
በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት በትኩረት ሲሰራባቸው ከቆዩት ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ዘርፉ በግብርና ላይ ለዘመናት ጥገኛ ሆኖ የኖረውን ምጣኔ ሀብት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡
ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ለባለሀብቶች በማስተላለፍ በዘርፉ ይታይ የነበረውን ሥር የሰደደ ችግር መፍታት ነው። ሀገሪቱ በኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በተለይ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ብዙ ሰርታለች፡፡
በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በሚከናወነው ተግባር ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች ይገጥማቸው የነበረውን የመስሪያ ቦታ አቅርቦትና የመሰረተ ልማት ችግር፣ የቢሮክራሲ መንዛዛት ለመፍታት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ታምኖ በተከናወነው ተግባር 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል፤ በዚህም በዘርፉ በርካታ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል፡፡
እነዚህ በሀዋሳ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ/ቂሊንጦ፣ ቦሌ ለሚ/፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር፣ መቀሌ፣ ሰመራና ጅማ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ኢንቨስትመንት በመሳብ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው፡፡
የግሉ ዘርፍም እንዲሁ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንዲያለማ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የቻይናው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ተገንብቶ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ በዚህም የወጪና ተኪ ምርቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መንግሥት በአዋጅ ባቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደሩ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑም ተቋቋሞ ወደ ሥራ ከገባ አንስቶ ያሉትን ያለፉትን አስር ዓመታት ፓርኮችን በማልማትና በማስተዳደር ለሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ ኮርፖሬሽኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አስራ አንዱ ሰፊ ሥራ እንዲሰሩ ወደሚደረጉባቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞንነት እንዲሸጋገሩ ተደርገዋል። ኮርፖሬሽኑም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹን ማልማትና ማስተዳደሩን ተያይዞታል፡፡
እነዚህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በቀጣይም በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ታምኖባቸዋል፡፡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ማዕከልነት በተጨማሪ ባለ ብዙ ዘርፍ በመሆን የንግድና የሎጀስቲክስ ማዕከላት በመሆን እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡
ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሀገሪቱን የዓለም አቀፍ እሴት ሰንሰለት ተሳትፎ በማጎልበት እና በቀጣናዊ ንግድ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመሳተፍ፣ በጊዜ እና በወጪ የመወዳደር አቅምን ለማጠናከር እንዲሁም የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን እነዚህን የትናንቶቹን የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የዛሬዎቹን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በማልማትና በማስተዳደር ያሳለፋቸውን አስር ዓመታት በቅርቡ በድሬዳዋ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አክብሯል፡፡
የኮርፖሬሽኑን የአስር ዓመት ጉዞና ቀጣይ ጉዞውን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀሩቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ/ዶ/ር/፤ ኮርፖሬሽኑ በእነዚህ አስር ዓመታት ፓርኮችን በማልማትና በማስተዳደር ልምድ እያካበተ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ሰፋፊ ሥራዎች እንደሚጠብቁት ጠቁመው፣ 10ኛ ዓመቱ እየተከበረ ባለበት ሁኔታ አዳዲስ ሥራዎችም መምጣታቸውን አስታውቀዋል፤ ከእነዚህ አንዱ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ከወጣ ትንሽ ቆይቷል፡፡ ፓርኮቹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የሚመረትባቸው፣ በዋናነት ማኑፋክቸሪንግ/አምራች ኢንዱስትሪ/ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
ከዚህ በኋላ ደግሞ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የንግድ ሥራዎች /የወጪ ንግድ/ እንዲሁም የሎጂስቲክስ ሥራዎች የሚሰሩባቸው ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ማዕከል /ሀብ/ በመሆን ያገለግላሉ፡፡
የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣናም ባለ ብዙ ዘርፍ ሆኖ የማኑፋክቸሪንግ፣ የንግድ እንዲሁም የሎጂስቲክስ ሥራም የሚካሄድበት ይሆናል፡፡ ነጻ የንግድ ቀጣናው በተለይ ለጅቡቲ ቅርብ መሆኑ በጅቡቲ በኩል የሚገቡ እቃዎች ቀጥታ እዚህ ተራግፈው ወደ መሀል ሀገር የሚሄዱበትን ሁኔታ ማቀላጠፍ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በ2007 ዓ.ም ታህሳስ መጨረሻ በሕግ የተቋቀቋመ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማልማቱንና ማስተዳደሩን ገልጸዋል፡፡
እስከ አሁን ሁለት ቢሊየን ዶላር የሚጠጉ ምርቶችን ለውጭ ገበያ መላኩን አስታውቀው፣ ከ300 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ እድል መፍጠሩን አመልከተዋል። የኢንዱስትሪ ወይም የማኑፋክቸሪንግ/ የአምራች ኢንዱስትሪ/ ባሕል እንዲስፋፋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ኮርፖሬሽኑን ገልጸውታል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ገና በጎረምሳነት እድሜ ውስጥ ነው ያለው፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ በሎጀስቲክስ፣ በንግድና በማኑፋክቸሪንግ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁበታል ብለዋል፡፡ ይህ ሥራ ለአንድ መቶ ሚሊየን ሕዝብ ይሄ በቂ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በግሉም በመንግሥትም ዘርፎች የሥራ እድል የሚፈጠርባቸው፣ ንግድ የሚቀላጥፋባቸው የሚመረትባቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እየተበራከቱ ይሄዳሉ፤ ለእዚህም ሰፊ ሥራ ይጠበቃል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በአስር ዓመት ውስጥ በአፍሪካ ቀዳሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚያለማ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማንኛውም አልሚ መጥቶ በቀላሉ ሥራ የሚጀምርባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወይም መሰረተ ልማቶች እንዳሉትም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ቀላል እድገት እንዳልሆነም አስገንዝበው፣ በዚህም ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽንም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ፓርኮቹ የተቋቁሙባቸውን ዓላማዎች ምን ያህል አሳክተዋል? ለአብነትም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ነበር፤ ይህ ሁኔታ ሲታይ የሀዋሳ ፓርክ አይደለም በአጠቃላይ ሁሉም ፓርኮች ይህን አላዩትም፤ የፓርኮቹ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅም በዚህ ደረጃ ላይ ባለበት ሁኔታ አንዴት ተደርጎ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል?›› የሚሉ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹በቅድሚያ ፓርኮቹ የሚመዘኑባቸው በርካታ መለኪያዎች አሏቸው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከሥራ እድል ፈጠራ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በኤክስፖርት ላይ አንተም እንዳልከው ሲመሰረቱ በነበረው ልክ አልሆነም›› ሲሉም አመልክተው፣ ለእዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ከአንድ ፓርክ አይደለም እንደ ሀገርም ከወጪ ንግድ የሚገኘው ከሶስት ቢሊየን ብዙም የዘለለ ሳይሆን ቆይቷል ሲሉ ጠቅሰው፣ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱንና አጠቃላይ የመንግሥት የልማት ፖሊሲም እየተቀየረ መሆኑን ተናግረው፣ ይህም በኤክስፖርት ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል፤ ከፍተኛ ችግር በሚታይበት የገቢ ንግድ ላይም እንዲሁ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለን እናስባለን›› ብለዋል፡፡
እርግጥ ነው ኤክስፖርት ላይ በተጠበቀው ልክ አልተሄደም ሲሉም ጠቅሰው፣ ኤክስፖርቱ ከዚህ በኋላ በደንብ ይስፋፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተሸጋግረዋል፤ ይህ የሆነበት ምከንያት ተፈጥሯዋዊ ነው ወይስ ወቅታዊ ሁኔታዎች ያመጡት ለውጥ ነው›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሰጡት ምላሽ ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያተኩረው በተለመደው /ትራዲሽናል ላይ/ የማኑፋክቸሪንግ ላይ ነው፤ የሀገሪቱ አብዛኞቹ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደ ጨርቃጨርቅና በመሳሰሉት አነስተኛ የማኑፋክቸሪንግ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡
ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የመሸጋገሩ ጉዳይ ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋርም ሊታይ ይችላል፤ በብዙ ሀገሮችም ከትራዲሽናል ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሽግግር እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም የበለጠ ኢንተርፕረነርሽፕን፣ ንግድን፣ ሪል ስቴትን የሚያበረታቱ ልዩ ቀጣናዎች እንዲሆኑ ማድረግ መንግሥት የያዘው የፖሊሲ አቅጣጫ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታው /ትሬንዱም. እንደዚያው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት፤ ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ሥራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲን አቡበከር በበኩላቸው ከትናንቶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዛሬዎቹ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በበለጠ የኢንዱስትሪ ባሕል ማስፋፋትና የሥራ እድል ፈጠራ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ300 ሺህ በላይ ለሚደርሱ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን እሳቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ በተለይም በአግሮ ፕሮሰሲግ ዘርፍ በዙሪያቸው ላሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ተደርጓል፤ በዚህም ከ90 ሺህ በላይ ለሚደርሱ አርሶ አደሮች ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህ በቢራ ገብስ አቅርቦት የተፈጠረው የገበያ ትስስር በቦሌ ለሚና ደብረብርሃን ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች (አርሲ፤ ባሌና ደብረብርሃን አካባቢ)፣ በአኩሪ አተር አቅርቦት በባሕርዳር ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዙሪያ የሚገኙ የጎጃም 10 ሺ ያህል አርሶ አደሮች፤ በጂማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዙሪያ ላሉ 15 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች በአቮካዶ ፍራፍሬ አቅርቦት የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ ሁሉ የ350 ሚሊዮን ዶላር ዘላቂ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህንንም የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሲሉ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸውታል፤ ምንም እሴት ሳይጨምር ትርፍ ሲያጋብስ የነበረውን ሕገወጥ ደላላ ከመስመሩ በማስወጣት አምራችና ተጠቃሚ በቀጥታ እንዲገናኙ አስችለዋል ብለዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ሌላኛው ትልቅ ስኬት በተኪ ምርት ላይ የተገኘው አፈጻጸም ነው፤ ባለፉት 4 ዓመታት የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅ ከተሰሩ ሥራዎች አንዱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱና ከውጭ የሚገባውን እንዲተኩ የተደረገበት ሁኔታ ይጠቀሳል።
በተለይም የመከላከያና የጸጥታ ኃይሎች የደንብ ልብስ በጋርመንትና ቴክስታይል ላይ ትኩረት ባደረጉ እንደ ሐዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባሉ እና ሌሎችም የኢኮኖሚ ማዕከላት ውስጥ እንዲመረቱ በመደረጉ ከ 800 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም በአልባሳት ብቻ ሳይገደብ በፋርማሲዪቲካል ዘርፍም ከውጭ የሚገቡ መድኃኒቶች በቂሊንጦ የፋርማሲዪቲካል ልዩ ኢኮኖሚ ዞን እንዲመረቱ በመደረጉ የመጣ አፈጻጸም ነው፡፡
በየዓመቱ በአማካይ ከ600 ሺህ በላይ አገር በቀል ችግኞችን ጭምር በመትከል ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡ እነኚህ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች በአብዛኛው ባለፉት አምስት ዓመታት ነው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው፣ ‹‹እንደ ሀገር ለምናስበው መዋቅራዊ ሽግግር፤ የኢንዱስትሪ ባሕል መጎልበት እንደ የማይተካ ሚና አላቸው›› ሲሉም እሳቸውም አስታውቀዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ ማዕከላቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የላቸውም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላቸው የኃይል አቅርቦትና መሰረተ ልማት አኳያ ተመራጭና ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ ምርቶቻቸው በዓለም ገበያ ያላቸው ተፈላጊነት /በኢትዮጵያ የተመረተ የሚሉ በመሆናቸው/ ለገጽታ ግንባታ፤ በዘርፉም እንደ አገር ያለንን መዳረሻዎች የሚያሳዩ በመሆናቸው አዎንታዊ አስተዋጿቸው ከፍተኛ ነው›› ብለዋል፡፡
አሁን በሁሉም ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ካሉት 177 የማምረቻ ሼዶች ውስጥ ከ87 በመቶ በላዩ በውጭና በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተይዘዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ ጋርመንት /ቴክስታይል/ ላይ ብቻ አተኩሮ የነበረውን አካሄድ ወደ ብዝሃ ዘርፍ በተለይም ወደ ፋርማሲዩቲካል፤ አግሮ ፕሮሰሲግ፤ ቴክኖሎጂ፤ የቤት መኪና መገጣጠምና የአውሮፕላን አካላት ማምረት፤ ንግድ፤ ሎጂስቲክና አይሲቲ ልማት ዘርፎችም በማስፋት በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት እየተቻለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም