
ሼህ እንድሪስ …
ሕይወት፣ ኑሯቸው በደቡብ ወሎ፣ ሀርቡ ቃሉ ወረዳ ነው:: ዕድገትውልደታቸው ከአካባቢው ቀዬ አይርቅም:: ትዳር ይዘው፣ ጎጆ ቀልሰው ልጆች ያፈሩት ከዚሁ ሥፍራ ነው:: ዛሬም ድረስ ትውልድ መንደራቸውን ቢለቁ፣ ርቀው ቢሄዱ አይወዱም:: ሁሌም ሰፈር፣ ቀዬአቸውን በፍቅር፣ በትዝታ ያስቡታል::
‹‹ቃሉ››ማለት ለእሳቸው መኖሪያ ብቻ አይደለም:: በትዳራቸው በረከት ያገኙበት፣ ወልደው ስመው፣ ዘርተው የቃሙበት ድንቅ ስፍራ እንጂ:: ሼህ እንድሪስ መሀመድ በአካባቢው ሥመ-መልካም ናቸው:: አገሬው በግብራቸው ለይቶ ያውቃቸዋል:: በእጃቸው ያለ ሙያ፣ በዓይምሯቸው ያደረ ዕውቀት ከብዙዎች እያገናኘ ከበርካቶች ሲያውላቸው ቆይቷል::
ሼህ እንድሪስ ቋሚ ይሉት ሥራ የላቸውም:: ሙያቸውን የሚሹ ብዙዎች በጠሯቸው ግዜ ግን ካሉበት ፈጥነው ይገኛሉ:: በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ‹‹ኒካ›› ሲፈጸም በክብር ተገኝተው ሥርዓተ- ጋብቻውን የሚመሩት እሳቸው ናቸው:: በድንገት ሰው ሞተ ከተባለም ከሀዘኑ ቤት ደርሰው ሟችን አጥበው፣ ለመከፈን፣ ለመገነዝ የሚቀድማቸው የለም::
ሼህ እንድሪስ ከዚህ አለፍ ሲል በአገር በመንደሩ የፈጣሪ ቃል የሆነውን ቁርዓን በማስቀራትና ሀይማኖታዊ ዕውቀትን በማስጨበጥ ታዋቂ ናቸው:: ሁሌም በተፈለጉበት ሥፍራ ለብዙሀን በተጠሪነት ያገለግላሉ:: ሼሁ ለመንደራቸው፣ መንደር ቀዬውም ለእሳቸው፤ የመኖር እስትንፋስ ሆኖ ጊዚያትን ተሻግሯል::
ሼህ እንድሪስ በትዳር ዓመታትን ዘልቀዋል:: በጋብቻ አብረዋቸው ከቆዩ ባለቤታቸው ጋር ያለቸው ቅርበት በፍቅርና መከባበር ነው:: ወደውና ፈቅደው በሚመሩት ጋብቻ ቤታቸው ሰላማዊ እንደሆነ ተራምዷል:: አባወራው ሁሌም እጃቸው እንዳያጣ፣ እንዳይነጣ፣ ጎጇቸው እንዳይነጥፍ፣ እንዳይጎድል፣ ሲተጉ፣ ሲሮጡ ይውላሉ::
እሳቸው አራት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት በወግና ሥርዓት ነው:: ሁሉም እንደልፋት ድካማቸው አድገው፣ ተምረው ካሰቡት እንዲደርሱ የአባትነት ድርሻቸውን ይወጣሉ:: የቤተሰቡ ተስፋ የአባወራው የዕለት ሩጫ ነው:: የቀን ዕድል በሚያመጣው ሲሳይ፣ ልጆች ያድጋሉ፣ የጓዳው ጎዶሎ ሞልቶም ሌላ ቀን መሽቶ ይነጋል::
ትንሹ መሐመድ…
ከቤቱ የመጨረሻ የሆነው ትንሹ መሐመድ መልከመልካም ይሉት ሕጻን ነው:: ድንቡሽቡሽ ሰውነቱ፣ ከሳቂታ ገጽታው ተዳምሮ ለቤተሰቡ ልዩ ደስታን ፈጥሯል:: የዓይን ማረፊያ ነውና ሁሉም መሐመድን በፍቅር ተንከባክቦ፣ ተቀባብሎ እያሳደገው ነው:: ሕጻኑ የቤቱ ናፍቆትና ጌጥ፣ የሁሉም ሥጦታና ስስት ሆኗል::
ቤተሰቡን በአቻ ስሜት በፍቅር ያሰረው መሐመድ የልጅነት አንደበቱ፣ የሕጻንነት ወዘናው፣ ይለያል:: የአንገቱ ስር ሽታ፣ የሳቅ ፈገግታ ለዛው ይናፍቃል:: ሁሉም ወጥቶ በገባ ቁጥር የዓይኑ ማረፊያ የድካሙ ማስረሻ አድርጎታል:: በየቀኑ ትምቡክ ጉንጮቹ፣ ለስላሳ እጆቹ በስስት ይሳማሉ:: ማንም ለእሱ ያሻውን፣ የጣፈጠውን ለመስጠት የእጁን ገንዘብ የኪሱን ሚስጥር አይሰስትም:: የሁለት ዓመቱ ሕጻን ትምህርት ጀምሮ ውሎ እስኪገባ፣ ከእናቱ ጉያ አይጠፋም:: ቀሚሷን ይዞ ሲከተላት ይውላል::
ያልታሰበው…
ከቀናት በአንዱ መላው ቤተሰብ ስለ ትንሹ መሐመድ ጭንቅ ገባው:: ከግዚያት በኋላ በጤናው ላይ የሚስተዋለው ችግር አሳሳቢ እየሆነ ነው:: የትናንቱ፣ ቀልጣፋ ልጅ ዛሬ ድካም አሸንፎታል፣ ሳቁ ተፋዞ ዝምታ አብዝቷል:: ውብ ገጽታው እንደ ቀድሞ አይደለም:: የመሐመድ ደርሶ መለዋወጥ የቤተሰቡ ጭንቀት ሆኗል::
ሼህ እንድሪስ ለአገር ለመንደሩ መፍትሄ ናቸው:: ሁሌም ስለሌሎች ፈጥነው የሚደርሱ ከተፎ:: ለልጃቸው መፍትሄም ቢሆን አልዘገዩም:: እስካሁን ትንሹን መሐመድ የነካባቸውን ለማወቅ ሲያስቡ ሲጨነቁ ከርመዋል:: አንድ ማለዳ አባወራው የልጃቸውን እጅ ይዘው ወደ ኮምቦልቻ አቀኑ:: በዚህ ከተማ ከአካባቢያቸው የተሻለ ሕክምና ስለመኖሩ ያውቃሉ::
መሐመድ ከሀኪም ዘንድ ቀርቦ ምርመራውን አካሄደ:: ውጤቱን ለማወቅ ጥቂት መጠበቅ ነበረባቸው:: የኮምቦልቻው ሀኪም ለአባት እንድሪስ ስለልጀቸው የምርመራ ውጤት አሳወቀ:: ትንሹ መሐመድ የ‹‹ሳምባ ምች›› ይሉት ሕመም አግኝቶታል:: ልጁ በወጉ ታክሞ ይድን ዘንድ መድሀኒቱን በአግባቡ መውሰድ ጤናውን መከታተል ግድ ይለዋል ::
አባቱ የተባለውን ሰምተው፣ መድሀኒት መርፌውን ገዝተዋል:: ትንሹ መሐመድ በልጅነት አካሉ መርፌ እየተወጋ:: መድሀኒት ሽሮፑን እየጠጣ ነው:: ያዝ ለቀቅ የሚያደርገው ሕመም በዋዛ ትቶት አልሄደም:: ሲጥል ሲያነሳው ዓመታትን ቆጥሯል::
መላው ቤተሰብ የትንሹን ልጅ መዳን በጉጉት እየጠበቀ ነው:: የትናንቱ ሳቂታ ልጅ በሕመም ተሸንፎ ከአልጋ መዋሉ ጉዳቱ ለሁሉም ሆኗል:: መሐመድ እንደትናንቱ እንዲስቅ፣ ሮጦ እንዲቦርቅ የማይፈልግ የለም:: ጠዋት ማታ ስለጤናው የሚጨነቁ ሁሉ መድሀኒት ስለመውሰዱ፣ መርፌ ስለመወጋቱ ይከታተሉ ይዘዋል::
የትንሹ ልጅ ጤና እንደታሰበው አልሆነም:: የወሰዳቸው መድሀኒቶች የተወጋቸው መርፌዎች ለውጥ አላመጡም:: እያደር ሕመሙ ቢብስ ቢያገረሽ ቤተሰቡ ጭንቅ ገባው:: ሼህ እንድሪስ አሁንም ስለ ልጃቸው ጤና ዝም አላሉም:: የዕለት ገቢቸው የኪሳቸው አቅም ፣ በቂ ባይሆንም ስለ መሐመድ ሲሉ የግል ሀኪምን ሊያናግሩ ወሰኑ::
እንደገና…
ትንሹ መሐመድ ለሁለተኛው ሕክምና ከግል ሀኪም ፊት ቀረበ:: የደሴው ሀኪም ዳግም የጤናውን አቋም አንድ በአንድ መረመረ:: አባት የልጃቸውን መዳን እያሰቡ መልካም ነገር ለመስማት ጠበቁ:: ጥቂት ቆይቶ ግን የእካሁኑን ሕክምና የሚቃረን አዲስ ውጤት ከእጃቸው ደረሰ:: ሀኪሙ የመሐመድ በሽታ የሳምባ ሕመም /ቲቢ/ መሆኑን አሳወቀ ::
ውጤቱን ተከትሎ ለሕመሙ ይበጃሉ የሚባሉ መድሀኒቶች ታዘዙ:: ለታመመ ልጅ መድሀኒት ካልወሰድክ ብሎ ማስገደዱ ከባድ ነው:: መሐመድ የውስጡ ጤና ማጣት ደስታውን ነጥቆት ከርሟል:: አስቀድሞ የወሰዳቸው መርፌና መድሀኒቶች ሰልችተውታል::
እንዲያም ሆኖ በልጅ አቅሙ የተሰጠውን መድሀኒት ለመውሰድ እየታገለ ነው:: ለሳምባው መዳን የጓጉት አባት ጠዋት ማታ ዓይን አይኑን እያዩ የታዘዘለትን ይሰጡታል:: ትንሹ ልጅ ግዴታ የሆነበትን መድሀኒት ሳያሰልስ ይወስዳል::
መሐመድ አሁንም እየተሻለው አይደለም:: ደጋግሞ ሀኪም ፊት መቅረቡ፣ መድሀኒት መውሰዱ ብቻ መፍትሔ አላመጣም:: መላው ቤተሰብ ተጨንቋል:: ወዳጅ ዘመድ በጤና ማጣቱ ግራ ተጋብቷል:: ከአንድ ወር በላይ የወሰደው የሳምባ መድሀኒት አልተቋረጠም:: ከቀናት በአንዱ ደግሞ በትንሹ ልጅ ቀኝ አንገት ላይ ዕብጠት መሳይ ምልክት ተስተዋለ:: ዕብጠቱን በበጎ ያላዩት አባት አንድሪስ ጊዜ አልፈጁም:: ውለው ሳያድሩ መሐመድን ከግል ሀኪሙ ፊት አቅርበው መፍትሄውን ተማጸኑ::
አሁን የግል ሀኪሙ ያየውን እውነት በእሱ አቅም የሚወጣው አይመስልም:: በራሱ ሕከምና ከመቀጠል ይልቅ ወደ ተሻለ ሆስፒታል መላኩን አምኖበታል:: አባትና ልጅ በአስቸኳይ የተጻፈላቸውን ማዘዣ ይዘው ከተባለው ስፍራ አቀኑ:: ተራቸው ደርሶ ከሀኪም ፊት ቀረቡ::
ትንሹ መሐመድ በሆስፒታሉ እንደ አዲስ ለተጀመረው ምርመራ እጁን ሰጠ:: የውስጡ ድካም ቀላል አልሆነም:: ሁኔታው የልጅ አቅሙን ፈተነው:: ፈገግታ ሳቁን አከሰመው:: አሁንም ምርመራው የሚያመጣውን ውጤት መጠበቅ ግድ ሆኗል:: ለቀጣይ ሕክምናው፣ ለመድሀኒቱ ምርጫ ውጤቱ መታወቅ አለበት::
ከምርመራው በኋላ …
አሁን ምርመራው ተጠናቋል:: አባት የልጃቸውን የጤና ምርመራ ለማወቅ ዳግም ከሀኪም ፊት ቆመዋል:: እንደወትሮው እያሰቡ እየጨነቃቸው ነው:: ለዓመታት የመሐመድ ጤና አለመመለስ፣ ለሁሉም ትርጉሙ ብዙ ነው:: ቤተሰቡ እፎይታ አላገኘም:: አባወራው ከእንጀራቸው ውለው አልገቡም::
አባት ከሀኪሙ አንደበት ለእሳቸው ጆሮ የደረሰውን አዲስ ውጤት አምኖ መቀበል ተስኗቸዋል:: ገና ‹‹ካንሰር›› ይሉትን ቃል ሲሰሙ ቀኑ እንደጨለማ ጠቁሮ ታያቸው:: አንደበታቸው ተዘግቶ መናገር መተንፈስ ተሳናቸው:: አዲሱ የምርመራ ውጤት ሕፃኑ መሀመድ ካንሰር እንዳለበት ያሳያል:: እስከዛሬ ሳምባ ምችና ቲቢ ተብሎ መድሀኒት ሲወሰድ ነበር::
ለአባት እንድሪስ ይህን እውነት አምኖ መቀበል ቀላል አልሆነም:: እሳቸውን ጨምሮ መላው ቤተሰብ ክው ያለበት ውጤት ሕመሙን የጋራ አድርጎታል:: ሀኪሞቹ ሼህ እንድሪስን እንደምንም አረጋግተው መሆን ያለበትን እየነገሯቸው ነው:: መሐመድ መታከምና መዳን አለበት:: ሕክምናው አዲስ አበባ እንጂ በቅርብ አይሰጥም::
አሁን መላው ቤተሰብ ስለ ትንሹ ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጥብቅ ምክር ይዟል:: እሱን አዲስ አበባ ይዞ ለመሄድ ከእናት ይልቅ አባት እንዲወጡት ተወስኗል:: ቤተሰቡ እንዲህ ይበል እንጂ ከማንም እጅ ወዴትም አርቆ የሚወስድ የገንዘብ አቅም አልነበረም::
ባለፉት የሕክምና ግዚያት የወጣው ገንዘብ ጥቂት አይደለም:: ሼሁ በወጉ ያልሰሩባቸው፣ ገቢ ያላገኙባቸው የውጣውረድ ግዚያት አሁን ዋጋ ማስከፈል ይዘዋል:: ገንዘብ አለመኖሩ ሌላ ሕመም ሆኖ ቤተሰቡን እያሳሰበ ነው:: አሁን የትንሹ ልጅ ጉዳይ ከምንም በላይ ነው:: ከታሰበው ደርሶ መታከም፣ መዳን አለበት::
አዲስአበባ…
ሼህ እንድሪስ ጓዛቸውን ሸክፈዋል:: መሐመድን አዲስ አበባ አድርሰው ሊያሳክሙ ነው:: ከወዳጅ ዘመዱ የተዋጣው ገንዘብ ከእጃቸው ገብቷል:: ቀዬ መንደሩ ቸር ተመኝቶ፣ ‹‹ዱአ›› አድርጎ ሸኝቷቸዋል:: እሳቸውና መሐመድ ከተከተላቸው አንድ የቅርብ ሰው ጋር አዲስ አበባ ሲገቡ የተቀበላቸው ወዳጅ ዘመድ አልነበረም:: መርካቶ ከአንድ ተራ ሆቴል አልጋ ይዘው ሊያርፉ ግድ ሆነ::
ማግስቱን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የደረሱት እነ መሐመድ ጊዜ ሳይረፍድ ወደ ሕክምናው አመሩ:: በቂ መረጃ የተጻፈለት ሕጻን ከሀኪሞች ደርሶ ምርመራውን ሲጀምር አልዘገየም:: በምልልስ ሕክምና ቀናት የገፋው ሕጻን ከየዕለት ሕመሙ ጋር ችግሩን መወጣት ያዘ::
አዲስ አበባ ላይ የሦሥት ሰው ወጪ ቀላል አልሆነም:: በየቀኑ ለአልጋና ምግብ፣ ለመድሀኒትና ትራንስፖርት የሚከፍሉት ገንዘብ አቅማቸውን አንገዳግዶታል:: ከሆስፒታሉ ቋሚ ክፍል አግኝተው እስኪገቡ በብዙ ችግሮች ተፈተኑ:: ሼህ እንድሪስ ይህን ግዜ ፈጽሞ አይረሱትም::
እሳቸው በአቅም ማጣትና ሕይወት ማትርፍ መሀል ብዙ አይረሴ ቀናትን አልፈዋል:: መሀመድ ኬሞ ሲጀምር ስቃዩ የዋዛ አልነበረም:: ለሌሎች ሕክምናዎች በኃላፊነት እንዲፈርሙ ሲጠየቁም ልጃቸው እንደሚሞት ገምተው ተሳቀዋል:: አዝነው፣ አምርረው የደም ዕንባ አልቅሰዋል::
ልጄን አትርፉልኝ …
አባወራው ሀኪሞቹን ባገኙ ቁጥር ስለልጃቸው መዳን አብዝተው ይወተውታሉ:: ብዙ የለፉበት መሐመድ ድንገት የሚያጡት በመሰላቸው ግዜ ‹‹ልጄን አድኑ! አትርፉልኝ›› ሲሉ መማጸን ልማዳቸው ነው:: ሼህ እንድሪስ ከእጃቸው የተረፈ በቂ ሳንቲም አልነበረም:: ጠዋት ማታ የመሐመድን ትንፋሽ እያዳመጡ ነገን ተስፋ ማድረግ ያዙ:: ከቀናት በኋላ በመሐመድ ጤና ላይ የለውጥ ጭላንጭል ታያቸው::
አባወራው ለችግራቸው የሚሸጡት ሀብት ንብረት የለም:: ከሆስፒታሉ ቢወጡ የሚጠብቃቸው ጎዳና መሆኑ አይጠፋቸውም:: ለዚህ ጎዶሏቸው ሁሌም ፈጣሪን በጸሎት ይጠይቃሉ:: ልጅነቱን በሕመም የገፋው መሐመድ በወጉ ድኖ እንዲመለስ ምኞታቸው ነው:: ነገ የሚሆነውን አያውቁም:: ግና ተስፋቸው አሁንም ከውስጣቸው አልነጠፈም:: ፈጣሪን በጸሎት፣ ይለምናሉ ይማጸናሉ::
የጸሎቱ መልስ…
ከቀናት በአንዱ ሀኪሞቹ ቀረብ ብለው ሼህ እንድሪስን አዋይዋቸው:: ሼሁ ስለኑሮ ሕይወታቸው፣ ስለችግር ገበናቸው አንዳች አልሸሸጉም:: ስለልጃቸው ጤና ሲሉ ቤት ንብረታቸውን የተው፣ አገር ቆርጠው፣ ወንዝ አቋርጠው የመጡ የሰው አገር ሰው መሆናቸውን፣ ተናገሩ:: ይህ እውነት የጠያቂዎቻቸውን ልቦና ለመግዛት ኃይል አገኘ::
ቤት ለእንግዳ…
አባትና ልጅ ማቲዎስ ወንዱ ከተባለ የካንስር ሶሳይቲ ግቢ ለመድረስ አልዘገዩም:: በመልካም ፈገግታ በእንግድነት የተቀበሏቸው ሰዎች ፈጥነው ቤተሰብ አደረጓቸው:: በስፍራው ከተዘጋጀው ንጹህ መኝታ እና ከእራት ገበታው ታደሙ:: ይህ አጋጣሚ ለእነሱ ከተአምር በላይ ነበር:: ከዛች ቀን ጀምሮ የሼህ እንድሪስ ልቦና ‹‹እፎይ!›› አለ::
አሁን በቀጠሮ ሲመጡ ሕክምናውን ለመቀጠል የት እገባለሁ ብለው አያውቁም:: ሰተት ብለው ‹‹ቤቶች›› የሚሉበት ሳሎን፣ ሲደክማቸው የሚያርፉበት መኝታ በእጃቸው ነው:: ደርሶ ለመመለስ፣ የትራንስፖርት ወጪ ቸግሯቸው ሆኖ አያውቅም:: ለመድሀኒትና ምግብ፣ አያስቡም:: ለሆስፒታል ቀጠሮ ወስዶ ሚመልሳቸው መኪና ሁሌም ዝግጁ ነው::
አሁን መሐመድ የስምንት ዓመት ልጅ ሆኗል:: ከአምስት ዓመታት በላይ የተሰቃየበት ሕመሙ በክትትል መፍትሄ ሊያገኝ ከዳር ደርሷል:: ዛሬ እንደትናንቱ አይደለም:: እንደ ልጅ ያማረውን ጠይቆ ይበላል:: ከእኩዮቹ ጋር አባሮሽ፣ ኩኩሉ ይጫወታል:: ደስተኛ ነው::
አባት እንድሪስ መሐመድ ዛሬ የአጸደ ሕጻናት ተማሪ መሆኑ ያኮራቸዋል:: ይህን እውነት አሻግረው የሚያዩት ደግሞ በተለየ ትርጉም ነው:: እሱ ባለፈበት መንገድ ሌሎች በስቃይ እንዲያልፉ አይሹም:: ይህ ይሆን ዘንድ ልጃቸው በሽታውን በትምህርት ታግሎ እንዲበቀለው ምኞታቸው ነው ::
ጠንካራው አባወራ አሁን ለቆሙበት አጋጣሚ ላበቃቸው የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የተለየ ቦታና ከፍ ያለ ክብር ይሰጣሉ:: ከሀያ ዓመታት በፊት በካንሰር ሕይወቱን ያጣው ብላቴና ማቲዎስ ወንዱ በእሱ ሞት የነ መሀመድ ትንሳኤ ታውጇል:: እሱ ቢያልፍም በጎ አሻራው ለሌሎች መኖር ማሕተም ነው:: ሼህ እንድሪስ ዓላማውን ላስቀጠሉ በሙሉ ምስጋናቸውን ከአከብሮት ጋር ያደርሳሉ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም