“ብሔራዊ አንድነታችንን ጠብቀን በፍጹም የአርበኝነት መንፈስና ወኔ እንዘልቃለን”-የብልፅግና ፓርቲ

/የብልፅግና ፓርቲ 2 መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ ሙሉ ቃል/

«ከቃል እስከ ባሕል» በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የብልፅግና ዐሻራ ደምቆ በሚታይባት፣ ከተመሠረተች መቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ ዳግም እንደገና እየተሠራችና እየፈካች በምትገኘው፣ የፓርቲያችን የሃሳብና የምናብ ኃይል በተጨባጭ ተግባር በተገለጠባት፣ በመሪዎቿ ድንቅ ትጋት ዘመናዊ ካባ በተጎናጸፈችው ውቧ መዲናችን አዲስ አበባ፣ የነዋሪዎቿን ትብብርና ርብርብ እንዲሁም ብዝሀነታችንን ጌጥ አድርጎ የሚያሳይ፣ የመላ አፍሪካውያንና የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል በሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ በመክተም ሲመክር የቆየው የፓርቲያችን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በድል መጠናቀቁን ስንገልጽ በታላቅ ደስታና ኩራት ነው።

ይህ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአንድ በኩል መላው የፓርቲያችን አመራርና አባላት በሕልም ጉልበት እየተመሩ ዕዳን ወደ ምንዳ ለመቀየርና በሀገራችን እመርታዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ልቆ በታየበት፤ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የሕግ አስከባሪ ተቋማት ነፃነትና ገለልተኝነት በተረጋገጠበት፤ የሀገር ሀብት አጠቃቀማችንን በማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ7 በመቶ በላይ በሆነ ፈጣን ዕድገትና ለውጥ ባሳየበት፤ በሰው ተኮርና ማኅበራዊ ካፒታል ግንባታ አቅጣጫችን ሰፋፊ የምገባ፣ የቤት እድሳትና ግንባታ እና የመሳሰሉ ሥራዎች የተሠሩበትና የማኅበረሰብ መረዳዳት ባሕል ወደ መሆን እየተሸጋገረ ባለበት፣ ከመሽኮርመም ዲፕሎማሲ በመላቀቅ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ዲፕሎማሲያዊ ዓውድ በተፈጠረበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ሁለንተናዊ ድሎች እየተደመምን ቀጣይ ህልማችንን ከዳር ለማድረስና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተልዕኮዎችን ለመፈጸም የሚያስችል ዐቅም በአጎለበትንበትና ቁርጠኝነታችን እያደገ በመጣበት ወቅት ላይ መሆኑ እጅግ ታሪካዊና ልዩ ያደርገዋል።

ይህን መደበኛ ጉባኤ ከማካሄዳችን አስቀድመን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ከታች ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ የፓርቲ አደረጃጀቶች በተካሄዱ የቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንሶች መላው አመራርና አባሎቻችን በፓርቲያችን ስኬቶች፣ ፈተናዎችና የመሻገሪያ ሃሳቦች ዙሪያ ጥልቅ ውይይትና ክርክር አካሂደናል።

በዚህም የጉባኤያችንን ሂደትና ውጤት ዴሞክራ ሲያዊነት የሚያረጋግጡ፣ ሁሉም የአደረጃጀትና የፖለቲካ ሥራዎች በተሻለ ጥራትና ብቃት ተከናውነዋል።

በተለይም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለዘመኑ የተቀረጹ ተልዕኮዎችን ብቻ ሳይሆን በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት ባስከተለብን ጉዳትና፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ባሳደሩብን አሉታዊ ተጽዕኖ ምክንያት ያመለጡንን ዕድሎች በሚያካክስ መንገድ በሁሉም ዘርፎች እመርታ ለማምጣት በሚያስችሉ ዕሳቤዎች ዙሪያ የተሻለ መግባባት ፈጥረናል።

በመሆኑም እኛ የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች ፓርቲያችን ባለፉት ሦስት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ያስመዘገባቸው ድሎች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ የእኛን ዘመን የአመራር ትውልድ መፍትሔ የሚሹ ጉድለቶች ደግሞ በብቃት እንዲታረሙ በሙሉ ልብ በመተማመንና የላቀ ተስፋ በመሰነቅ የሚከተለውን ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

1ኛ. የመጀመሪያው ጉባዔያችን ለጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ልዩ ትኩረት የሰጠው ጠንካራ ፓርቲ ለውጤታማ መንግሥትና ለጠንካራ ሀገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለሆነም በሁለተኛው ጉባኤያችን የዚህን ውሳኔ አፈጻጸም፣ ስኬቶችና ጉድለቶች በጥሞና ገምግመናል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ግባችንን ለማሳካት ታልመው የተፈጸሙ የፖለቲካና የአደረጃጀት ሥራዎች ፓርቲያችንን ከዕድሜው የቀደመ የውጤትና የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ እንዲገኝ ማድረጋቸውን አይተናል።

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብርና በፉክክር መካከል ሚዛን በመጠበቅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባሕል ለመቀየር ያሳየነው ቁርጠኝነትም ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚሆን አይተናል።

ይህም ሆኖ በቅድመ ጉባዔ ኮንፈረንሶቻችንና በጉባኤያችን አማካኝነት ባካሄድናቸው ተከታታይ ውይይቶች ጠንካራ፣ ጤነኛና ውጤታማ ፓርቲ የመገንባት አጀንዳ ቋሚ ትግል የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበናል።

በዚህ ምክንያት የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያችንን በማጎልበት፣ የአደረጃጀቶቻችንን ሁለገብ የተጽዕኖ አድማስ በማስፋት፣ የአሠራር ሥርዓቶቻችንን የበለጠ በማዘመንና የኢንስፔክሽንና የሥነ ምግባር ኮሚሽናችንን በየደረጃው ማጠናከር፤ እንደሚገባ አምነናል፡፡

በዚህም ጉድለቶችና ብልሽቶችን የማረም አቅም ያለው፣ ሀገራዊ የመንግሥት ኢንሼቲቮችን በሃሳብ የሚመራና የሕዝብ ንቅናቄዎችን በብቃት የሚያስተባብር ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር የጋራ አቋም ወስደናል።

በመሆኑም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታትም የአመራራችንንና የአባላችንን ብቃትና ጥራት በሥልጠናና በተከታታይ ውይይቶች በማሳደግ በአስተሳሰብና በተግባር ብልፅግና የሆኑ፣ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በውጤታማነት እየፈጸሙ የሕዝቡን ሕይወት የሚለውጡ፣ በሥራና በመኖሪያ አካባቢያቸው የጠንካራ ዲስፕሊንና የመልካም ሥነ ምግባር መገለጫ የሆኑ፣ የኢትዮጵያን ህልም እውን የሚያደርጉ አመራሮችና አባላትን በማፍራት፣ በማብቃትና የለውጡ ሞተር እንዲሆኑ በማድረግ በላቀ ውጤት የሚገለጽ ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት የምንሠራ ይሆናል።

ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት እንዲቻል አባላትን ለማጥራት የሚያስችል ውጤታማ የምዘናና የግምገማ ሥርዓት እንዲዘረጋ፤ የሥነ ምግባርና የሞራል ዝቅጠት ተጠቂ በሆኑ አመራሮችና አባላት ላይ የማረም ተግባር እንዲከናወን፤ አዳዲስ አባላትን የመመልመል ሥራ በጥራትና በብቃት እንዲፈጸም እንደምናደርግ እናረጋግጣለን፡፡

ጠንካራ ፓርቲ ለመገንባት እንዲቻል ዘመኑን ማላመድ የሚያስችሉ የሃሳብና የታሪክ ውህደት በመፍጠር፣ መዋቅራዊ ልህቀት በማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ስክነትን እውን በማድረግና የውጤት ዘላቂነትን በቁርጠኝት ለመፈጸም ዳግም ቃል እንገባለን!!!

2ኛ. የተቋማት ግንባታ ስኬት ለውጤታማ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በእጅጉ ወሳኝ ነው ብለን እኛ ብልፅግናዎች ከልብ እናምናለን።

ከዚህ ጽኑ እምነት ተነስተንም ዴሞክራሲን ተቋማዊና ሕዝባዊ ባሕል በማድረግ የሀገረ መንግሥት ቅቡልነትን ለማረጋገጥ ወደ ተጨባጭ ሥራ ገብተናል።

በመሆኑም የተጀመረውን የተቋማት ሪፎርም በየዘርፉና በየደረጃው አጠናክረን በማስቀጠልና ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸውን ተቋማት በማባዛት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራችንን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆምና ጠንካራ የዴሞክራሲ ባሕል ለመፍጠር አበክረን የምንሠራ ይሆናል።

ፓርቲያችን የሚመራው መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት ልዩ ልዩ ሀገራዊ የዴሞክራሲ ተቋሞችንና የሀገር ደኅንነትንና ሉዓላዊነትን የሚጠብቁ ተቋሞቻችንን አቅም፣ ብቃትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባሕል ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጉባኤያችን በስኬት ተመልክቷል።

በመሆኑም ሁሌም እነዚህ ተቋሞቻችን አስተማማኝ የሀገር ጋሻና መከታ ሆነው እንዲገነቡና ነፃነታቸው ተጠብቆ እንዲቀጥል በሙሉ ልብ እንደግፋለን!!! ከዚህም ጋር ተያይዞ የሕዝባችን ፍትሕ የማግኘት መብት በተሟላ መልኩ እንዲረጋገጥ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን የማዘመን፣ ብቁ ባለሞያዎችን የማፍራት፣ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጥ የማስቻል፣ የዳኞች ነፃነትንና የዳኞች ተጠያቂነትን በሚዛን የማረጋገጥ ተግባራት እንዲከናወኑ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንታገላለን፡፡

3ኛ. ሕልማችን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እውን በማድረግ የሀገራችንን ብልፅግና ማረጋገጥ ነው። ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ማየትን በእጅጉ እንሻለን።

ሕልማችን ሁለንተናዊ ብልፅግና የተረጋገጠበትና አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን የበቃች እና ዓለም አቀፋዊ የተጽዕኖ አድማሷ የሰፋ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው።

በጉባኤያችንም ሆነ በቅድመ ጉባኤ ኮንፈረንሶቻችን ሕልማችን እውን ይሆን ዘንድ እያንዳንዳችን ለኢትዮጵያ ብልፅግና በላቀ ተነሣሽነትና ቁርጠኝነት መሥራት እንዳለብን ከልብ ተግባብተናል።

ለኢኮኖሚ ብልፅግና ግቦቻችን በጋራ በመቆም ኢኮኖሚያችን ነባር አቅሞችን የሚያጠናክር፣ ወደ አዳዲስ ዘርፎች የሚሸጋገርና ወደ መጪው ዘመን የፈጠራ ኢኮኖሚ የሚያስፈነጥር እንዲሆን በውጤታማነት ለመታገል ወስነናል።

ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ሥርዓት በመፍጠር፣ ሀገራችንን ከብድር ጫና የሚያላቅቅ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉን አቅጣጫዎች አስቀምጠናል። ገቢ የመሰብሰብ ዐቅማችንን በማጎልበት የሕዝባችንን አዳጊ ፍላጎቶች ለመመለስ በቁርጠኝነት እንሠራለን።

የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራማችን ወደ ቋሚ ሕዝባዊ ባሕልነት እንዲሸጋገር የሕዝባችንን ተሳትፎ ከፊት ሆነን ለመምራት ጠንካራ አቋም ወስደናል።

በመሆኑም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የተቃና የኢኮኖሚ ማሕቀፍ በመገንባት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ተደምሮ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በማምጣት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ያስችል ዘንድ በመፍጠር፣ በመፍጠንና በማላቅ እንሠራለን !!!

4ኛ. ብልፅግና ማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ደኅንነቱና ክብሩ ተጠብቆለት ማኅበራዊ መስተጋብሩም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል ሁለንተናዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ አካታች ማኅበራዊ ልማት ዓላማን ይዞ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።

ይህንን ለማረጋገጥ ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ ሁለንተናዊ ልህቀት ወሳኝ ግብዓት መሆኑን ያምናል። በሽታን ቀድሞ መከላከልና አክሞ ማዳን ለጤናማና አምራች ትውልድ ግንባታ ያለውን ፋይዳም በጥልቀት ይገነዘባል። በዚህ ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሣሽነት “ትምህርት ለትውልድ” የሚል ፕሮግራም ተቀርጾ በ2016 እና በ2017 ዓ.ም ብቻ 39 ቢሊዮን ብር የሚገመት የሕዝብ ተሳትፎ ለትምህርት ዘርፍ ልማት አውሏል።

በፓርቲያችን የሚመራው መንግሥት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል። ይህንኑ ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየርም የትውልድ ዕሴት ግንባታ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ትውልዱ መቻቻልን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን/ እኅትማማችነትንና አርበኝነትን እየተማረ እንዲያድግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚረዳ ሀገራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርጸን የምንንቀሳቀስ ይሆናል።

በጤና ዘርፉም የጤና መድኅን ተጠቃሚዎችን የማበራከት፣ ሆስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን የማስፋፋት ሥራዎችን ጨምሮ አመርቂ የጥራትና የተደራሽነት የማሻሻያ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ጉባኤያችን ተመልክቷል።

በተጨማሪም ፓርቲያችን ሰው ተኮር ባህሪውን መሠረት በማድረግ የሕፃናትን እና የአረጋውያንን ሁለንተናዊ መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ፣ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብት፣ ክብርና ደኅንነት የሚያስጠብቁ፣ አቅመ ደካሞችን እና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚደግፉ ሥራዎች በውጤታማነት መሠራታቸውን አረጋግጠናል።

የወጣቶችና የሴቶች ክንፎቻችንንም ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በማጠናከር ወጣቶችና ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው ከማረጋገጥ አኳያ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን አይተናል።

በመሆኑም እነዚህ የጀመርናቸው የማኅበራዊ ልማት ሥራዎቻችን የዕድገትና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ግቦቻችንን በሚያሳካና ማኅበራዊ ብልፅግናን በሚያረጋግጥ መልኩ በከፍተኛ ቁርጠኝነት አጠናክረን እናስቀጥላለን!!!

5ኛ. ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከርና የሀገረ መንግሥት ግንባታችን እንዲሳካ ነጣጣይ ትርክቶች ተሸንፈው አስተሣሣሪ ትርክት የበላይነት ማግኘት እንዳለበት እኛ ብልፅግናዎች እናምናለን፡፡

በመሆኑም ብሔራዊነት ገዥ ትርክት ሆኖ በልሂቃን እና በሕዝቡ ዘንድ እንዲሠርጽና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጠናከር እንሠራለን፡፡

ይህንንም የበለጠ ለማሳካት በማኅበረሰባችን መካከል መግባባትን የሚፈጥሩ ልዩ ልዩ ሕዝባዊ ውይይቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና በሁሉም አማራጭ መንገዶች እንዲከናወኑ እናደርጋለን፡፡

በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ውይይቶችን በማድረግ የብሔራዊነት ገዥ ትርክት እንዲሠርጽና በሕዝቦች መካከል ትስስርና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጠር እንሠራለን፡፡

የሚዲያ ነፃነትና ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አፍራሽ ተልዕኮ ይዘው ሚዲያውን ለግጭት፣ ለብጥብጥና ለወንጀል በሚጠቀሙት አካላት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠራ፤ አበክረን እንታገላለን።

የብልፅግና አመራሮችና አባላት መላውን ሕዝብ በማሳተፍ፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን ለገዥ ትርክት ግንባታ፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ለዕውቀት ሽግግር እና የኢትዮጵያን እውነት ለመግለጥ እንደምንጠቀምበት ቃል እንገባለን፡፡

6ኛ. ብልፅግና የሀገራችን ሲቪል ሰርቪስ የዕድሜውን ያህል ተቋማዊ ልህቀት ማረጋገጥ አልቻለም ብሎ ያምናል። በመሆኑም አሁን ላይ የጅምላ ሀገራዊ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እያደረገ አይደለም።

ከዚያ ይልቅ በየደረጃው እየተተገበረ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ፤ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅም መሪነት የተሣሠረ፤ ከሌብነት እና ከብልሹ አሠራር የተላቀቀ፤ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት እንዳለበት ፓርቲያችን ያምናል።

ለዚህም ተቋማዊ ባህሪን መሠረት ያደረገ፣ ገቢር ነበብ ሪፎርምን ለማሳካት በቁርጠኝነት እና በከፍተኛ ትኩረት እየሠራ ይገኛል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር በተለያየ መልክና ደረጃ የሚገለጹ ብልሹ አሠራሮች ሕዝባችንን ለእንግልትና ለእሮሮ እያጋለጡ መሆናቸውን ጉባኤያችን በዝርዝር ገምግሟል።

በመሆኑም ዜጎች የሚተማመኑበት የፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረውን የፍትሕ ሥርዓት ሪፎርም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማሻገር ወስኗል።

የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በፍጥነት በመተግበርም የመንግሥትን የማስፈጸምና የአገልግሎት አቅም ለማሻሻል ጠንካራ አቋም ወስዷል።

ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን ለመቆጣጠር በፓርቲያችን መሪነት በየደረጃውና በየዘርፉ ጠንካራ ትግል ከማካሄድ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ስለሆነም ውጤታማ የሆነ ገቢር ነበብ ሪፎርም ለማካሄድ እና በተለይም የሕዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ በልዩ ጥናት የአገልግሎት ማስተካከያ ዘርፎች ለማድረግና የሕዝቡን ርካታ ለማሳደግ ፓርቲያችን የወሰደውን ጠንካራ አቋም ለማስፈጸም ሌት ተቀን ለመሥራት ቃል እንነባለን!!!

7ኛ. ጉባኤያችን ባለፉት ዓመታት ፓርቲያችን በተከተለው ሀገራዊ ክብርን የሚያጎናጽፍና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ብሔራዊ ጥቅማችንና ክብራችንን ከፍ ያደርጉ ሥራዎች መፈጸማቸውን በድል ተመልክቶታል።

ኢትዮጵያን የብሪክስ አባል ለማድረግ የተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግልና የተገኘው ውጤት የፓርቲያችንና የመሪያችንን ዘመን የዋጀ ብቃት ህያው ማሳያ ነው።

የዘመናት የትውልድ ጥያቄ የነበረውን ዘላቂ የባሕር በር አጀንዳ በዓለም አደባባይ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው ከማድረግ በተጨማሪ ጥያቄው ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲያገኝ እየተደረገ ያለውን ጥረትም በከፍተኛ አድናቆት ተመልክተነዋል።

ፓርቲያችን የቀረፃቸው የዜጐች ክብር የውጭ ግንኙነት መርህ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቻችንን ደኅንነትና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ያስገኘውን ጥቅምም በሚገባ ገምግመናል።

ዲፕሎማሲያችን ከመሽኮርመም እየወጣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት መርህንና እውነትን መሠረት ባደረገ ይገባኛል ባይነት መጠየቅና ማስፈጸም የሚያስችሉ ተጨማሪ አቅጣጫዎችን መርምረን ትክክለኛውን መንገድ ቀይሰናል።

በመሆኑም እነዚህ አቅጣጫዎች በብቃት እንዲፈጸሙና ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎታችን ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እስኪያገኝ በሙሉ አቅማችን በተገኘው የዓለም መድረክ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ቆርጠን መነሣታችንን እናረጋግጣለን!!!

8ኛ. ፓርቲያችን ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም የሀገራችን የህልውና መሠረትና የሁለንታናዊ ብልፅግናችን ዓይነተኛ ዋስትና መሆኑን በጥልቀት ይረዳል።

በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ በዚህ ጉባኤው የተጀመረው አካታች ሀገራዊ ምክክር በስኬት ተጠናቆ የኢትዮጵያን የዘመናት የፖለቲካ ስንክሳር እንዲዘጋ፣ በልዩነትና በግጭቶች አያያዛችን ላይ ዘላቂ የመፍትሔ መንገዶች እንዲቀይስና ከተቻለም በጋራ ራዕያችን ላይ እንዲያግባባን ሂደቱን በሙሉ ልብ ለመደገፍ ወስኗል።

ለተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፕሮግራም ተግባራዊነትና ስኬታማነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትም ይሠራል።

አዎንታዊ ዘላቂ ሰላማችንን እያስተጓጐሉ ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጨማሪ አቅጣጫዎች አስቀምጧል።

ግጭትን ለማስቀረትና መረጋጋትን ለመፍጠር ሁሉም አመራርና አባል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተስማምተናል።

ስለሆነም ለጉባዔያችን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ተግባራዊነት ተግተን በመሥራት የሀገራችንን ሰላም ለማረጋገጥና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠናክረን ለማስቀጠል ሁላችንም በአንድነትና በጽናት እንቆማለን!!!

በመቀጠልም እኛ የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች ከዚህ የጋራ መስዋዕትነታችንና ድላችን ዘለዓለማዊ ዓርማ ከሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ ለመላ ኢትዮጵያውያንና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የምናስተላልፈው መልዕክትና አደራ አለን።

የተከበራችሁ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች!

ፓርቲያችሁ ብልፅግና በመጀመሪያ ጉባዔው ዋዜማ ላይ በተካሄደው ፍጹም ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሌሊት ቁር፣ የቀን ሀሩር ሳይበግራችሁ፣ በአስደማሚ ጽናት፤ በእልህና በቁጭት ተሰልፋችሁ የተጣለባችሁን ኃላፊነት እድልም አደራም እንደሆነ ከልብ ያምናል።

ፓርቲያችን በምርጫ የጣላችሁበትን ኃላፊነትና የሰጣችሁትን እምነት የሚያከብረው ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የኢትዮጵያን ሕልም እውን ለማድረግ በሚረዱ ሥራዎች ላይ በመረባረብ፣ ድህነት፣ ተረጂነትና ውርደትን ድል በመንሣት፣ የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት በመቀየርና ጠንካራ ተቋማትንና ሥርዓትን በመገንባት እንደሆነ በአንክሮ ይገነዘባል።

በዚህ ረገድ ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት ዓለምን የሚያስደምም ዕድገትና መነቃቃት የፈጠርነውና ሀገራችንን በአፍሪካ 5ኛ፣ ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት 3ኛ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ 1ኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እንድትሆን ማድረግ የቻልነው ሀገር በቀል እና የብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ተከትለን ነው።

ቀድሞም ቢሆን በጀግንነት ሀገራዊ ክብራችንን ተጎናጽፈን ስናበቃ ዓለም በተመጽዋችነት የመዘገበን በራሳችን ስህተት ነው።

ዛሬ ግን ፓርቲያችን ለልጆቻችን ምንዳን እንጂ ዕዳን አላወርስም በሚል አቋም ቆርጦ ተነሥቷል። ስለሆነም በራሳችን ጥረት በዐውደ ውጊያ ወደተጎናጸፍነው የክብር ማማ ተመልሰን መውጣት አለብን።

ድህነት ያመጣብንን ሀገራዊ ውርደት መስበርና ዳግም ገናና መሆን የምንችለው በእልህ፣ በቁጭትና በአዲስ ብሔራዊ የአርበኝነት ስሜት የራሳችንን ታሪክ ለመሥራት ከታገልንና ለድል ከበቃን ብቻ ነው።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ የማድረግ ትልቁ ሸክም የሚወድቀው በእኛ ኢትዮጵያውያን ትከሻ ላይ ነው። ታዲያ ይህ ራዕይ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታ፣ ሙሉ ትብብርና ጠንካራ ተሳትፎ ውጭ ለስኬት ሊበቃ አይችልም።

ፓርቲያችን ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የወሰደውን ተልዕኮ ለማሳካት የሚመራበትን የመደመር ዕሳቤ መሠረት በማድረግ ያዘጋጃቸው እና የውስጠ ፓርቲ ዐቅሙን ለማጎልበት የተጠቀመባቸውን ያደጉና አሻጋሪ ሃሳቦቹን ከፓርቲ አጥር እያወጣ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማዕከል ባደረገ መልኩ ለሕዝቡ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ያደርገው ለዚህ ነው።

ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገብናቸው ሁሉም ድሎች የተገኙትም ሕዝቡ በፓርቲያችን ላይ ባሳደረው እምነት፣ በሰጠው ድጋፍና ባደረገው ተሳትፎ ልክ ነው።

እስከ ቀጣዩ ጉባኤው ድረስም ሕዝቡን በሁሉም ሀገራዊና ከባቢያዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በንቃትና በስፋት ለማሳተፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ሲያረጋግጥላችሁ በላቀ ኩራትና ቁርጠኝነት ነው።

እኛ ብልፅግናዎችና መላው ኢትዮጵያውያን የጀመርነው ለውጥ የሀገራችንን የቆዩ ውስብስብ ችግሮች ከመሠረቱ የሚፈታና ስብራቶችን የሚጠግን ነው።

በመሆኑም በለውጡ ሂደት እዚም እዚያም ያጋጠሙ ችግሮችና ጉዳቶች እያመመንም ቢሆን ለውጥ የሚያልፍበትን ተፈጥሯዊ ባሕሪ በመረዳትና መጭውን ብሩህ ዘመን በመሻት ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።

ይህን የትግል ጉዞ የሚፈትኑ አንድም ከነባሩ የፖለቲካ ባሕል የሚመነጩ ፈተናዎች፣ ሁለትም አዲሱ ዘመን በራሱ የሚፈጥራቸው አዳዲስ ፈተናዎች መኖራቸውን ተገንዘበንና ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር ልምዳችንን ተጠቀምን ሁል ጊዜም ወደ ፊት እንራመዳለን።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ የጀመርነው ትግል ግቡን ይመታ ዘንድም ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን አስተሳስረን በመመልከት፣ የወል ትርክታችንን በመገንባትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ጠብቀን በፍጹም የአርበኝነት መንፈስና ወኔ እንዘልቃለን።

በሂደቱም ጠንካራ ፓርቲና መንግሥት በመገንባት የወል ሕልማችን ዳር እንዲደርስ የድርሻችንን በማበርከት የሀገራችንን ቅቡልነትና ከፍታ ከግብ እናደርሳለን።

ይህን የተቀደሰ ዓላማችንን በመደገፍ ከፓርቲያችንና ከመንግሥታችን ጎን ለቆማችሁት በሙሉ ያለንን ልባዊ አክብሮት እየገለጽን በቀጣይም አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ታደርጉልን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

እኛም ክቡር ቃላችንን ወደ ባሕል በማሸጋገር ኢትዮጵያን ማጽናት ብቻ ሳይሆን ወደ ብልፅግና ማማ ማድረሳችን አይቀሬ መሆኑ እሙን ነው!!!

በቀጣዩ ጉባኤያችን ስንገናኝ ከተሰጠን በላይ ሠርተን፤ ከሚጠበቅብን በላይ ፈጽመን፤ ኢትዮጵያን ይበልጥ ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና አሸጋግረን እንደሚሆን እምነታችን ጽኑ ነው፡፡ ከጉባኤያችን ያየነው ተስፋ ይሄንኑ በጽኑ ያረጋገጠ ነው፡፡

ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

እናመሰግናለን!

Recommended For You