።
በዚሁ መሠረት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረውን ኮንፈረንስ በንግግር የዘጉት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስገን መረባ፣ ወጣትና አንጋፋ ምሁራን ያቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ተጨባጭ እውቀት እንዳስጨበጡ በመግለፅ ወደፊት በሚደረጉ መሰል ጥናታዊ ኮንፈረንሶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የኦሮሞን ህዝብ ሁለንተናዊ ገጽታ የሚያሳዩ ከሃያ በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ዋና ማጠንጠኛቸውም የኦሮሞን ሕዝብ የቋንቋ፣ የባህል የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እሴቶችና ታሪካዊ ዳራ ያመላከቱና የመጪውን አቅጣጫ የሚጠቁሙ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2011
ኢያሱ መሰለ