አዲስ አበባ፡- የአገር ውስጥ አልሚዎች የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማ ስለማያሠሩ ቅርሶች ውድመት እየደረሰባቸው መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ምዝገባ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማውን እንዲያሠራ የሚገደደው የአየር ንብረት ተጽዕኖ ግምገማ በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ሲሆን፤ የባህል ተጽዕኖ ግምገማ የሚል ጉዳይ ሲመጣ ወደ ባለሥልጣኑ ይመራል። በዚህም ባለሥልጣኑ በርካታ የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማዎችን አድርጎ ለአልሚዎቹ አስረክቧል።
ይሁን እንጂ እስከአሁን ባለው መረጃ የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማ ያሠሩት የውጭ ባለሀብቶች ብቻ ናቸው። የአገር ውስጥ አልሚዎች ይህን እያደረጉ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡ ስለዚህም በርካታ ቅርሶች መመዝገብ ሲኖርባቸው ሳይመዘገቡ የቀሩ ሲሆን የተመዘገቡትም እንዲጠፉ ነው።
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለፃ ባለሥልጣኑ እንዲጠብቅ የተሰጠው ሥልጣን ባህላዊ ሀብቶችን ብቻ ቢሆንም የተለያዩ ተግባራትን ይፈፅማል። ከእነዚህ መካከል ከኮሚሽኑ ጋር በጥምረት የሚሠራው የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማ አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የማድረግ ሥልጣን በአዋጅ አልተፈቀደም። ሆኖም ሥራው በተቋሙ መሠራት ስላለበት የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማውን ያደርጋል።
በአገር ደረጃ የልማትና የቅርስ ጥበቃ ሥራዎች አራምባና ቆቦ እንደሆኑ የሚያነሱት አቶ ደሳለኝ፤ በአገር ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶች ተነድፈው አልሚዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል። ሆኖም የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲያደርጉ የማስገደዱ ሁኔታ የለም። ይህ ደግሞ ብዙ ቅርሶችን እያሳጣ ይገኛል፤ በቀጣይም ማሳጣቱ አይቀርም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተሠራበት አካባቢ አርኪዎሎጂካል ሳይት ቢሆንም የልማቱ ሥራ ሲከናወን የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማ ባለመከናወኑ ከዩኒቨርሲቲው አልፎ ኮንዶሚኒየም እንደተገነባበት የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ በቅርቡ እየተሠራ ያለው የለገሐርና የሸገር ፕሮጀክቶችም እንዲሁ የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማ የላቸውም ይላሉ። ይህ ደግሞ ቅርሶችን ማሳጣቱ እንደማይቀር ይገልፃሉ።
ጊዜያዊ መፍትሔ እየተወሰደ እንደሆነና ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን የመለየት ሥራ መሠራቱን ያነሱት ደግሞ በባለሥልጣኑ የቅርስ ምዝገባ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እዮብ ዋቅቶላ ናቸው።
እርሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ብዙዎች የአገር ውስጥ አልሚዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አይመስላቸውም። ባለሥልጣኑም ቢሆን በአዋጅ ይህንን ጉዳይ አሻሽሎ ኃላፊነቱን ወስዶ እየሠራበት አይደለም። ስለዚህ በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በሚያመጣለት መረጃ ብቻ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ አቶ እዮብ ገለፃ፤ የተጽዕኖ ግምገማው ለቅርስ ጥበቃ ሁነኛ መፍትሔ እንደሚሆን ታምኖበት ኃላፊነት የተሰጠው አካል በሚገባ ተከታትሎ እንዲሠራበት ካላደረገ ቅርሶች አደጋ ውስጥ ናቸው። የቅርስ ጉዳይ የሚመለከተውም አካል አዋጁን አሻሽሎ በቀጣይ ወደ ራሱ በማምጣት ሊሠራበት ይገባል።
እስከዚያ ግን መንግሥት በአስገዳጅነት ይህንን ተግባር ሳይፈፅሙ የሚገቡ አልሚዎች ላይ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል። የቅርስ ተጽዕኖ ግምገማውን ሳይሠሩ የሚገቡም እንዳይኖሩ ማድረግ ላይ መሥራት አለበት ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው