
ከእናቷ ብርታትና ጥንካሬን፤ አልበገር ባይነትን፤ ለዓላማ መጽናትን፤ አዛኝነትና ለሌሎች መኖርን ወርሳለች። ለእናቷና ለሀገሯ ያላትን ፍቅር ስትገልጽ ቃላት ይከዷትና እንባዋ ይቀድማል። ለሁለቱም ያላትን ፍቅርና ክብር በቃል ሳይሆን በተግባር የገለጸችባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።
እርሷ ብርታትን ከእናቷ ወርሳለችና ያላትን የሕይወት ልምድ ለመሰሎቿ ለማካፈል ስስትን አታውቅም፤ እንደወርቅ ተፈትና ዛሬዋን ያደመቀች ናትና ዓለም እንድትደምቅላት ትፈልጋለች፤ የልጅነት ሕልሟን እየኖረችው ትገኛለችና ሴቶች ወደ ሕልማቸው እንዲቀርቡ ትሻለች፤ የወደፊት ሕልሟም ብዙ ነው፤ ከራሷ ተሻግሮ ብዙዎች እንዲኖሩበት አጥብቃ ትመኛለች፤ በብርታቷ ሌሎች እንዲበረቱ፣ በጀግንነቷ ሌሎች እንዲጀግኑ በርትታ ታበረታለች። የዛሬ “የሕይወት ገጽታ” ዓምድ እንግዳችን ብቸኛዋ የአገር አቋራጭ ከባድ መኪና አሽከርካሪ ሰሚራ ይማም።
ያልተኖረ ልጅነት
የተወለደችው በደቡብ ወሎ ከደሴ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ገርሻ ወይም ግራኝ ሜዳ በምትሰኘው ትንሽ የገጠር ከተማ ነው። ለቤተሰቦቿ የመጨረሻና 6ኛ ልጅ በመሆኗ የተለየ እንክብካቤ እንዳገኘች ታስባለች። አባቷ አቶ ይማም በላቸው የአንድ ዓመት ልጅ እያለች ከዚች ዓለም በማለፋቸው እናቷ ወይዘሮ ዘይነባ መኮንን ናቸው የአባትነት ሚናን ደርበው በመወጣት ያሳደጓት።
እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ትምህርቷን እስከ 8ኛ ክፍል በአካባቢው ባለው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። በእናቷ የተሠራች እንደሆነች የምታስበው ሰሚራ ይማም ለእናቷ ያላት ክብር እዚህ ድረስ ነው አይባልም፤ እናቷ ስድስት ልጆችን ብቻቸውን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያሳደጉ፤ ለአካባቢው ሴቶች ምሳሌ የሆኑ፤ አስታራቂና የአካባቢው ነዋሪ የሚያከብራቸው ብርቱ ሴት እንደሆኑም ትናገራለች፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢው ስላልነበረ ወደ ደሴ ከተማ በመሄድ ተምራለች። ሰሚራ በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከሌሎች ሴት ተማሪዎች ለየት በማለት ትታወቃለች። ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ጋር ታዘወትራለች፤ ከሴቶች ጨዋታ ይልቅ ወደ ወንዶቹ ታደላለች፤ በተለይም የመረብ ኳስ ጨዋታ ነፍሷ ነው። የመረብ ኳስ ጨዋታም ቢሆን ከሴቶች ጋር ከምትጫወት ከወንዶቹ ጋር መጫወትን ትመርጣለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል ወደ ደሴ ከተማ እንደመጣች የመረብ ኳስ ፍቅሯ አይሎባት እንደነበር ታስታውሳለች። ከትምህርቱ ይልቅ ለጨዋታው በማድላቷ የደሴ ዙሪያን ወክላ በተለያዩ ከተሞች የመጫወት ዕድልም አግኝታለች። ከአካባቢዋ ርቃ ብዙ ውድድሮች ላይ መሳተፏ በራስ መተማመኗን እንዳዳበረላት ትናገራለች።
በመረብ ኳስ ፍቅር የተለከፈች ብትሆንም እንጀራ እንደማይሆናት ቀድማ ተረድታለች። ስድስት ልጆችን የማሳደግ ጫና እናቷ ላይ በማረፉ እናቷን የምታግዝበትን መንገድ ስትፈልግ የመረብ ኳሱን ነገር እርግፍ አድርጋ ትታለች፤ ገና በ14 ዓመትዋ ቤተሰቦቿን ለማገዝ በአንድ የቻይና የመንገድ ሥራ ኩባንያ በንብረት ክፍል ተቀጠረች።
