
ኢትዮጵያ ከተራራማ ቦታዎች የሚነሱ ድንበር ተሻጋሪና ተሻጋሪ ያልሆኑ በርካታ ወንዞች፣ ትናንሽና ትላልቅ ሐይቆች እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት ያላትና በየዓመቱ ከፍተኛ ዝናብ የምታገኝ ሀገር ናት፡፡
ሀገሪቱ ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሀገራት የሚተርፍ የውሃ ሀብት ቢኖራትም ይህንን ፀጋ በአግባቡ መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ መቆጣጠርና ማልማት የሚያስችል ወሳኝ የሕግ ማሕቀፍ ባለማዘጋጀቷ ሀብቷ ለብክነትና ለብክለት ሲዳረግ ኖሯል፡፡
ከሰሞኑ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያግዛሉ የተባሉ የውሃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማትና እንክብካቤ እንዲሁም የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጆችን አዘጋጅቶ ከውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
ረቂቅ አዋጆቹ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ሥርዓትን ከማሻሻልና ለዘመናት ቁጭታችን መልስ ሰጥተው የዜጎችንና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር የሚኖራቸው አበርክቶ ምን ሊሆን ይችላል? ስንል ምሑራንን እና የዘርፉን ተመራማሪዎች አነጋግረናል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ምሕንድስና እና አስተዳደር መምህር እንዲሁም የኢትዮጵያ ውሃ ሀብት ባለሙያዎች ማኅበር መሥራች ፕሬዚዳንት አማኑኤል አባተ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ ሌሎች ሀገራት አልማዝና ወርቅ የመሳሰሉ የተፈጥሮ ፀጋዎች እንደተሰጣቸው ሁሉ ኢትዮጵያም ከተሰጧት የተፈጥሮ ፀጋዎች ትልቁ የውሃ ሀብቷ ነው፡፡ ይሁንና እስከ አሁኑ ድረስ የተሰጣትን ፀጋ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ክፍተት አለባት፡፡
ግብፅ ከኢትዮጵያ ውሃ እየወሰደች ምርታማ እንደሆነችና 24 ሰዓት ለዜጎቿ ውሃ እንደምታቀርብ ያስረዱት አማኑኤል (ዶ/ር) እስከ አሁን ድረስ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ውሃ በፈረቃ እንደሚዳረስና፤ ለዚህም አንዱ ምክንያት ውጤታማ የሆነ የውሃ አስተዳደር ሥርዓት አለመዘርጋቱ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
እነዚህ ረቂቅ አዋጆች ፀድቀው ወደ ሥራ የሚገቡ ከሆነ ግን የውሃ ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚቻልና ከሀብቱ የሚገኘውን ጥቅም ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ያስረዳሉ፡፡ ውሃ ወደፊት የዓለምን ኢኮኖሚ የሚዘውር ትልቁ የተፈጥሮ ሀብት ይሆናል ተብሎ ይገመታል የሚሉት አማኑኤል (ዶ/ር)፤ ሀብቱን በሥርዓት ለማስተዳደር የሚወጡት ሕጎች አስፈላጊ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃና መስኖ ምሕንድስና ፋኩሊቲ መምህርና ተመራማሪ አያኖ ሂርቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያ ከ122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የገጸ-ምድር እና ከ2 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የከርሰ-ምድር የውሃ ሀብት እንዳላት ጥናቶች ግምታዊ መረጃን ያስቀምጣሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ጥቅም እየሰጠ የሚገኘው ሦስት በመቶ የሚሆነው ብቻ እንደሆነና ከሦስት በመቶው 11 በመቶ የሚሆነው ለመጠጥነት ሲውል ሌላው ለንጽሕና እና ለግብርና የሚውል እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
በዚህ የጥናት መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ገልጸው፤ ለውሃ ሀብት ትኩረት ሰጥቶ እንዲህ አይነት የሕግ ማሕቀፍ ማዘጋጀት ሀብቱን፣ ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ፣ ለመቆጣጠርና ለማልማት መደላድል ይፈጥራል ይላሉ ፡፡
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና እና ገጠር ልማት ምርምር ማዕከል መሪ ተመራማሪ መኮንን በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ በሀገር ደረጃ ትልቅ የውሃ ሀብት ቢኖርም የሚገባውን ያህል ጥቅም እንዲሰጥ አልተደረገም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፖሊሲ የወጣው በ1999 ዓ.ም ነው፤ ፖሊሲው ውሃ ለመጠጥና ለንጽሕና፣ ለመስኖ እና ለኤሌክትሪክ ኃይል በሚውልበት ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥን እንደነበርም ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ዜጎች ከውሃ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ኢንቨስትመንት ባለመኖሩ ባለው ሀብት ልክ ጥቅምን ማረጋገጥ አልተቻለም ይላሉ፡፡ ከሰሞኑ በውሃ ሀብት ላይ የተረቀቁ አዋጆች የሚፀድቁ ከሆነ የዘርፉ ችግሮች ተቀርፈው፤ የዜጎችና የሀገር ተጠቃሚነት እንደሚረጋገጥ ያስረዳሉ፡፡
እንደ አማኑኤል (ዶ/ር) ገለጻ የውሃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማትና እንክብካቤ በሚል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፤ የውሃ ሥነ ምሕዳሮችን በአግባቡ በመጠበቅ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እና ሀብቱ ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ያስችላል፡፡ ከውሃ ዳርቻ በቅርበት ሆነው የውሃ አካልን የሚበክሉ የእርሻ ሥራዎች፣ በካይ የሆኑ ቆሻሻዎች፣ መፀዳጃ ቤት፣ የሞቱ እንስሳት፣ የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችና ፍሳሾች በውሃ አካላት ላይ እየተጣሉ በኢኮ ሲስተሙ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ያደርጋል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባትም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ይላሉ፡፡
አያኖ (ዶ/ር) ይህንኑ ሀሳብ ሲያጠናክሩ የውሃ ዳርቻዎች ወሰን ተደርጎላቸው በሣርና ዕፅዋት ካልተሸፈኑ ወንዞች ይበከላሉ፤ በደለል ሊሞሉ ይችላሉ፤ ግድቦች የማመንጨት አቅማቸው ይቀንሳል፤ ከፋብሪካ የሚለቀቁ በካይ ነገሮች ውሃ ውስጥ ገብተው እንደዓሣና ሌሎች እንስሳትን ወይም ሰውን ጭምር ሊጎዱ ይችላሉ፤ ስለዚህ የውሃ አካላት ለአደጋና ለብክነት ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ወሰን (buffer zone) ማበጀት አስፈላጊ ነው።
የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ወቅትን ጠብቆ የሚዘንበውን ዝናብ መሰብሰብ ወይም ማቆርም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በዚህ አዋጅ ውስጥ መታቀፍ ያለበት አንድ ጉዳይ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ ሀብት አጠቃቀምና እና አስተዳደር ዙሪያ ወንዞችን እና ሐይቆችን መሠረት አድርጎ ጥናትና ምርምር የሚያደርግ እንደመሆኑ የአዋጆቹ መውጣት እንደ አርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ላሉና በውሃ ዙሪያ ለሚሠሩ ተቋማት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
በየጊዜው እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር አንጻር የውሃ ፍላጎትም በዚያው ልክ ያድጋል ያሉት መኮንን (ዶ/ር) የሚቋቋመው የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት የውሃ ሃብትን በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡ የመስኖ ሥራን የመጠቀሙ ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ ገልጸው ከወዲሁ የሕግ ማሕቀፍና ረዥም እቅድ ማዘጋጀት ከውሃ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለማስወገድና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ያስረዳሉ፡፡
የስንዴ ምርታማነትን ማሳደግ የተቻለው በበጋ የመስኖ ግብርናን በማከናወን ነው፤ ለዚህም ትልቁ ግብዓት ውሃ ነው፤ ውሃ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እና የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ በመሆን ዘመናዊ አኗኗርን ለመምራት አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ምሑራኑ ይስማማሉ፤ ሀብቱን በአግባቡ ለመምራትና ለማስተዳደር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም በጣም አስፈላጊ ግን ደግሞ የዘገየ ነው ይላሉ፡፡
የውሃ አስተዳደር ሥርዓትን በማስፈን የበጋ ግብርናን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫን፣ የዓሣ ርባታን ፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ኢኮኖሚን ማሳደግና በእርግጥም ውሃ ለኢትዮጵያ የተሰጣት ትልቁ ፀጋ መሆኑን በሥራ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስረድተው፤ አዋጆቹ ይህንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእጅጉ የሚያግዙ ስለመሆናቸው ምሑራኑ ተመሳሳይ ሀሳብ ያካፍላሉ፡፡
በኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም