አዲስ አበባ፡- መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የሚንከባከባቸውን አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ቁጥር 10 ሺህ ለማድረስ ዘመናዊ ሕንጻ እየገነባ ነው፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለት ዘመናዊ ሕንጻ ለአረጋውያኑ እና የአዕምሮ ሕሙማኑ ዘመናዊ ህክምናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የማዕከሉ ሕንጻ ግንባታው በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው ሕንጻው ከምድር በታች ሁለት ወለል ያለውና በአጠቃላይ ባለ 11 ወለል እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ መቄዶንያ በክልል ከተሞችም ሌሎች ማዕከሎችን ለመክፈት ያሰበ ሲሆን በ8161 አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ማንኛውም ሰው የበጎ አድራጎቱ ተግባር ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ከሁለት ሺህ በላይ ጧሪ እና ደጋፊ ላጡ ወገኖች እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባሩ ዓለም አቀፍ እውቅናን እያገኘ መምጣቱ በመግለጫው ተካቷል፡፡ በተለይም በአሜሪካን አገር በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከአሜሪካ ኮንግረስ፣ ሴኔት እና ካውንቲ እውቅና ማግኘቱ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር