
“‹ቢስት ባር› የቤንች ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ እና የምስጋና በዓል ነው። የመጀመሪያው እህል የሚቀመሰው በዚሁ ወቅት ነው” ይላሉ የብሔረሰቡ ተወላጅ እና የቤንች ጎሳ መሪ ሻንቆ ጋቲናት:: የጎሳ መሪ የሆኑት ሻንቆ ለታላላቅ የዕድሜ ባለፀጋዎች ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውን የ”ቢስት ባር” በዓልን በተደጋጋሚ የማስጀመር ዕድል ገጥሟቸዋል። እህል ተሰብስቦ ፤ጎተራ ሞልቶ አርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ የልፋቱን ፍሬ በሚበላበት የአዲስ ዓመት መባቻ ወቅት እንደእርሳቸው ያሉ የሀገር ሽማግሌ እና የጎሳ መሪ የግድ መገኘት አለበት። በቤንች ብሔረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል “ቢስት ባር” ላይ።
በአጠቃላይ በብሔረሰቡ ያሉት ሦስት የጎሳ መሪዎች በተገኙበት ነው የሚጀመረው። በእንዲህ ዓይነቱ ብዙ የዘመን መባቻ በዓላት የጎሳ መሪው ሻንቆ በበዓሉ ታዳሚ የብሔረሰቡ ተወላጆች መካከል ይገኛሉ። እንደ ጎሳ መሪነታቸው፤ ታላቅነታቸውና የዕድሜ ባለፀግነታቸው የመጀመሪያውን የብሔረሰቡን እህል የደስታ የተድላ ይሁን በማለት መርቀውና ቆርሰው ለፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ያስጀምራሉ። አምናም ዘንድሮም በዓሉ የቤንች ብሔረሰብ መገኛ በሆነው በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ዣዥ ቀበሌ ሲከበር የጎሳ መሪው ተገኝተው ነበር። ከዚህ ከጎሳ መሪው ሻንቆና እሳቸውን ጨምሮ ከሌሎች የታወቁ ሦስት የጎሳ መሪዎች ምርቃት በኋላ ነው ተወላጁ ሁሉ ከያለበት በመጠራራት በዓሉ ወደ ሚከበርበት ወደ ዚህ ዣዥ የተሰኘው ስፍራ የሚሰበሰበው። ያኔ በርካቶች የሚሳተፉበት በኢትዮጵያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የሆነውን እና በማኅበረሰቡ ዘንድ “ቶህ” ተብሎ የሚታወቀው የትንፋሽ መሳሪያ ጨምሮ የተለያዩ ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ተጠቅመው የሚከናወኑ ወደ 13 ዓይነት ባሕላዊ ሙዚቃ፤ ውዝዋዜና፤ ጭፈራ የጨዋታ ትዕይንቶች ይደራሉ። “ሀገራችንን እና አካባቢያችንን ሰላም ያድርግልን፤ የተመረተው ምርት በረከት ይሙላበት፤የተወለደው ይደግ “የሚለው የአባቶችና የጎሳ መሪዎች ምርቃት ይዥጎደጉዳሉ። በበዓሉ ፈጣሪም ሰውን እርስ በእርሱ አራርቆ ካቆየው አስፈሪው የክረምት ወቅት፤ የጨለማውን ዘመን አስወግዶ ወደ ብርሃን ያሻገረን፤ የተዘራውንም እህል ከብዙ ጥፋት ተጠብቆ፤ታጭዶ ጎተራ እንዲገባ ቢያደርግልን አምላክ ብሔረሰቡ በሰፊው ያመሰግናል።
ለፈጣሪ ከሚቀርበው ምስጋና ተነስተው ጎሳ መሪው ሻንቆ እንደሚናገሩት፤ በዓሉ አንዳንዶች እንደሚሉት ምንም ዓይነት የእምነትም ሆነ የሐይማኖት መሰረት የለውም። ቢስት ባር የቤንች ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ማኅበራዊ የኑሮ ዘይቤውን ጠብቆ ያቆየው ታሪካዊና ባሕላዊ ይዘት ያለው ነው። የእርስ በእርስ፤ የፍቅር፤ የሰላም፤ የመተሳሰብ፤ የአንድነት መገለጫና ለታላላቅ አባቶች ክብር የሚሰጥበት ፈጣሪ የሚመሰገንበት የዘመን መለወጫ በዓል ነው።
“በብሔረሰቡ ባሕል ለታላቅ ልዩ ክብር ይሰጣል።ታላቅ እያለ ታናሽ ፊቱን እንኳን ቀድሞ እንዲታጠብ አይፈቀድም። ማንኛውም ዕድል ቀድሞ በታላላቆች እንዲከናወን ነው የሚደረገው” ሲሉም ለታላላቆች የሚሰጠውን ጉልህ ስፍራ ይገልጻሉ።
የሲዝ ከተማ አስተዳደር ነዋሪና የብሔረሰቡ ተወላጅ ወይዘሮ ወሰነች ኮምቴስ ያጋሩን አስተያየትም ይሄንኑ ያጠናክራሉ። በብሔረሰቡ ባሕል የመጀመሪያው ተዘርቶ እሸት ያሸተ እና ፍሬ የሰጠ እህል በዕድሜ ተዋረድ ነው የሚቀመሰው። የሚቀመሰው ደግሞ የዘመን መለወጫ በሆነው በብሔረሰቡ “ቢስት ባር” በዓል ላይ ነው። ይሄ የብሔረሰቡ የምስጋና እና የአዲስ ዓመት በዓል ሲደርስ ባለቤቱ “እህሌ ደርሷል ኑ እንቃመስ” ብሎ ይጠራና ወደ ቤቱ ይጋብዛል። ቅድመ አያት፤ በሕይወት ከሌለ አያት፤ አያት ከሌለ ደግሞ አባት፤ አባት በሕይወት ከሌለ፤ ሌሎች ተወላጆች ወይም ጎረቤትና በአካባቢው በአንድ ላይ የሚኖሩ ቁጥራቸው እስከ አሥር የሚደርስ ሰዎች ግብዣውን ተቀብለው ይቀምሱታል። ይሄም የብሔረሰቡ ማኅበራዊ መስተጋብር፤ አብሮነትና ፍቅር የሚገለጽበት ሲሆን ብሔረሰቡ ለትልልቅ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ለሌሎች አባቶች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ መሆኑን ለማሳየት የሚደረግ ድንቅ የመከባበርና ባሕል የሚንፀባረቅበት በዓል ነው። ክንውኑ እህትማማችነትና ወንድማማችነትን ማዕከል ያደርጋል።
ቢስት ባር ቤንች ማኅበረሰብ ውስጥ የሚከበር የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ በዓልም ነው። ብሔረሰቡ ዓመቱን እንደ ማስጀመሪያና መሸጋገሪያ አድርጎ ታላቅ ክብር ይሰጠዋል። በልዩ ሁኔታ የሚያከብረው ነው የሚሉት ደግሞ የቤንች ሼኮ ዞን ባሕል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊው አቶ ጌታቸው ኮይካ ናቸው።
ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ ቢስት ባር የሚለው ስያሜ ለበዓሉ ተሰጥቶታል። በብሔረሰቡ ዘንድ የሚከበረውም የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል መሆኑን ታሳቢ አድርጎ ነው። ቢስት በብሔረሰቡ ቤንችኛ ቋንቋ ቃል በቃል ሲተረጎም የበኩር እንደማለት ሲሆን ባር ደግሞ በዓል ማለት ነው። በኩር በራሱ ጥንድ ሀሳቦች ያያዘ ሲሆን አንደኛው በዓሉ የበኩር በዓል መሆኑን የሚያመላክት፤ ሁለተኛው በብሔረሰብ ውስጥ የደረሰው የመጀመሪያው እህል የሚቀመስበት መሆኑን ለመጠቆም ይሰጣል። ሆኖም ከባሕል ውጭ ከየትኛውም እምነትና ሐይማኖት ጋር የሚያያዝበት ሁነታ የለም።
“ምስጋና ለፈጣሪ የሚቀርብበት ሁኔታ ከእምነት ጋር የተያያዘ አይደለም። በብሔረሰቡ አካባቢ እህል ገና ሲዘራ ጀምሮ በሚያሽትበትና በሚደርስበት ጊዜ ሰብሉን የሚያጠቁ የተለያዩ ተባዮች፤የዱር እንሰሳና የቤት እንስሳት አሉ። ተወላጆቹ ታዲያ ፈጣሪ ከነዚህ ሁሉ እህል ሊያጠፉ ከሚችሉ ጠብቆ እህሉ ስላደረሰላቸው ከሕዳር አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚያቀርቡት ምስጋና ነው። ሰኔ፣ ሐምሌ፤ነሐሴ፣ መስከረም እስከ ጥቅምት መጨረሻ ያለው ወራት ደግሞ ኃይለኛ ዝናብ ፤ጎርፍ የውሃ ሙሌት አስጨናቂ የጨለማ ወቅት አልፎ ብርሃን ለማየት ከመብቃታቸው ጋርም ይሰናሰላል።
የቤንች ብሔረሰብ ቋንቋ ‹‹ቤንችኛ›› ሲሆን ከምዕራብ ኦሞ አዊ የቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል። የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ አማርኛ፣ ካፊኖኖ እና ሸኮኛ ቋንቋዎችን ይናገራሉ።
በ‹‹ቤንችኛ›› ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑት በነዚህ ብሔረሰብ ዘንድ ታድያ ከወቅቶች ጋር ተያይዞ ምርት እንዲሰጥ፣ በሽታ እንዲጠፋ፣ ሰላም እንዲሰፍን በዓመት ሦስት ጊዜ የሚከበሩ በዓላቶች አሉ። ቢስት ባር ከነዚህ አንዱና ዋነኛው ነው። የዘመንና የወቅት አቆጣጠርን ተንተርሶ ከአዝመራ ወቅቶች ጋር በመዛመድም እንዲሁም በዚሁ ወቅት ከፈጣሪው ለተቸረው ፀጋ ምስጋና ከማቅረብ ጋር ተያይዞ ይከበራል። ለዚህ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያና የምስጋና በዓል ድምቀት፤በምግብ መጠጥ ፌሽታ ለማድረግ ቦርዴ ይጠመቃል፤ ከብትና ዶሮ ይታረዳል።
ግን ደግሞ ይሄ ሁሉ ዝግጅት ከመደረጉና በዓሉ ከመድረሱ አንድ ወርና በፊት ለግድያ እስከ መደራረስ ዘልቀው ደም የተቃቡ እንኳን ቢሆኑ በሃገር ሽማግሌዎች እንዲታረቁ ይደረጋል። ከባሏ ተፋትታ ከቤት የወጣች ሴት የግድ ከባለቤቷ ጋር እርቅ መፈፀም አለባት። በዓሉ የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት በመሆኑም አስቀድሞ እርቅ ሳይፈፀም አይከበርም። በመሆኑም ቢስት ባር ባሕላዊ የአንድነት እሴት ያለበትም በዓል ነው ማለት ይቻላል።
ቢስት ባር አምናና ዘንድሮ ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ፤ በተደራጀና በዘመናዊ መልኩ ከመከበሩ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ሳይከበር ቆይቷል። በሕይወት ያሉ የዕድሜ ባለፀጋ አባቶች እና አፈታሪኮችን ዋቢ አድርገው ኃላፊው እንደሚያነሱት ከሆነ በዓሉ መከበሩ ከተቋረጠ ከ40 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ምክንያቱ ትልልቅ ወረርሽኝ በሽታዎች፤ጦርነቶች ፤በተለይም .የቢስት ባር. በዓል ምንጭ የሆኑት ብሔረሰቦች አንድ ቦታ ላይ ተረጋግተው መቀመጥ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰው ስለነበር በዓሉ ተቋርጦ እንዲቆይ ተደርጎ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
ሆኖምየብሔረሰቡ ተወላጆች፤ ወጣቶች፤ በተለይም የጎሳ መሪዎችና አባቶች፤ ሴቶች የራሳቸው ማንነት ጉዳይ በመሆኑ፤አብሮነቱ፤ በጋራ መመገብ፤ ለአባቶች የሚሰጠው ቦታ ክብር ለማኅበረሰቡ ሊጠቅሙ የሚችሉ ባሕላዊ እሴቶች በተደጋጋሚ ጉልህ እሴቶች እንዳሉት በመጥቀስ ባደረጉት ግፊት ነው ከአምና ጀምሮ መከበሩ የቀጠለው። ከመከበሩ በፊት አምስት ዓመታት የፈጀ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ሲደረግበት ቆይቷል። ጥናቱ በዓሉ ሲከበርበት የቆየውንና አምና እና ዘንድሮ የተከበረበትን የቤንች ብሔረሰብ መገኛ የሆነውን በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ዣዥ ቀበሌ በሚገኘው ሥፍራ ላይም ጥልቅ ዳሰሳ ያደረገ ነው።
“በቤንች ማኅበረሰብ ታሪክ ውስጥ ሁለት ትላልቅ ቦታዎች ይጠቀሳሉ” የሚሉት ኃላፊው አንዱ የቤንች ብሔረሰብ እንደ ሕዝብ ራሱን ያደራጀበት ቤንች የሚባለው ብሔር መገኛ ዣዥ የሚባለው ቦታ ስለመሆኑም ያወሳሉ። 16 ሄክታር ስፋት ያለውንና እስከ 20ሺህ ሕዝብ የሚይዘው ይሄ ሥፍራ ቤንች የሚገኝበት ቦታ ነው ተብሎ የሚወሳ፤ማንም ያልነካው፤ማንም ያላረሰው፤ማንም ያልደረሰበት ነው። ቦታው በጋም ሆነ ክረምት ደርቆ የማያውቅ፤ የትልቅ ውሃ መገኛ ሲሆን ትላልቅ ከድንጋይ የተሰሩ የሰው፤ የፈረስ ኮቴና የሰው ኮቴ ጎጆ ቤቶችም አሉበት።
መምሪያው በዚህ ሥፍራ የሚከበረው ቢስት ባር በዓል ለቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ማገልገል የሚችልበትን መንገድ አመቻችቷል። ቦታውም በማዕከልነት ለቱሪስት መዳረሻ እና ለአርኮሎጂስቶች ጥናትና ምርምር፤ የቱሪስት ማዕከልም ሆኖ ያገለግላል ብሎ አስቦ እየሰራ ይገኛል።
ኃላፊው እንደሚናገሩት በብሔረሰቡ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ሁለተኛው ቦታ ከዛሬ 40 ዓመት በላይ የቢስት ባር በዓል ማጠቃለያ የሚከበርበት የነበረው ሚዛን አማን አካባቢ ላይ የሚገኝ የአየር ማረፊያ ማዕከል ነው። ማኅበረሰቡ ማዕከሉን የሰራው ማንኛውም ዓይነት ዶዘርም ሆነ ዘመናዊ ማሽን ሳይጠቀም በሰው ኃይልና ጉልበት ብቻ በመሆኑ የአባቶች ጀግንነትና የሥራ ወዳድነት ማንፀባረቂያ ተደርጎም ይወሰዳል።
በብሔረሰቡ የጎሳ መሪዎች የሚባሉት መገኛም ነው። እነዚህ የጎሳ መሪዎች ቤኒስቴክ ፤ማቴክና ሼኬት ተብለው የሚጠሩ ሲሆኑ ሦስት የተለያዩ ንጉሶችም አሏቸው። በመሆኑም ቦታው የተለያዩ የዳኝነት ስርዓታቸውን የሚፈጽሙበት ቦታ ሆኖ ያገለግላል። በመምሪያው የቱሪዝምና የባሕል ሀብት ሆኖ ማገልገል ይችላል የሚል እምነትም አለ። በዚህ መሰረት ጥናት ቢደረግ በዩኒስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ሊያገለግል የሚችልበት ሁኔታ ለመፍጠርም እየተሰራ ይገኛል። ሥራው በስፍራው ማኅበረሰቡ በታሪኩ ከጥንት ጀምሮ ሲገለገልባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን ማዕከል አድርጎ እየተከናወነ ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ባሕል ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ የባሕልና ታሪክ ቅርስ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ ደምሴ ሶኪያብ እንደሚናገሩት፤ ከሙዚቃ እና አጨፋፈር ስርዓት ጋር በተያያዘ በሀገሪቱና በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የለም የሚባል “ቶህ” የተሰኘ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ አለ። ተወላጆቹ ቤስት ባር በሚከበርበት ወቅት ይጫወቱበታል። በመሳሪያው ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሲጫወቱ ያደጉ ካልሆኑ በስተቀር መጫወት አይችሉም። እናም ይሄን መሳሪያ ጨምሮ የብሔረሰቡ የጦር መሳሪያ፤ጠመንጃ፤ ጦር፤ ባሕላዊ ቁሳቁሶች፤ባሕላዊ አልባሳት ፤ መቀመጫዎች እና ሌሎች በርካታ መገልገያዎች በስፍራው ይገኛሉ። ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እነዚህ በማዕከሉ ተከልለው በብሔረሰቡ በቅርስነት በጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል።
የቤንች ሸኮ (ቤንች ማጂ) ዞን ሕዳር 14 ቀን 2014 ላይ ከሕዝበ ውሳኔ በኋላ በተመሰረተው አዲሱ የኢትዮጵያ ክልሎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው። እንደ ዲዚ፣ ሱሪ፣ ሸኮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ መዠንገር፣ ቤንች፣ እና መኢኒት ያሉ ብሔረሰቦች በዞኑ የሚገኙ ናቸው። በዓመት ሦስቴ በብሔረሰቡ ከሚከበረው በዓል አንዱና ዋነኛውም ቢስቲ ባር የተሰኘው የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም