ዲዛይነሯ የኢትዮጵያ ተወካይ…

ኤደን ሙሉሸዋ ትባላለች። ትውልድና እድገቷ በአዳማ ከተማ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ መጥታ መኖር የጀመረችው በልጅነቷ ነበር። ‹‹ ከተሜ ፋሽን ›› የተሰኘ የተለያዩ የእደ-ጥበብ ውጤቶችና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ናት ።

ከተሜ ፋሽን ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ያክል ጊዜን አስቆጥሯል። የእደጥበብ ውጤቶችን በክር የሚሰሩ ልብሶችን፣ ጫማዎችንና የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎችን እንዲሁም ከክር የሚሰሩ ቦርሳዎችን ከቦርሳ ጋር በማጣመር ትሰራለች። በዚህም ሥራዎቿን በምታስተዋውቅባቸው የማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የራሷን ደንበኞች ማፍራት ችላለች ።

ለምትመለከታቸው የተለያዩ ችግሮች መፍትሄ መስጠት ውስጤን ያስደስተኛል የምትለው ኤደን ሥራዎቿን የጀመረችበት አጋጣሚ ከራሷ ችግር በመነሳት መሆኑን ትናገራለች። ዛሬ ላይም ለብዙዎች መድረስ የሚችልና ጥሩ ተቀባይትን ያገኘ ‹‹ ከተሜ ፋሽን ›› መመስረት እንደቻለች ታስታውሳለች።

ኤደን በመምህርነት ሙያ ላይ ያለችው እናቷ የተለያዩ የልብስ ዲዛይኖችን፣ ጥልፎችን ትሰራ እንደነበር አስታውሳ በተጨማሪም ለቤት ውስጥ ማስዋቢያነት የሚውሉ የእደ-ጥበብ ውጤቶችን በቤት ውስጥ መመልከቷን ታስታውሳለች። ኤደን የዩኒቨርሲቲ የሦሥተኛ ዓመት ተማሪ በነበረችበት ወቅት የኮቪድ – 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋ ከተደረገ በኋላ በኢትዮጵያም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተገደቡበት ሰዓት ነበር። በዚያን ወቅት ኤደን ልክ እንደሌሎች ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ በቤት ውስጥ የመቀመጥ እድል ነበራት ።

‹‹ የኮቪድ ወቅት ብዙዎች ጊዜያችንን አባከንን ብለው የሚቆጩበት እና ሌሎች ደግሞ ራሳቸውን ያገኙበት ነው ። ›› የምትለው ኤደን በዚህን ወቅት ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የሚያሰላስለው አዕምሮዋን በመፈተሽ አዳዲስ ልምዶችን መቅሰሟን ገልጻለች ።

አብዛኛውን ጊዜ የሴቶች ጫማ በሚፈለገው የጥንካሬ ደረጃ ፣ ምቾት እና ባለው የጥራት ማነስ ምክንያት ረጅም ጊዜ መቆየት የማይችል መሆኑ ኤደንን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ሴቶች የሚስማሙበት ነው ። ታዲያ በዚህ ምክንያት ኤደን ይህንን ችግር ለመፍታት በቤት ውስጥ የምታገኛቸውን ያገለገሉ ሶሎች ከጫማዎች ላይ በማንሳትና ክርን በመጠቀም በተለየ ዲዛይን ምቾት ያለው ጫማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰራች።

በቤት ውስጥ በሚኖራት ሰፊ ሰዓትም የተለያዩ የአበባ ማስቀመጫ እቃዎችን በመስራት አዳዲስ ልምዶችን ማዳበሯን ቀጠለች ። ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎችን መስራትና አዳዲስ ፈጠራዎችን መሞከር የሚያስደስታት ኤደን ከምታያቸው የተለመዱ የክር ሥራዎች ባሻገር ለየት ያለ ፈጠራን በማከል ልብሶችን በመስራት በወቅቱ በማኅበራዊ ገጽ ላይ በማጋራት መሸጥ ጭምር እንደቻለች ታስታውሳለች ።

ከወራት ቆይታ በኋላ ወደ ትምህርቷ ስትመለስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የነበራትን ቆይታ ለማጠናቀቅ የቻለችው ከተለመደው የተማሪዎች መመረቂያ ወቅት ዘግይቶ የዓመቱ መጀመሪያ መስከረም ወር ላይ ነበር። እንደ ማንኛውም ተማሪ የተለያዩ ተቋማት ላይ ተወዳድራ አልፋ በመቀጠር መስራት በእቅዷ ውስጥ ቢኖርም አብዛኛዎቹ ተቋማት የሰው ኃይል ለመጨመር የሥራ ቅጥር የሚያወጡት በሰኔ ወር ላይ በመሆኑ እሷ በምትፈልገው ዘርፍ ሥራ ማግኘት አልቻለችም ።

‹‹ ማንኛውም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የወጣ ተማሪ የራሱን ገቢ ማግኘት መፈለግ ግልጽ ነው ። እኔም ከቤተሰቦቼ ገንዘብ መጠየቅ ስለማልፈልግ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እያመለከትኩ የራሴን ሥራ ለመስራት አስብ ነበር ። ›› ስትል የነበረውን ሁኔታ ታስረዳለች።

ኤደን ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች በኋላ ከዚህ በፊት የሰራቻቸውን ሥራዎች እንደ ግብዓት በመጠቀም ለራሷ በመስራት በቅርቧ ላሉ ሰዎች በማስተዋወቅ በዙርያዋ ያሉት ሰዎች ሥራዎቿን እንዲሞክሩት ታደርግ ነበር። በዚህም ወቅት ቤተሰቦቿ በሥራዋ ይደግፏት እንደነበርና የጎደሏትን እቃዎች በማሟላት ይበልጥ እንድትሰራ ያበረታቷት ነበር ። ይህ ከቤተሰቦቿ የምታገኘው ድጋፍና ማበረታቻ የምትሰራቸውን ሥራዎች ራሷ ተጠቅማ በምትወጣበት ጊዜ ከሰዎች የሚደርሳት አድናቆት ሀሳቧን በማጠናከር ወደ ቢዝነስ እንድትቀይረውና ትኩረት ሰጥታ እንድትሰራበት አግዟታል ።

‹‹ በምንም ሊተካ የማይችለውን የሰው ልጅ ፈጠራና በገንዘብ ሊተመን የማይችለውን የሰው ልጅ ጉልበት የሚፈስበት ቢሆንም ብዙ ሰዎች ይህንን ለማቃለል ይሞክራሉ ። ለእደ-ጥበብ ውጤቶች በማኅበረሰባችን ዘንድ ያለው ተቀባይነት አነስተኛ መሆኑን የምትገልጸው ኤደን ሰዎች በእጃቸው ለሚሰሯቸው ሥራዎች ለሚያጠፉት ጊዜ ልፋት እና የፈጠራ ውጤት የሚሰጠው ግምት አነስተኛ እና ሊቀረፍ የሚገባው ነው ስትል ትገልጻለች ።

ሥራዎቿን ሊወደዱ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ ሰዎች ከሰራች በኋላ ወደ ማኅበራዊ ገጽ ላይ በማስተዋወቅ ሌሎች ደንበኞችን ማግኘት እንደምትችል በማሰብ ሥራዎቿን ማስተዋወቅ ጀመረች ።

‹‹ ከተሜ የሚለው ሀሳብ በሀገር ውስጥ የተሰራ በመሆኑ ስያሜውን እንዲለቅ አልፈለኩም ። አንድ ሰው በተምዶው ወደ ከተማ ሊዝናና ሲወጣ ዘንጦ አምሮበት ነው የሚወጣው ። ታዲያ ከከተማ ሲመለስ ከተሜው የሚል መጠሪያ ይሰጠዋል ። ›› ኤደን የምትሰራቸው ሥራዎች በሀገር ውስጥ የተሰሩ የሀገር ውስጥ ምርት የሆኑ እና ሰዎች ሊዘንጡበት የሚችሉት በመሆኑ ከተሜ የሚል ስያሜ ልትሰጠው ችላለች ። ለአንድ ዓመት ያክል ጊዜ ከሰራችበት በኋለም ሥራዎቿ የሚጠሩበትን ከተሜ የሚል ስያሜ ልትሰጠው ችላለች።

የተመረቀችበት የትምህርት ዘርፍ በይበልጥ የተለያዩ ማሽኖች ዲዛይን ማድረግ ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ዲዛይኖችን መስራት በይበልጥ ትኩረት አድርጓል ። በመሆኑም ልዩነቱ በዚያኛው ዘርፍ የተለያዩ ማሽኖችን ዲዛይን ማድረግ ሲሆን ይኼኛው ሥራዋ ደግሞ ፋሽን ላይ ያተኮረ ነው ።

አዳዲስ ፈጠራዎችን መሞከር የሚያስደስታት ኤደን ሥራዎቿን ወደ ገበያ ይዞ በመውጣት ሰዎችን አሳምኖ እንዲገዙ ማድረግ ፣ ማስተዋወቅ እስክትለምደው ድረስ የከበዳት ነገር እንደነበር ታስታውሳለች ። ኤደን ሥራዎቿን በምታስተዋውቅበት የማኅበራዊ ገጽ አብዛኛው በሥራ ዓለም ላይ ያሉ ሰዎች እርስ በርስ ሀሳብ የሚለዋወጡበት እና የሥራ ማስታወቂያዎች በብዛት የሚታዩበት የሊንክዲን ገጽ ኤደን የምታዘወትረውና ሥራዎቿን ለማስተዋወቅ በይበልጥ የምትመርጠው ነው ።

‹‹ ሊንክዲን ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች በብዛት ሀሳባቸውን የሚያጋሩበት ነው ። ብዙ ሰዎችን እዚያ ላይ ያበረታቱኛል ሥራዬን ያዩ የውጭ ሀገር ዜጎችም ትዕዛዞችን ተቀብዬ እሰራለሁ። ›› የምትለው ኤደን በአብዛኛው በማኅበራዊ ገጽ ላይ ደንበኞችን አፍርታ የምትሰራ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች በስልክ ፎቶ ላይ ያዩትን ከተለያዩ ድህረ-ገጾች ላይ ወስዳ የምታጋራው እንጂ ራሷ የምትሰራቸው ስለማይመስሏት ለማመን እንደሚጠራጠሩ ትገልጻለች ። ወደፊትም ከማኅበራዊ ገጽ ባሻገር የምትሰራቸውን ሥራዎች ሰዎች በአካል ሄደው ማየት እና የወደዱትን መግዛት የሚችሉበትን መንገድ መፍጠር አንዱ እቅዷ ነው ።

ኤደን አሁን ላይ በክር የሚሰሩ ጫማዎችን ፣ ቦርሳዎችን ፣ ልብሶችን ምንጣፍና ሌሎች የቤት ውስጥ ማስዋቢያዎቸ እየሰራች ትገኛለች ።

ኤደን የተለያዩ አዳዲስ ልምዶችን የመሞከር ልምድ ያላት በመሆኑ በሚቀጥሉት ሳምንታት ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ለእንግዶቿ ሊያስተዋውቁ የሚችሉ የተለያዩ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን አሰልጥኖ እንግዶቹን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ትገኛለች ።

‹‹ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ትልቅ ሁነት ነው ። በዚያ ላይ ሀገርን ወክሎ መገኘት ትልቅ እድል በመሆኑ ጥሩ ልምድ ይሆነኛል በሚል ነበር የተመዘገብኩት ።›› የምትለው ኤደን ቦታው የሚጠይቀውን መስፈርት የቋንቋ ክሕሎት አሟልታ ስልጠናውን ልትወስድ ችላለች። በስልጠናው በከተማችን አዲስ አበባ የተሰሩ የቱሪስት መስሕብ ቦታዎችን በመጎብኘት ይበልጥ እውቀት እንዲኖራቸው ያደረገ በመሆኑ በራስ መተማመን እንዲኖረን እና ያለን የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚጨምር ስልጠና ሆኖ እንዳገኘችው ገልጻለች ።

‹‹ ዋናው ሥራ ሀገርን ማስተዋወቅ ፣ የሀገርን ገጽታ መገንባት ነው ። በሥራዬም ብዙ የውጭ ዜጎች ሥራዬን ሲያዩ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ከየት ሀገር ነሽ የሚል ነው ። ስለዚህ ይህንን ስልጠና መውሰዴ በጣም ጠቅሞኛል ። ››

ኤደን አሁን ላይ የምትሰራውን የራሷን ከተሜ ፋሽን ጥሬ እቃዎችን ከመሰብሰብ አንስቶ ፈጠራዎችን አክሎ በመስራት ትዕዛዞችን መቀበል ማስተዋወቅ እና የመሸጥ ሥራ ሁሉንም የምታከናውነው ራሷ ነች ። በሥራ አጋጣሚ ባገኘችው እድልም የተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ላይ ሥራዎቿን ይዛ ትቀርባለች ።

ኤደን የምትሰራቸውን በርካታ የእደ-ጥበብ ውጤቶች የፋሽን ሥራዎች በማስፋት ሰዎች በአካል መጥተው ሊያዩ እና ሊገዙ የሚችሉበትን ሱቅ ፣ የከተሜ ፋሽንን በማሳደግ እያንዳንዱ የፈጠራ ሥራ የራሱ የሥራ ክፍል በማደራጀት እና ለሌሎቸ ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር ማስፋት የወደፊት ሕልሟ ነው ።

ዛሬ ላለችበት የሥራ ወቅትም እቃዎችን በማሟላት የሚያግዟትን እና ሥራዎቿን አይተው የሚያበረታቷትን ቤተሰቦቿን ታመሰግናለች ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You