እንደ እድሜ እኩዮቿ ጊዜዋን በመዝናናት አላሳለፈችም፤ በመንገድ ሥራ ኩባንያው ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርታለች። ይሁን እንጂ በልቧ በአካባቢው ወንዶች ብቻ የሚደፍሩትን ሥራ ለመሥራት በመወሰኗ የሎደር ኦፕሬተሮች ጋር በመጠጋት ተለማመደች። ገና 16 ዓመት ልጅ እያለች ሎደርን የመሰለ ከባድ ተሽከርካሪ በማሽከርከር አሠሪዎቿን አስደመመች። መንጃ ፈቃድ ለማውጣት እድሜዋ ስላልደረስ በግቢው ውስጥና በሥራ ቦታዎች ሎደሩን ብታገላብጠውም እድሜዋ 18 ዓመት እስኪሞላ መጠበቅ ግዴታዋ ሆነ። ከሁለት ዓመት በኋላ እድሜዋ ደረሰና በነፃነት የሎደር ኦፕሬተርነት የሚፈቅደውን ልዩ መንጃ ፈቃድ አውጥታ በሎደር ኦፕሬተርነት ተቀጠረች።
ብዙዎች “ይቅርብሽ ይሄ ሥራ ለሴት አይሆንም” ቢሏትም አሻፈረኝ ብላ በብቃት ለአራት ዓመታት ካለምንም እንከንና አደጋ ሠራች። በተለይ ለጋዋ ወጣት ሰሚራ ትልቁን ሎደር እንድትሠራበት ቻይናዎቹ አሠሪዎቿ ያበረታቷት እንደነበር ታስታውሳለች። ቻይናዎቹ በጣም ቢያበረታቷትና ክብር ቢሰጧትም እናቷ ግን አብዝተው ያዝኑባት ነበር። “በብዙ ችግር ያስተማርኩሽ ለዚህ ነው ወይ? እንዴት በዚህ እድሜሽ ከዚህ ከባድ ማሽን ጋር ትታገያለሽ?” እያሉ አደጋ እንዳይደርስባት ይጨነቁላት እንደነበር ትናገራለች።
በወቅቱ ከሎደሩ ላይ ሆና ሲያይዋት ብዙዎች እንደሚሳቀቁ ብታውቅም እርሷ ግን በከፍተኛ ትኩረትና ኩራት ሙያውን ወዳና ፈቅዳ በመሥራትዋ ምንም አደጋ አጋጥሟት አያውቅም። በተለይም የቻይናውያኑ ማበረታቻ ይበልጥ ያጀግናት ነበር። እነርሱ ስለሚተማመኑባት እርሷም በሥራ ብቃቷን አስመስክራ ታስደስታቸው ነበር።
የሰሚራ ሕ ይወት እ ንደ እ ድሜ እ ኩዮቿ ሳ ይሆን በ/አድቬንቸር/ የተሞላ ነበር፤ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ያዝናናታል፤ በተለይም “ይሄ ለሴት አይሆንም” ካሏት ሠርታ ካላሳየች እረፍት አይኖራትም፤ ትሞክረዋለች አይሳካላትም፤ አትችይውም መባልን አትወድም፤ መቻሏን በመከራከር ሳይሆን በተግባር ሠርታ ነው የም ታስመሰክረው።
ሰሚራ በትውልድ አካባቢዋ ባገኘችው ልምድ መሥራት እስካለባት ጊዜ ከሠራች በኋላ ራሷን ለማሻሻል ያልሞከረችው ነገር አልነበርም። ጥቂት ጊዜ በአካባቢዋ ከሠራች በኋላ በተሻለ ደመወዝ ወደ ወለጋ ሄዳ በሙያዋ መሥራት የምትችልበትን አጋጣሚ አገኘች። በወቅቱ ብዙዎች ከአካባቢዋ ርቃ ወለጋ መሄዷን አልደገፉላትም። በጣም ሩቅ በመሆኑ ውሳኔዋን እንድትቀይር ቢወተውቱም የሰሚራ ልብ አንድ ጊዜ ወስኗልና /መስሚያዬ ጥጥ ነው/ አለቻቸው። አላቅማማችም ወለጋ የሚባለው አካባቢ የት ይሁን የት ባታውቀውም ሻንጣዋን ብቻ አንጠልጥላ ወደ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ ሄደች።
ወለጋ ስትደርስ እንዳስፈራሯት ሳይሆን አብረዋት የሠሩ ጓደኞቿን አገኘችና በደስታ ተቀበሏት። ብቸኝነቷን አስረስተው ሥራዋ ላይ ብቻ እንድታተኩር አደረጓት። ይሁን እንጂ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ሥራዋን መቀጠል አላስቻላትም። ብዙ ነገሮችም እንዳሰበቻቸው አልሆኑላትም፤ ያላት አማራጭ አልቻልኩም ብሎ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ሌሎች አማራጮችን መሞከር ነበር። ወደ አዲስ አበባ በአንድ ድርጅት በክሬሸር ኦፕሬተርነት በመቀጠር ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ መጣች፡
ሰሚራን የሚያሸንፍ ምንም ነገር አልነበርም፤ ያጋጠማትን አስቸጋሪ የሚባሉ ፈተናዎችን በመቋቋም በአጭር ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ሥራ ማግኘቷ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር። እሷ ግን ዓላማዋ ሩቅ ነበርና የሚያጋጥሟትን የዛሬ መሰናክሎች ነገዋን እያሰበች በብቃት ነበር የምታልፋቸው። ወደ አዲስ አበባ መግባቷም ራስዋን ለማዝናናትና የሀገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ እየሠራሁ ነው ለማለት ሳይሆን ራሷንና ብቃቷን ለማሻሻል ነበር ያዋለችው። ያላትን ገንዘብ አጠረቃቅማ 5ኛ መንጃ ፈቃድ አወጣች። የምትሠራው የሎደርና ክሬሸር ኦፕሬተርነት በመሆኑ ብዙ አስቸጋሪ የሚባሉ ነገሮችን አሳልፋለች። አሁን ደግሞ ሕይወት መለወጥ አለበትና 5ኛ መንጃ ፈቃዷን በማውጣቷ የከባድ መኪና አሽከርካሪ የመሆን ሕልሟን የምታሳካበት ጫፍ ላይ ደርሳለች።
የሰሚራ 5ኛ መንጃ ፈቃድ መያዝ ያልተዋጠላቸው ብዙ ወዳጆች ነበሯት፤ “አንች ሴት ሆነሽ ከባድ መኪና ለማሽከርከር ማሰብሽ እብደት ነው። መንገድ ላይ የሚያጋጥምሽን ፈተና እንዴት ልትቋቋሚው ነው?” እያሉ ሃሳቧን ለማስለወጥ የሞከሩም እንደነበሩ ታስታውሳለች። እርሷ ግን ያሰበችውን ነገር ለማሳካት እረፍት አታውቅምና በአጭር ጊዜ ነበር ወደ ከባድ መኪና አሽከርካሪነት የገባችው።
ወደ ሕልም ጉዞ
በልጅነትዋ ከአጎቷ ልጅ ጋር በሽቦ መኪና ሠርተው ሲነዱ የሷ ምርጫ ከባድ መኪና ነበር። የአጎቷ ልጅ ግን አንች አትችይም በሚል መንፈስ የመኪናው ረዳት እንድትሆን ሲያደርጋት “ምን ሲደርግ እኔ ነኝ ሹፌሩ” እያለች ታስቸግረው እንደ ነበር ታስታውሳለች።
በወቅቱ በአካባቢያቸው የሴት ሹፌር አይተው አያውቁምና “የሴት ሹፌር የለምኮ” ስትባል “የሴት ረዳትም የለምና አንተ ረዳት ሁን እኔ የመጀመሪያዋ የሴት ሹፌር እሆናለሁ” በማለት ትሟገት ነበር። እንደተመኘችው ሆነላትና ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ ሁለቱም አሽከርካሪ ሆነዋል።
ሹፍርናን ያስመኛት የልጅነት ሕልም መነሻው ምን እንደሆነ ባታውቀውም የሎደር ኦፕሬተርነትን በመሸጋገሪያነት እንደተጠቀመችበት የምትናገረው ሰሚራ ለሎደር ኦፕሬተርነት ያላትን ፍቅርና ክብር አልደበቀችም። ለዚህም ነው 4 ዓመታትን በዚሁ ሙያ ውስጥ የቆየችው።
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን
5ኛው መንጃ ፈቃዷ የሥራ ዕድልን በቀላሉ ይዞ አልመጣላትም፤ እንዲያውም ከጠበቀችውና ካሰበችው በላይ ፈተና ነበር የሆነባት። መንጃ ፈቃዷን እና የሎደርና ክሬሸር ኦፕሬተርነት የሥራ ልምዷን ይዛ ያልረገጠችው ቀጣሪ መሣሪያ ቤት እንዳልነበረ ታስታውሳለች። የሁሉም ምላሽ “ሥራው ለሴት ልጅ አይሆንም አርፈሽ ራይድሽን ሥሪ” የሚል ነበር። “በምን ድፍረትሽ ነው ጅቡቲ ደረስ ሄደሽ የምትሠሪው፣ ስለ ረጅም ጉዞ መረጃ የለሽም ወይስ ሴትነትሽን ረሳሽው?” እያሉ ሴት መሆኗን ሊያስታውሷት የደፈሩም ነበሩ። አንዳንዶቹ ደግሞ መረጃዋን ተቀብለው የውሃ ሽታ እንደሆኑባት አትዘነጋውም። ያመለከተችባቸው ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ምላሽ ቢሰጧትም እርሷን ይበልጥ አፈረጠማት እንጂ አላኮሰሳትም።
በዚህ ውጣ ውረድ መሐል ቻይናዎች ሰመራ ላይ የክሬን ኦፕሬተር ይፈልጉ ነበርና የሚያውቋት ሰዎች ጠቆሟት። ከቻይናዎች ጋር ብዙ ጊዜ በመሥራትዋ ምን እንደሚፈልጉ ታውቃለችና አላቅማማችም፤ በትንሽ መኪና አዲስ አበባ ላይ ተፈትና በብቃት በማለፏ ወደ ሰመራ አመራች።
ሰሚራ ደፋር ናት፤ ትኩረቷ ሁሉ ሥራና ሥራ ብቻ ነው፤ ሴትነቷን አክብራ በብቃቷ ታምናለች እንጂ ወንዶች ከሚሠሩት እንደማያሳንሳት ታውቃለች፤ በስም ብቻ ወደምታውቀው ሰመራ ለመሄድ ስትወስንም ወዳጆቿ እንደተለመደው ውሳኔዋን አልወደዱላትም ነበር። “እንዴት አዲስ አበባን ትተሽ ወደ በረሃ ትገቢያለሽ?” እያሉ የሆነውንም ያልሆነውንም እየነገሩ ቢያስፈራሯትም በረሃ ካለ ሥራ ከመቀመጥና የሰው እጅ ከማየት አይከብድምና ከውሳኔዋ ያንሸራተታት አልነበረም።
“ሰው የሚኖርበት ቦታ እንዴት እኔ መኖር ያቅተኛል” ያለችው ሰሚራ ሻንጣዋን ይዛ ሰመራ ስትገባ ያመናት አልነበርም። የዓላማ ፅናት የሌለው ሰው ያሰበበት
አይደርስም የምትለው ሰሚራ የሰመራ ሙቀትና የቦታው ርቀት ምኗም አልነበረም። ሰመራ በአንድ የውሃ ቁፋሮ ድርጅት ውስጥ የክሬን ኦፕሬተርነት ተቀጠራ መሄዷ እውን ሆነ። በርግጥም ሰመራ ለሰሚራ በበጎ አልተቀበለቻትም። ጥቂት ጊዜ እንደሠራች በከፍተኛ ደረጃ ታመመች፤ ከረዳቷ ጋር ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ሆነ፤ ድርጅቱም ከአቅሙ በላይ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ላካቸው።
“ተይ ይቅርብሽ አይሆንም” ያሉት የሰሚራ ወዳጆች ቢሳለቁም ሰሚራ በውሳኔዋ አልተፀፀተችበትም። ተፈተነች እንጂ አልወደቀችበትም። ቤተሰቦቿ ከሆስፒታል አውጥተው ሌላ ቦታ ሕክምና እንድታገኝ አደረጉ፤ በሕክምናም በፀበሉም ብለው ስትድን አብሯት የታመመው ረዳትዋ ማለፉን ስትሰማ በእጅጉ አዘነች። የበሽታው ምንነት ሳይታወቅለት ላለፈው ረዳትዋ እንድታዝን ቢያደርጋትም ይህ በሰው ልጅ ላይ የሚያጋጥም ፈተና መሆኑን ተቀብላ ወደ ራስዋ ማሰብ ጀመረች። ከዚህ በፊት በሠራችባቸው ጎጃም መርጡለማሪያም አካባቢ በሚገኘው የዓባይ በረሃ የደረሰባት ፈተናን በማስታወስም ከማሽነሪ ሥራው ይልቅ ሹፍርናው ላይ ማተኮር እንዳለባት ወሰነች።
5ኛ መንጃ ፈቃዷን ይዛ ሥራ ብትፈልግም አምኖ የሚቀጥራት በማጣትዋ ተስፋ አልቆረጠችም። ወደ ዱከም አካባቢ በመሄድ አሸዋ የሚጭኑ ሲኖ ትራኮችን በ300 ብር የቀን አበል እየተከፈላት አሸዋው ካለበት መቂ እስከ ዱከም ድረስ እያመጣች ለሹፌሮቹ ማስረከብን ተያያዘችው። ሥራው አድካሚ በመሆኑ ከሚከፈላት ጋር ባይመጣጠንም ከመቀመጥ ይሻላልና እሱን እንደ መሽጋገሪያ እየሠራች ሹፌሮች ማኅበር ላይ የአባልነት ጥያቄ አመለከተች።
እነርሱም አዳዲስ መኪኖችን ከጋላፊ የሚያስመጡ ቢሆንም ደፍረው ሊቀጥሯት አልቻሉም። ይሄም አልተሳካምና “እስኪያልፍ የአባትህ አሽከር ይግዛህ” እንዲሉ የአሸዋውን ሥራ በ300 ብር አበል እየሠራች የራሷ ጊዜ እስኪመጣ በትዕግስት ጠበቀች።
ከትንሽ መጉላላት በኋላ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ መቶ ሹፌሮችን እንደሚቀጥር ሰማች። ፈትኖ የሚያስረከበው ደግሞ የሹፌሮች ማኅበር በመሆኑ መረጃዎቿን ይዛ አመለከተች። ነገር ግን ለፈተና የጠራት አልነበርም፤ ለፈተና ባለመጠራቷ ያዘነችው ሰሚራ ተስፋ ቆርጣ እንባዋን ዘርታ ለመቀመጥ አልወሰነችም፤ “እልህ ጩቤ ያስውጣል” ነውና የፈተናውን ቀን አጠያይቃ ከዱከም ፈተናው ወደሚሰጥበት አዲስ አበባ የሺ ደበሌ አካባቢ ከፈተናው ሰዓት ቀድማ ተገኘች።
“ቀድሜ በቦታው ሲያገኙኝ ‹ስልክሽ አልሠራ ብሎን ነው› የሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት ሰጥተው እንድፈተን ዕድሉን ሰጡኝ” የምትለው ሰሚራ ይሄን አጋጣሚ ማሳለፍ እንደሌለባት በማመን ራስዋን ለፈተና ዝግጁ አድርጋ ሦስተኛ ተፈታኝ ሆና ገባች።
መፈተኛዎቹ ገልባጭ ሲኖ ትራኮች በመሆናቸው አሸዋ ያመላለሰችባቸው ሲኖዎች ግፏን ቆጠሩላትና “ትንሽ እንደዳሁ በቃሽ ውረጂ ተባልኩ፤ ደነገጥኩና ጣልከኝ ማለት ነው? ስለው ፈታኙ ‘አንችን ጥዬማ ማንንም አላሳልፍም፤ አያያዝሽን ሳየው ትችያለሽ’ አለኝ፤ የሹፌር ማኅበሩ ኃላፊም ጎበዝ ብሎ አቀፈኝ፤ ላምን አልቻልኩም ነበር” ትላለች ወደሕልሟ ያደረሳትን ፈተና ስታስታውስ።
ሰሚራ አላመነችምና ከፊታቸው እንድትጠፋ ያደረጉት ነበር የመሰላት። ውጤት የሚለጠፈው በቀጣዩ ቀን በመሆኑ ማልዳ ተገኘች። እንደተባለውም “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃልና” በ96 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የፅናት ተምሳሌቷ ሰሚራ እውነትም አንደኛ ሁና አልፋለች።
ወደ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሂዳ ማለፏን ስታመለከት ደግሞ ሌላ ፈተና ተከተላት። “ተያዥ አምጭ” ተባለች። አዲስ አበባ ውስጥ ብዙም የምታውቀው ሰው አልነበርምና ከየት ታምጣ? ነገሮች ሁሉ ግራ ሆኑባት ቤተሰቦቿን ብትጠይቅም ሥራውን ስለማይወዱላት ማንም አባከና የሚላት እንደማይኖር ታውቃለች።
“በቅርበት ያሉ ወዳጆቼን ሁሉ ጠየኩ፤ አንዱ ወዳጄ 10ሺ ብር ክፈይና አለቃዬን ልለምንልሽ አለኝ፤ ወዳጅ ያልኩት ሰው እንደዚህ ሲለኝ በጣም አዘንኩ፤ እጄ ላይ የነበርኝን ከፍዬ አለቃው የተባለው ሰው ዋስ ሲሆነኝ ‘እንኳን እንዳንች ጠንካራ ለሆነች ሴት ይቅርና ለማንስ ብሆን’ ብሎ በደስታ ዋስ ሆነኝ 10ሺ ብሩን የተቀበለኝን ወዳጄን ግን ዛሬም ድረስ እንደታዘብኩት ነው” በማለት ሁኔታውን ታስታውሰዋለች።
ሀገር አቋራጯ ሰሚራ
ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በጥሩ አቀባበል አስተናገዷት፤ “ብቸኛዋ ሴት አሽከርካሪ በመሆንሽ ድምቀታችን ነሽ ብለው ለሁሉ ነገር ቅድሚያ እየተሰጣት ከባዱን የጭነት ተሽከርካሪ ተረከበች።
ሕልሟ እንደተሳካ ያመነችው ሰሚራ በሥራዋ ደስተኛ ሆነች፤ የሥራው ባሕሪ ሆኖ ለጭነት ሌሊቱን ሙሉ ተሰልፎና ተጋፍቶ መጫን፣ ሲሚንቶውን አራግፎ የሲሚንቶ ግብዓትን ከጅቡቲ ማምጣትን የሚጠየቅ ቢሆንም ለችግር የማትበገረው ሰሚራ በደስታና በትጋት ሥራውን ተያያዘችው። በአንድ ወር ውስጥ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብም በትጉሕ ሠራተኝነት ስሟ ተጠራ፤ 40ሺህ ብር እንደተሽለመች በአደባባይ ተነገራት፤ ብሩ እጇ ባይገባም አንደኛ መውጣቷና አክብሮቱ ብቻ ከትጋት አላቦዘናትም።
የሥራ ባልደረቦቿ ከጅቡቲ የድንጋይ ከሰል ለማምጣት ሲመደቡ ሲያቅማሙ እርሷ በደስታ ነበር የምትሄደው። የጅቡቲ የደርሶ መልስ ጉዞ እስከ 7 ቀን ድረስ ሊሆን ይችላል፤ ጅቡቲ ውስጥ ያለው ኑሮ ውድነት ተቋቁማ እንድትወደው ያደረጋት የሕዝቡ አቀባበል እንደሆነ ታስታውሳለች። ሹፌሮች እንደ ብርቅ ነው የሚንከባከቧት፤ መንገድ ላይ ጎማ መቀየር ቢኖርባት እያዩ አያልፏትም፤ ሁሉም ያግዛታል፤
ሰሚራ ከባድና አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜያቶችን ብታሳልፍም በሥራዋ ደስተኛ ሆናለች። ተረጋግታም መሥራት ጀምራለች፤ የጅቡቲ በረሃ ሰሚራን አላቀለጣትም፤ የመንገዱ አስቸጋሪነት ተስፋ አላስቆረጣትም፤ ውሃ ጥሙና እንግልቱን ተዝናንታበታለች እንጂ አላኮማተራትም። ሌሊቱን እንቅልፍ አጥቶ ተሰልፎ ጭኖ መንገድ ሳይዘጋ መውጣቱ፤ ረጅሙን መንገድ በብቃት ማሽከርከሩ የእለታዊ ተግባሯ ሆኗልና አንድም ቀን ለምሬት አልዳረጋትም።
ሰሚራ ራስዋን ለመፈተን ሁልጊዜም ዝግጁ ናት። ከባድ የሚባሉ ቦታዎች ላይ መገኘትና አይቻልም የሚባሉ ሥራዎችን ሠርቶ ማሳየት ያስደስታታል። የወንድ እና የሴት የሚባለው የሥራ ልዩነት እሷ ውስጥ ቦታ የለውም፤ ሁልጊዜም የሚያቅተኝ የለም ብላ በማሰቧ ሁልጊዜም ይሳካላታል።
ለሀገር የተከፈለ ዋጋ
የአሁነኛው ድፍረት ግን ብዙዎችን አስደንግጦ እንደነበር ታስታውሳለች። ብዙዎችም “አብደሽ ከሆነ ፀበል እንወስድሻለን” ብለዋታል። ነገሩ እንዲህ ነው ወቅቱ ተረጋግታ ኑሮዋን የጀመረችበት ቢሆንም፤ ከየመሥሪያ ቤቱ ሹፌሮች ለሀገር መከላከያ ግዳጅ የሚፈለጉበት ጊዜ ነበር።
ሰሚራ ግን በራስዋ ፈላጊነት “ሀገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ሁሉ ማገልገል እፈልጋለሁ” ብላ ነበር ለመዝመት የጠየቀችው። ይሄን ሃሳቧን የሰሙ ሁሉ “አርፈሽ ሥራሽን ሥሪ፣ ልጆችሽን ካለ እናት አታስቀሪያቸው” ብለዋታል። ሞት እንደጠራትም የተነበዩላት ነበሩ።
እርሷ ግን ወዶ ዘማች ሆነች፤ የመከላከያን ከባድ ተሽከርካሪ ተረክባ በታዘዘችበት ዓውደ ግንባር ሁሉ ፈጥና መድረስን ተያያዘችው። መከላከያ ስትገባ ጥቂት ጊዜ ሀገራዊ ግዴታዋን ተወጥታ ለመመለስ ቢሆንም ውስጡ ስትገባ ግን ያገኘችው ክብርና ፍቅር ሁሉን አስረስቷት እዛው አስቀራት። ሲቪሏ ሴት ሚሊቴሪ ለብሳ ድረሽ በተባለችበት ሁሉ ኮብራ እስካኒያ የተሰኘውን ከባድ ተሽከርካሪ ይዛ ሦስት ዓመት ከምናምኑን ሀገሯን አገለገለች፡ ሰሚራ የአንድ ዓመት ልጇን ጥላ ነበር የዘመተችውና ያን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲህ ታስታውሰዋለች።
ነገሩ እንዲህ ነበር፤ ወልዲያ ከተማ በግዳጅ ላይ እያለች ልጇ ሁለተኛ ዓመት ልደቷ እንደሆነ እየነገረች “አትመጭም? ልደቴን አታከብሪልኝም” እያለች ትጠይቃታለች፤ በዚህ ሁኔታ በጣም ደብሯት እያለች የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ያገኟትና ለምን እንደተደበረች ይጠይቋታል። የመደበሯን ምክንያት ትነግራቸዋለች። በወቅቱ የነበረውን ስሜት በኦን ላይን ያስተላልፉታል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያየው ሁሉ ነበር ኃዘኗን የተጋራውና የተረበሸው።
“ልጅሽ ያለችበትን ንገሪንና ሄደን ልደቷን እናክብርላት” ያሏትም ብዙዎች ነበሩ፤ እርሷ ግን ለልጇ እንዲህ የሚል መልዕክት ነበር ያስተላለፈችላት “ልጄ ሀገር ሰላም ሲሆን አብረን እናከበራልን፤ ዛሬ ግን የሀገሬ ነኝ፤ ሀገሬ በፈለገችኝ ሰዓት ማፈግፈግ አልፈልግም፤ እናትሽ ሰሚራ ትወድሻለች መልካም ልደት ይሁንልሽ፤ ሀገር ሰላም ሲሆን አብረን እናሳልፋልን”።
መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የነበረውን አክብሮትና ፍቅር ዛሬም ድረስ አትረሳውም፤ በተለይ ለሴት ልጅ ያላቸው ክብር አብራቸው እንድትቆይ አድርጓታል። ጦርነቱ በሰላም ሲቋጭ ነው እሷም ግዳጇን ጨርሳ በክብር የተሰናበተችው። ሰሚራ ተገቢውን ክብርና እውቅናም እንደተቸራት ትናገራለች። ሀገሯ በፈለገቻት ሰዓትም በደስታ ለማገለገል ፈቃደኝነቷ ዛሬም ድረስ እንዳለ ነው።
የመልካምነት ክፍያ
ሰሚራ በመከላከያ በአሽከርከሪነት ስትሠራ ስለእርሷ ዝና በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ ሰዎች ሲቀባበሉት ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኮካ ፋብሪካ ያያል። በዚህ አጋጣሚ ነበር አብራቸው እንድትሠራ የጠየቋት። በቀጥታ ወደ ኮካ ስትገባም በልዩ እንክብካቤ ነበር የከባድ መኪና አሽከርካሪ አድርገው የተቀበሏት።
“ ኮካ ለሴት ልጅ ክብር ያለው ድርጅት በመሆኑ መላውን ኢትዮጵያ ስዞር ምርጫዬን ያከብሩልኛል፤ በፈለኩት ነገር ሁሉ ይደግፉኛል፤ በሄድኩበት ሁሉ ልዩ ፍቅር አግኝቻለሁ” የምትለው ሰሚራ በምታገኘው ክብርና ሞራል በምርጫዋ እንድትኮራ አድርጓታል። የማኅበራዊ ሚዲያ ወዳጆቿም ፍቅራቸውን አሳይተዋታል። ማኅበራዊ ሚዲያው ከብዙ ሰዎች ጋር አስተዋውቋታል፤ መረጃ ለመለዋወጥም ተጠቅማበታለች።
ሰሚራ የሹፍርና ሙያ አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሆነ ታውቃለች። ወጥቶ መቅረት አለ፤ ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም ለሰሚራ ምንም ማለት አይደለም፤ ይልቁንስ ለሌሎች ብርታት ሆናበታለች፤ ለብዙዎች ከእርሷ ጥንካሬን አሻግራበታለች። በማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ የሚከተሏት አሉ፤ ብዙዎቹ በሷ ጥንካሬ በመገረም አርዓያቸው አድርገዋታል፤ በስደት ላይ አስቸጋሪውን ሕይወት የሚገፉ ሴቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው ለመሥራት ብርታት ሆናቸዋለች።
ሰሚራ 14 ዓመታት በከባድ መኪና አሽከርካሪነት ስታሳልፍ አደጋና ሰሚራ ተገናኝተው አያወቁም። ለዚህም ምክንያቱ ሙያዋን ወዳ በመሥራትዋና የጠንቃቃ አሽከርካሪነትን መርሕ መከተሏ፤ ሁልጊዜም ሙያዋ የሚፈቅደውን ሥነምግባር ጥንቃቄን መርሆዋ በማድረጓ እንደሆነ ትናገራለች።
ሰሚራ የራስዋ ማሠልጠኛ ኖሯት በርካታ ሴት አሽከርካሪዎች ወደ ከባድ መኪና አሽከርካሪነት እንዲመጡ ትፈልጋለች። ቢያንስ 20 በመቶ የሚሆኑት አሽከርካሪዎች ሴቶች ቢሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ያለውን የመኪና አደጋ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንሰው ታምናለች።
ሰሚራ የሁለት ልጆች እናት ናት፤ የሟች እህቷን ሁለት ልጆች ታስተምራለች ደካማ እናቷንም በመጦር ላይ ትገኛለች። ብትችልና አቅሙ ቢኖራት ከዚህም በላይ ሰዎችን በመርዳት መደሰት ትፈልጋለች አሁንም ቢሆን የሷን ድጋፍ ፈልገው ያጡ የሉም፤ የሰው ፍቅር የረበበባት ናት፤ብቻዋን መሆን አትፈልግም፤ ያላትን ተካፍላ መብላት ያስደስታታል።
ሰሚራ ለስሙ ቤትና ቤተሰብ አላት እንጂ ቤቷ ያለው መኪናዋ ላይ ነው። ሁልጊዜም ሻንጣዋ ዝግጁ ነው፤ ልብሶቿና መዋቢያዎቿ ሁሉ መኪና ውስጥ ናቸው፤ ከወር እስከ ወር መንገድ ላይ ናት፤ የሴት ወጉን እምብዛም አላየችም፤ በእርግዝና ላይ ሆና እስከ 9 ወር ድረስ አሽከርክራለች፤ ሁለተኛ ልጇን የወለደችው ከፊልድ መጥታ በቀጥታ ሆስፒታል በመግባት እንደሆነ ታስታውሳለች።
ችግር አይፈትናትም፤ ተስፋ መቁረጥ አያምበረክካ ትም፤ ዓላማዋን ለማሳካት ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትልም፤ ብዙዎች ከእርሷ ሕይወት እንዲማሩ ትፈልጋለች፤ የእናትነት ጫናው እንዳለ ነው፤ ልጆቿ ሲያም እና ቢላል የቤቷ ድምቀቶች ናቸው። በአገኘችው ጊዜ ሁሉ ትንከባከባቸዋለች፤ የቤት ውስጥ ሥራውም ቢሆን እንዲጎድል አትፈልግም፤ በዓል የሚባል ነገር የላትም በደረሰችበት ነው የምታከብረው። ጎረቤቶቿ የልጆቿ ነገር ይገዳቸዋል፤ በብዙ ነገር ያግዟታል፤ ዘመዶቿም ልጆቿን ይንከባከቡላታል።
ሁለተኛው እርግዝና ከባድ በመሆኑ ለአምስት ወራት ከመኪና እንዳልወረደች ታስታውሳለች፤ “ጎማ ልቀይር ወርጄ ነው ሐኪም ያየኝ፤ ወዲያው ሪፈር ሲጽፍ እየነዳሁ እንደሆነ ስነግረው ደንግጦ በዛው ነው ልወልድ የገባሁት፤ መኪናውን ባልደረቦቼ ናቸው የወሰዱት፤ የሥራ ባልደረቦቼ ብዙ ይደግፉኛል፤ ያግዙኛል፣ ያበረታቱኛል፤ ለሚያከብሩኝ፣ለሚያደንቁኝ ለሚያግዙኝ ሁሉ አመሰግ ናለሁ!” ትላለች።
ሥራዋን ትዝናናበታለች እንጂ የመኖር ግዴታዋ እንደሆነ አታስበውም፤ በፍቅርና በደስታ ነው የምትሠራው፤ ሥራዋ ማስተዋልን የሚጠይቅ በመሆኑ ሀገሪቱ ሰላም ሆና ሁሉ በማስተዋል ቢያሽከረክር አደጋ እንደማይደርስ ትናገራለች፤ “ብዙ ሰው በራሱ ሃሳብ እየተብሰለሰለ ስለሚያሽከርክር ነው አደጋ የሚደርሰው” የሚል እምነት አላት።
ሰሚራ ከ15 ዓመት ላላነሰ ጊዜ አሽከርክራለች። በእነዚህ ጊዜያት ብዙ ገጠመኞችን እንደምታስተናግድ ይታመናል። ዘበኛ ሌባ መስላው ከራሷ መኪና አባሯታል፤ አፋር በረሃ ላይ ተኝታ እያለ ዝንጀሮ ከእንቅልፏ ቀስቅሶ አስደንግጧታል፤ ትራፊክ ወንድ አሽከርካሪ እያለማመዳት መስሎት ሹፌሩን ቀስቅሽው ብሏትም ያውቃል።
ምክር ቢጤ
ሁሉም ሴቶች ማድረግ ይችላሉ፣ ራሷን ያከበረች ሴት የሚያግዳት ነገር አይኖርም፤ የቤት እመቤትነት ሥራ ፈትነት ሳይሆን ከባዱ ሥራ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፤ ሴቶች ሥራ መምረጥ የለባቸውም ሁሉንም ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ማመን አለባቸው።
ሽልማቶችን ከመከላከያ ሎጂስቲክ መምሪያና ከትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር አግኝታለች፤ የድሬዳዋ ከንቲባን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እውቅናን ሰጥተዋታል፤ በጀግንነቷ አመስግነዋታል። ወደፊት ዓላማዋ ተሳክቶ የማሠልጠኛ ተቋም ብትከፍት ለብዙ ሴቶች ልምዷን እያካፈለችና እያበቃች ወደ ገበያው እንዲገቡ ማድረገ እንደምትፈልግ ትናገራለች፤
ሰሚራ እንደ ሀገር ብዙ የምታስባቸው ነገሮች ቢኖሩም ብዙ ሴቶችን እንደ እርሷ ደፋር እንዲሆኑ ትፈልጋለች። በርካታ ሴቶች እንዲተኳት ትሻለች፤ ይሄን ለማድረግ ደግሞ እንደ ወርቅ ተፈትና ያለፈች ስለሆነች እንደሚሳካላት ታምናለች። ከመንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ከቀረጥ ነፃም ይሁን በብድር ተሽከርካሪ ብታገኝ እንደ እርሷ በችግር ውስጥ እያለፉ ያሉትን ሴቶች ማገዝ ትፈልጋለች።
የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን ሹፌር መንግሥት ሊደገፈው ይገባል፤ በየመንገዱ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ቀረጥ ቢያነሳ፤ ለአሽከርካሪዎች በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ያገባኛል ብሎ ቢሠራ፤ በአጠቃላይ ዋስትና ያለው ሥራ እንዲሆን ቢደረግ” የሚለውን ሃሳቧንም ታጋራለች።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም