
/ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው የብልፅግና ጉባኤ ያደረጉት ንግግር ሙሉ ቃል/
ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ክቡር አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የተከበራችሁ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የተከበራችሁ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ፣ ክቡር ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የቀድሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት፣ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የቀድሞ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የተከበራችሁ የእህት ፓርቲ ተወካዮች፤ የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፤ የተከበራችሁ የሀገር ሽማግሌዎች የተከበራችሁ ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም የኢትዮጵን ብልፅግና እውን ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ሚና ያላችሁ የአርሶ አደር ተወካዮች የባለሀብት፣ ወጣቶች የሴት ተወካዮች በሙሉ እንኳን ለዚህ ታሪካዊ ቀን በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ።
በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ በጣም አጭር ነው። 60 ዓመት ያልሞላው ታሪክ ነው። ላለፉት 60 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ሀሁን ስንጀምር ብልፅግናን እስከፈጠርንበት ጊዜ ድረስ ያሉ ድካሞች፣ ስንክሳሮች፣ ውድቀቶች ልንሻገራቸው ያልቻልናቸው ድካሞች አንደ ፓርቲ ለውጥ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ለውጥ መሪ መሆናችን አለመገንዘባችን ነው።
ለውጥ መፍጠር ብቻ ለውጥ ለመምራት የሚያስችል ብቃት እስካልፈጠረ ድረስ የተሟላ የፓርቲ ሕልውና አይኖረውም። ለውጥ መፍጠር ማለት ስላለው ችግር አብዝቶ መናገር፤ ስላለው ድካም አብዝቶ መናገር ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ማፍለቅ ይጠይቃል።
የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ ብቻ ሳይሆን የምንወድው፤ የምንፈልገውን ነገርም አስተሳስረን ማስቀመጥ፤ ማሳየት ማመላከት ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት የነበረን የፓርቲ የፖለቲካ ልምምድ የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ፤ ልናፈርስ ልንንድ የፈለግነውን ያለ ማስረጃ መክሰስ እንጂ፤ ልንገነባ የምናስበው ልናመጣ የምፈልገውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንት ነበረብን።
ብልፅግና ሊያፈርስ የሚፈልገው በጣም ኋላቀር አሠራሮችና ልምምዶች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ነገር ግን ሊያፈርስ የሚፈልገው ነገር ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አልቆ መገንባትንም አስቀድሞ የሚያስብ ነው። ፒያሳን ማፍረስ ሳይሆን ፒያሳን አልቆ መገንባት የብልፅግና መለያው ነው።
የአንድ ፓርቲ አስኳሉ ሀሳብ ነው። የደረጀ ሀሳብ የሌለው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን ማፍረስ፤ ለውጥ መፍጠር ቢችልም ለውጥ ለመምራትና የሚያልመውን ለመትከል ይቸገራል። ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል የሆነ እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ነው።
በጣም የሚያሳዝነው ጉዳይ ብልፅግና ለኢትዮጵያ ፍቱን መድኃኒት መደመር ነው ብሎ ሃሳብ ይዞ ሲመጣ ላለፉት ስድስት ዓመታት አሁንም ከሳሽ እንጂ አማራጭ ሃሳብ ይዞ የመጣ ግለሰብ፤ ቡድን፤ ፖርቲ አላየንም።
ነገር ግን በታቀዱ እሳቤዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት የገጠሙን ችግሮች ስለምናውቅ የኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳብ ሀገር በቀል ሀሳብ ቢያቀርቡ ብልፅግና ለመማር ዝግጁ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። ምክንያቱም ሃሳብ የለሽ ፖለቲከኞች ሃሳብ የለሽ ፓርቲዎች ለአጭር ጊዜ ድል የረጅም ጊዜ መከራን ያመጡብናል። ለታክቲካል ድል ስትራቴጂክ ሽንፈትን ያስከትሉብናል። ሃሳብ የነጠፈበት አካባቢ ማፍረስ ቢቀልም መልሶ መገንባት ግን ፈተና ይሆናል።
አንድ ፓርቲ ሃሳብ ከነደፈ በኋላ ሃሳቡን የሚያንሸራሽርበት ጉባኤ ያስፈልገዋል። ብልፅግና ለሁለተኛ ጊዜ ይህንን ጉባኤ የሚያዘጋጅበት ዋና ምክንያት በዚህ ጉባኤ እስከ ባለፈው ቀን ድረስ የመጣንበት ጉዞ አብቅቶ አዲስ የምንጀምረውን ጉዞ ሊያስኬድ የሚችል ሃሳብ፤ ያንን ሃሳብ ደግሞ በእውቀት ተገንዝቦ ሊመራ የሚችል አመራር እንዲሁም አመራሩንና ሃሳቡን አሰናስሎ ውጤት የሚያመጣ አሠራርና ደንቦች በጉባኤ መፅደቅ ስላለበት ነው።
አሁን ተወያይተን፤ ተመካክረን የምናፈልቀው ሀሳብ ለሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ የምትጓዝበትን መንገድ የሚቀይስ ስለሆነ በዚህ ጉባኤ ሃሳብ ማፍለቅ፤ ሃሳቡን ሊመሩ የሚችሉ አመራሮች መምረጥ፣ አሠራር መንደፍ ብቻውን በቂ አይደለም። ከዚህ ጉባኤ የሚጠበቀው አንድ ቁልፍ ነገር በጉባኤው ሂደትም፤ በውጤትም ዲሞክራሲያዊ አሳታፊ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል።
ሁላችሁም እንደምታውቁት በልበ ሙሉነት መናገር የምችለው በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባኤ የብልፅግና ጉባኤ ብቻ ነው።
ይህ አካታችነት፤ አሳታፊነት ዲሞክራሲያዊ በሆኑ የሃሳብ መንሸራሸሮች ዳብሮ፤ ብቃት ያላቸው አመራሮች ከሁሉም የኢትዮጵያ ጫፍ እንዲመረጡ አድርጎ፤ አሠራር ቀይሶ፤ በተለመደው መንገድ ተደምሮ አንድ ሆኖ የወጣ እንደሆነ የሚቀጥለው የኢትዮጵያ ምዕራፍ ስኬታማ እንደሚሆን ከባለፈው ታሪካችን መማር፣ መገንዘብ፣ ማስተዋል አንቸገርም።
ለዚህም ነው ሁለተኛው የፓርቲያችን ጉባዔ ‹‹ከቃል እስከ ባሕል›› ያለው። ምን ማለት ነው ከቃል እስከ ባሕል ስንል ያላችሁ እንደሆነ ሃሳብ በቃል ይነገራል። በመጽሐፍ በሰነድ ይሰነዳል። በተግባር ይገለጣል። ነገር ግን ይህ ሃሳብ በድግግሞሽ ውስጥ፤ በልምምድ ውስጥ ባሕል ይሆናል።
ባሕል ምን ማለት ነው ልማድ፤ እሴት፤ ትዕምርት፤ ያለማንም ጎትጓች፤ ካለማንም ቀስቃሽ በራስ ፈቃድ የሚከወን ነገር ባሕል ይባላል። ባለፉት ዓመታት ፅዱ ኢትዮጵያን መፍጠር አለብን። በየመንገዱ ቆሻሻ መጣል፤ መፀዳዳት የለብንም ብለን በጋራ ሥራ መጀመራችን ይታወቃል።
ይህ ነገር ግን ባሕል ሆኖ እያንዳንዱ ሰው ሶፍት መጣል፤ ቆሻሻ መጣል፤ መኪና እየነዳ ከመኪና ውስጥ ላስቲክ መጣል እስኪጠየፍ ድረስ ዘመቻ እንጂ ባሕል አይደለም። ከዘመቻ ወጥቶ የዕለት ተዕለት ካለመካሪ ካለቆስቋሽ ልምምድና ክንውን እንዲሆን ባሕል መፍጠር ያስፈልጋል።
በዘመቻ መልክ በጓሮ ምግብ ማምረት፤ ግርግዳዎቻችን ላይ ምግብ ማምረት ሥራ ጀምረናል። ዘመቻ የአንድ ወቅት ነው። ባሕል ግን በተደጋጋሚ የሚከወን ተግባር ስለሆነ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባሕል መሆን ይጠበቅበታል። ተፈጥሮን አለማወክ፤ ውሃ አለማቆሸሽ፤ ዛፍ አለመቁረጥ፤ ተራራ አለማራቆት በዘመቻ የጀመርናቸው ሥራዎች ልምምድ ሆነው ባሕል መሆ ን መቻል አለባቸው።
ከሁሉ በላይ በፍጥነት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ እየመጣ ያለው አዲሱ ልምምድ ባሕል መሆን አለበት። ብልፅግና ባሕል ማድረግ አለብን ባሕል መፍጠር አለብን ሲል ምን ማለት ነው፤ አንደኛ ብልፅግና ባሕል መሆን አለባቸው ከሚላቸው አምስት አንኳር ጉዳዮች አንደኛው ማወቅ ነው።
ሀገርን በቅጡ ማወቅ ሕዝቡን ባሕሉን፣ ቋንቋውን፣ ሥነምግባሩን በወግ በትክክል ማወቅ፣ የኢትዮጵያን ፀጋ ማወቅ፣ የኢትዮጵያን ተፈጥሮ ማወቅ፣ ብዙዎቻችን ከተወለድንበት መንደር ያለፈ ዕውቀት ሳንይዝ ነው ኢትዮጵያ የምንለው። ኢትዮጵያን በቅጡ ስናውቅ ተዝቆ የማያልቅ ሃብት ያላት የምታጓጓ፤ እንኳን ልንጋደልባት ሠርተን የማንጠግብባት ሀገር መሆኗን መገንዘብ እንድንችል ሀገራችንን ሕዝባችንን ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ብዙዎች የኢትዮጵያን ክፍሎች ካለማወቅ ካለመገንዘብ በቀላሉ ኢትዮጵያን እንዳሻቸው ማድረግ የሚችሉ ይመስላቸዋል። ያ ኢትዮጵያ ዛሬ የለም ዛሬ ያለው ኢትዮጵያ በእኩልነት በዲሞክራሲ በመከባበር በወንድማማችነት ስሜት ብቻ ለጋራ ሕልምና ራዕይ የምንሠራበት እንጂ አንዱ ሌላውን ተጭኖ አንዱ ከሌላው ዘርፎ የሚሄድበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከእንግዲህ መከወን የሚቻል ተግባር ስላልሆነ ኢትዮጵያን በቅጡ ማወቅ የመጀመሪያው ተግባር ይሆናል።
ሁለተኛው ማላቅ ማሻሻል ነው። ያለንን የተሰጠንን ፀጋ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማላቅ ጣና ነበረ ጎርጎራን መጨመር ፋሲል ነበረ አሸብርቆ አምሮ እንዲታይ ማድረግ አባጅፋር ነበር የበለጠ እንዲታይ ማድረግ ሃላላ ኬላ ነበረ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ የሚባል ስፍራ ለማየት ለማወቅ እንዲጓጉ አልቆ መሥራት ያስፈልጋል። ማላቅ ካልቻልን ያለንን ማወቅ ብቻውን አያሻግረንም።
ሦስተኛው መፍጠር ነው፤ መፍጠር በተለየ መንገድ ማየት ነው። በተለምዶ ከምናየው መንገድ ባሻገር በአዲስ መልክ በአዲስ መነጽር መመልከት መቻል ነው። ማየት ብቻ ሳይሆን በጭንቅላት ጨርሶ መጀመር ነው። በጭንቅላት ያልጨረስነውን ጉዳይ ብንጀምር እንደተለመደው የሚጓተት የማያልቅ ሥራ ስለሚሆን ጨርሰን መጀመር የመፍጠር አካል ነው።
በመፍጠር ውስጥ ሊሰመርበት የሚገባው ሌላው አንኳር ጉዳይ ለወል ጥቅም ለጋራ ራዕይ ለብሔራዊ ጥቅም መጀገን ነው። ለግል ጥቅም ለሌብነት አይደለም። ለኢትዮጵያ ጥቅም ሪስክ መውሰድ መጀገን ያስፈልጋል። በተለመደው መንገድ ከሄድን መፍጠር የሚባለው ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ሊከወን ስለማይችል ለጋራ ጥቅም መጀገን የመፍጠር አካል ሆኖ መወሰድ ይኖርበታል።
አራተኛው መፍጠን ነው፤ ጊዜ የለንም። ብልፅግና እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ አንድ ዓመት ብቻ ነው ያለው፤ መተኛት አንችልም። የተሰጠን ኮንትራት አምስት ዓመት ነው፤ በአምስት ዓመት የበቃ፣ የሚታይ የሚጨበጥ ፍሬ ካለን ሌላ አምስት ዓመት እናገኛለን። ሌላ አምስት ዓመት ለማግኘት ግን ዛሬ ጊዜ የለንም ብለን የምንሮጥ፣ ቀነ ከሌት የምንሠራ፣ ባለን ነገር የምናምን፣ ጀምረን የምንጨርስ፣ ተናግረን የምንፈጽም መሆን አለብን። ጊዜ የለኝም በሚል ስሜት ፈጥነን የማንከውን ከሆነ ኢትዮጵያ በተለመደው መንገድ ትጓዝ ይሆናል። በልፅጋ ለዓለምና ለአፍሪካ አርዓያ መሆን ግን አትችልም።
አምስተኛው ማስተሳሰር ነው። ሕዝብን ሃሳብን ውጤትን በተለያየ ዶት ማስተሳሰር ያስፈልጋል። ክቡራትና ክቡራን አዲስ አበባ ላይ የጀመርናቸውን ለውጦች ከዚህ ቀደም ለበርካታ ወንድምና እህቶቻችን ገለጻ ማድረግ፣ ማስረዳት ይኖርብናል። ምክንቱም ዶት ብቻ ነበረ አሁን ንግግር አያስፈልግም። ከአንድ ጫፍ ሌላ ጫፍ የሚሄድ ሰው ለውጡን ያየዋል ይዳስሰዋል። ኢትዮጵያውያን እንኳን ማድነቅ ገና መለማመድ ያለብን ባሕል ቢሆንም ከእህት ፓርቲዎች መካከል ዛሬ አንድ ለዚህ ጉባኤ የመጡ ወንድም አግኝቼ ነበር።
‹‹የዛሬ አራት ዓመት አዲስ አበባ መጥቼ ነበር አሉ አዲስ አበባን ለማወቅ በማያስችል ደረጃ ተለውጣለች። ግን መለወጧ ሳይሆን የገረመኝ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከተማ እንዲህ ለመሥራት ይቻላል ወይ የሚለው ጉዳይ እኔም ጓደኞቼም እየተነጋገርንበት ነው›› አሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጓዝንበት የመጀመሪያው የብልፅግና ጉዞ ምዕራፍ አንድ የመነሳት ዘመን ነበር። ከጥልቅ እንቅልፍ ከብዙ ዕዳ መንቃት መነሳት የጀመርንበት ዓመት/ምዕራፍ ነበር። በዚህ ምዕራፍ የታሰረ ይፈታ፣ የተሰደደ ይመለስ፣ ያኮረፈ ይታረቅ፣ የተባረረ ከመከላከያም ከዩኒቨርሲቲም ይመለስ፣ የተከፋፈለ፤ በኦርቶዶክሱም በሙስሊሙም ይደመር፣ አቧራ ይራገፍ፣ ፀጋ ይገለጥ፣ ቶርቸር በኢትዮጵያ ይቁም ብለን ላለፉት ስድስት ዓመታት ብታምኑም ባታምኑም አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ቶርች አይደረግም ፣በዚህ እኛ እንኮራለን።
ይሄ የመነሳት ዘመን ልክ አውሮፕላን ስትሳፈሩ ያለው ዓይነት ስሜት ነው። ልክ ስትቀመጡ አብራሪው ”ቀበቷችሁን አጥብቁ ልንነሳ ነው ይላችኋል” ብዙ ማስጠንቀቂያ፣ ገለጻ፣ ማስተማሮች አሉ። ከዚያ ስንነሳ መሬት ላይ ስለሆን መንገጫገጮች አሉ ድምፆች ይሰማሉ። ከፍታውን ከያዘ በኋላ ቀበቷችሁን ዘና በሉ ይባላል ።
የመጀመሪያው የመነሳት ምዕራፍ አብቅቶ አሁን በዚህ ጉባኤ የሚፀድቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የማንሰራራት ዘመን ነው። የማንሰራራት ዘመን፣ የቁልቁለት ጉዞ፣ የጎንዮሽ ጉዞ የሚያበቃበት ማለት ነው። በአንደኛው ጉባኤያችን በቂ ስንዴ ማምረት ይኖርብናል። ከውጭ ስንዴ ማምረትን ማቆም አለብን፤ ኤክስፖርት ማድረግ አለብን፣ ህዳሴን መጨረስ አለብን፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚክ ሪፎርም መጀመር አለብን ብለን ነበር።
ከዚህ ጉባኤ በኋላ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እነዚህ የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች የምናስመርቅበት፤ ሪቫን የምንቆርጥበት፤ ዐሻራ የምናስቀምጥበት፤ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለማስቆም ከግራ ከቀኝ፤ ከውስጥ ከውጭ ጥረት ቢደረግም ጨክነን ጨርሰን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሥራት የምንነግርበት ዘመን ከፊታችን ባሉት ወራቶች የሚገለጥ ይሆናል።
ግሪኮች አንድ አባባል አላቸው ‘አንድ ሰው አንድን ወንዝ ከአንድ ጊዜ በላይ ሊሻገረው አይችልም’ይላሉ ። ምክንያቱም ወራጅ ወንዝ አንዴ ስትሻገሩት ያልፋል። ስለማይቆም ያንን ወንዝ፤ ያንን ውሃ ደግሞ መሻገር አይቻልም ይላሉ ።
የብልፅግና የማንሰራራት ዘመን አንዱ ዋነኛ አሳሪ ቃል እና የተግባር ምንጫችን የሚሆነው በዚህ ዓመት ያየነውን የኮሪደር ልማት በሚቀጥለው ዓመት ስትመጡ አታዩትም። በዚህ ዓመት ያያችሁት ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት አታዩትም። ጨርሰን አስውበን አሳምረን በአዲስ መልክ ታዩታላችሁ እንጂ የዘንድሮውን በሚቀጥለው ዓመት አንደግመውም። ያን ውሃ ተሻግሯል።
ከተሞቻችን፣ ፕሮጀክቶች፣ ሰርቪስ፣ ተቋማት አሁን ካላቸው ቁመና ውበት ብቃት ውጤት በላይ ልቀው በሚቀጥለው ዓመት ይታያሉ። ይህንን ለማድረግ ጉባኤው በቂ ሃሳብ ማፍለቅ፣ የተሻለ አመራር መምረጥ፣ አሠራር መቀየስ፣ የሥራ ባሕልን ማዳበር፤ ለነዚህ ወሳኝ ሃሳቦች የጋራ ውሳኔ ማሳለፍ ይጠበቅበታል። እንደሚያደርግም ከፍተኛ እምነት አለኝ።
ብልፅግና ትልቅ ተቋም ነው። በአፍሪካ 15 ነጥብ 07 ሚሊዮን አባል ያለው ፓርቲ የለም። በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፓርቲዎች በሕንድና በቻይና ይገኛሉ። በሕንድና በቻይና ያሉ ፓርቲዎችም ቢሆኑም ቁጥራቸው 100 ሚሊዮን አካባቢ የሚደርስ ቢሆንም ካላቸው የሕዝብ ቁጥር አንጻር እኛ ካለን የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ ብልፅግና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፓርቲ ነው።
ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፓርቲ በወጣት የተሞላ ነው፤ ለኢትዮጵያ የብልፅግና መሠረት እንዲጥል እኛ መስዋዕት ሆነን፣ እንደሻማ ቀልጠን ልጆቻችን ችግር፣ መከራ እና ዕዳን እንዳይወርሱ ካላደረግን በቀር ቁጥሩ ብቻውን ትልቅነትን አይናገርም። ትልቅነታችንን በሥራና በውጤት የሚታይ ስለሆነ፤ ይህ ትልቅ ተቋም፣ ትልቅ ሃሳብ ያለው ተቋም፤ ጅማሮው ውጤት ማሳየት የጀመረው ተቋም፣ ለልጆቻችን ምንዳን፣ ለልጆቻችን ብልፅግናን፣ ለልጆቻችን መስጠትን ማስለመድ መሠረት መጣል ይጠበቅበታል። መለመን የበቃው፣ መስጠት የጀመረ፤ መቆሸሽ የበቃው፣ ለፅዳት ምልክት የሆነ፤ መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ የተለማመደ ለብልፅግና አስተማማኝ መሠረት የጣለ ፓርቲ መሆን ይኖርብናል።
ያንን ካደረግን የብልፅግና ፓርቲ አባላት አሁን ያለውን የፖለቲካ ጩኸት እንዳትመለከቱ፤ ከፊታችን አስደማሚ ዘመን ነው ያለው። እያደጉ ያሉ ልጆች ብልፅግና ምን አይነት መሠረት እየጣለ እንዳለ ያውቃሉ። የኛ ዕጣ ፋንታ፤ የኛ ውጤት የሚወሰነው በልጆቻችን ነው። አባቶቻችን ፖለቲካን በቅጡ አልተለማመዱም ።
ግጭት በቃን፤ በ60ዎቹ የታጠቃችሁትን ክላሽ አውርዱ፤ በሰላማዊ መንገድ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በጋራ እንሥራ፤ ብልፅግና ስለሰላም በድርድር በውይይት እና በሃሳብ ለሚደረግ ትግል ግማሽ መንገድ የምንሄድ መሆኑን ባለፈው አሳይቷል። አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል። በኛ በኩል ሰላም፣ ልማት እና አንድነት ዋናው አጀንዳችን ነው።
ክብራንና ክቡራት ብልፅግና በመጀመሪያው የመነሳት ምዕራፍ በገፍ ስላስገባ፤ በገፍ ስለፈታ፤ በገፍ ስላቀፈ ብዙ ፈተና ገጥመውት ነበር። ይሄ ግን ነበር ነው። አሁን ፈተናዎችን ጨፍልቆ ለማለፍ የሚያስችል ብቃት ፈጥሯል።
ከፊታችን ምንም ዓይነት ፈተና የለም ልላችሁ አልችልም። ከቀኝ፣ ከግራዎች በርካታ ፈተናዎች ይደቀኑብናል እንደትላንት ነው ጨክነን አሸንፈን ለኢትዮጵያ መሠረት እንጥላለን። የጀመርነውን እንጨርሳለን የኢትዮጵያን አንድነት የኢትዮጵያን ልማት እናረጋግጣለን።
ከዚህ ውጭ ያሉ ሃሳቦች በሰላማዊ መንገድ እንዲከውኑ ብልፅግና በሰላማዊ መንገድ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል። የኛ ተገን፤ የኛ ጋሻ፣ የኛ መከታ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ሰፊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በመያዝ ለልጆቻችን ምንዳን፤ ለልጆቻችን የብልፅግና መሠረት እና የሰላም ተምሳሌት የሆነች፣ የአበበች ኢትዮጵያን ለመተው ተግተን እንሠራለን።
በመጨረሻ ሁለተኛው የፓርቲያችን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲዘጋጅ ልዩ ልዩ ሚና የነበራችሁ ግለሰቦች እና አመራሮች ለነበራችሁ ሚና ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብኩ በተለይ ቅድም በአርት መልክ የቀረበው፣ የብልፅግናን የውይይት ሰነድ በቴአትር መልክ የገለጸ ስለሆነ እነዛን ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ ማመስገን እፈልጋለሁ።
ውይይታችን ሰላማዊ፤ ብልፅግናን የሚሻ፣ የሚሰባሰብ፤ የሚደመር፤ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚወስድ፤ በጋራ በተባበረ ድምፅ ለሚቀጥለው ምዕራፍ የምንነሳበት እንደሚሆን ያለኝን ሙሉ እምነት እየገለጽኩ፣ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት በልፅጋ፣ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር። አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም