አዲስ አበባ፡- አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ለሚደረጉ የመጻሐፍት ዓውደ ርዕዮችና የንባብ ፕሮግራሞች መንግስት ትኩረት እንዳልሰጠ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ በየዓመቱ የሚያካሂደውን የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይና የንባብ ፕሮግራም ትናንት ጀምሯል፡፡ በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ተቋማትና ባለሥልጣናት አልተገኙም፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ባለሥልጣናት ያልተገኙት መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ስላልሰጠውና ንባብን እንደ ተራ ነገር ስለሚያየው ነው፡፡
በየዓመቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ይደረግ የነበረው የማህበሩ የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይና የንባብ ፕሮግራም በዚህ ዓመት የዘገየውም በጸጥታ ስጋት በሚል ምክንያት በመንግስት ክልከላ ነው፡፡
‹‹የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይና ንባብ የፀጥታ ስጋት ሊሆን አይችልም›› ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ የፀጥታ ስጋት አለ በተባለበት ሰሞን የጠጅ እና የሌሎች አልኮል መጠጦች ባዛር እንደነበር ታዝበዋል፡፡ ከአልኮል መጠጥ ይልቅ መጽሐፍ የፀጥታ ስጋት መሆን እንደማይችልና መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠቱን ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያለው ችግር ሁሉ ያለማንበብና የዕውቀት ማጣት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ንባብን ለማበረታታት ታዋቂ ሰዎችን እና ባለሥልጣናትን ወደ ዓውደ ርዕዩ በማምጣት የማነቃቂያ ንግግር እንዲያደርጉ አስቦ የነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው እንደ ትምህርት ሚኒስትር ያሉ አካላትን ጨምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት አለመስጠታቸው በተለይም ወጣቱ ትውልድ አስተዋይ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ መንግስት ለንባብ ፕሮግራም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይና የንባብ ፕሮግራም ትናንት ሐምሌ 13 ቀን የተጀመረ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ያህል ይቆያል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ላይ ከ20 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸው መጻሕፍት ይሻጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
ዋለልኝ አየለ