ኢትዮጵያ በዚህ ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ትግበራ ገብታለች። በዚህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንደሚተከል ይጠበቃል። የዚሁ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካል የሆነ ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል መርህ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኞች የሚተከሉበት መርሐ ግብር የፊታችን ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል።
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት የሚካሄደውን ይህን የአራት ቢሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር የሚመራ ኮሚቴም ተዋቅሮ ነው ሥራው እየተካሄደ የሚገኘው።
ሀገሪቱ ይህን ያህል ችግኞችን ለመትከል ያቀደችው በጥናት ላይ ተመስርታ እና 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞች መኖራቸውን አረጋግጣም ነው። ይህም መርሐ ግብሩ ታስቦበት እና ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ያመለክታል።
የችግኝ ተከላው በሰኔ ወር የተጀመረ ሲሆን፣አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መርሐ ግብር 1 ሺ ችግኞችን እንደሚተክሉ ቃል በመግባት በግቢያቸውና በየሄዱበት ሁሉ ችግኝ ተከላውን ተያይዘውታል።
የፊታችን ሀምሌ 22 ለሚካሄደው የችግኝ ተከላም በክልሎች የሚተክሉትን የችግኝ ብዛትና የመትከያ ስፍራዎች ይፋ ተደርገዋል። የኦሮሚያ ክልል 126 ሚሊዮን ፣የአማራ ክልል 108 ሚሊዮን፣ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል 48 ሚሊዮን፣ የትግራይ ክልል 12 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅተዋል። ክልሎቹ ችግኞቹ እንደሚተከሉ የሚጠበቅባቸውንና በእርግጠኝነት የሚተከሉባቸውን ስፍራዎችም ለይተዋል።
የተቀሩት ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችም ለችግኝ ተከላው ዝግጅት እያደረጉ ናቸው። በሀገሪቱ ከተሞችም ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ለችግኝ ተከላውም የጉድጓድ ቁፋሮና ችግኞችን ወደሚተከሉበት አካባቢ የማጓጓዝ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ህዝቡ ችግኞቹን ለመንከባከብ እንደሚሠራ በማረጋገጥም ጭምር ነው ተከላውን እያካሄዱ የሚገኙት። ክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ እያደረጉ ያሉት ዝግጀት መርሐ ግብሩ በስኬት እንደሚጠናቀቅ አመላካች ነው።
የችግኝ ተከላው ከማንም በላይ በደን መመናመን ሳቢያ ክፉኛ እየታመመች ለምትገኘው ሀገራችን ፍቱን መድሃኒት ነው። እንደሚታወቀው የሀገራችን የደን ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ያለበት ሁኔታ ነበር። ሀገሪቱ ህዝቡን በማስተባበር በደን ልማት ላይ ባለፉት ዓመታት ባከናወነቻቸው ተግባሮች ይህን አኀዝ ወደ 15 በመቶ ከፍ ማድረግ ችላለች።
አራት ቢሊየን ችግኞችን የመትከሉ አካል የሆነውን 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል የተያዘው እቅድም ግዙፍ እንደመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ ነውና ህዝቡ በተከላው ርብርቡን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ስኬታማ ማድረግ ይጠበቅበታል።
የችግኝ ተከላው ትርጉም ብዙ ነው። የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣የደን መመናመን እና የመሳሳሉት ዓለማችንን ለካርቦን ልቀት እየዳረጓት ባለበት በዚህ ዘመን ከዚህ ችግር ለመውጣት ሁነኛው መፍትሔ የደን ልማት እንደሆነ ሳይንቲስቶች ይፋ እያደረጉ ይገኛሉ። ሀገራችን ይህን ያህል ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል እያካሄደች የምትገኘው ርብርብ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ከካርቦን ልቀት ለመታደግ ለተያዘው ዓለም አቀፍ ጥረትም ፋይዳው ከፍተኛ ይሆናል።
200 ሚሊዮን ችግኝ ተከላው የዓለማችን ክብረ ወሰን እንደሚሆንም እየተጠበቀ ይገኛል። እስከ አሁን ክብረ ወሰኑ የተያዘው 50 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ቀን መትከል በቻለችው ህንድ ነው። የደን ልማት በዓለም አቀፍ ድጋፍ ጭምር መካሄድ ያለበት ተግባር እንደመሆኑ ይህ ክብረ ወሰን ለደን ልማቱ ዓለም አቀፍ ድጋፎችን ለማሰባሰብም ይጠቅማል።
ይህን ያህል ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ከፍተኛ የንቅናቄ ሥራ ማካሄድን ይጠይቃል። ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚተክሏቸውን ችግኞች ብዛት በማሳወቅ፣ የመትከያ ስፍራዎችን በመለየት፤ የመትከያ ጉድጓድ በማዘጋጀትና ችግኞችን በማጓጓዝ የሚያደርጉት ዝግጅት ህዝቡን ለማነቃነቅ የተከናወነው ተግባር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል።
200 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ቀን ለመትከል እጅግ በርካታ ህዝብ እንደሚሳተፍ እና ይህም በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው እንደሚሆን ይጠበቃል። አሁንም ህዝቡን የማነቃነቁ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ በክብረ ወሰን ሊያዝ የሚችል እንደመሆኑም ምን ያህል ህዝብ በተከላው እንደሚሳተፍም ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል።
የችግኝ ተከላው ችግኞቹን ለመንከባከብ እንዲረዳ በሚልም ህዝብ በሚኖርበት አቅራቢያ ላይ እንደሚካሄድ መገለጹ ይታወቃል። እየተካሄዱ ከሚገኙ አንዳንድ የችግኝ ተከላ ሥራዎች መረዳት እንደሚቻለው ትንሽ ወጣ ማለትም ሊኖር ስለሚችል ለስምሪቱ የሚያስፈልገው ትራንስፖርት በበቂ ሁኔታ መዘጋጀትም ይኖርበታል። ስለሆነም ሁሉም ‹‹ለአረንጓዴ አሻራ››ው መርሐግብር አሻራውን ያሣርፍ-መልዕክታችን ነው።
ከወዲሁ ማን የት እንደሚተክል መርሐ ግብር ከወዲሁ በማውጣት ህዝቡን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ሁላችንም በነቂስ ወጥተን በእዚህ የችግኝ ተከላ በመሳተፍ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ››ው አሻራችንን እናሳርፍ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011