• 16 ሚሊዮን ሰዎች በፍሎራይድ ውሃ ተጠቅተዋል
• 100 ሺዎቹ ብቻ ከፍሎራይድ የጸዳ ውሃ ያገኛሉ
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚኖሩ 16 ሚሊዮን ሰዎች ፍሎራይድ ባለበት ውሃ መጠቃታቸውንና ከእነዚህም መካከል ከፍሎራይድ የጸዳ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያገኙት 100 ሺ ሰዎች ብቻ በመሆናቸው መንግሥትና የተለያዩ ድርጅቶች ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ።
በመንግሥት ቦርድ የሚተዳደረው የኦሮሞ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት (ኦሾ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ከበደ እንደገለጹት፤ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ 16 ሚሊዮን ዜጎች በፍሎራይድ የተጠቃ ውሃ እንደሚጠጡ በጥናት ተረጋግጧል። በመንግሥት ተቋማት እና በተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች ትብብር ሥራዎች ቢከናወኑም እስከአሁን ከአካባቢው ነዋሪው አንድ በመቶ የሚሆነው እንኳን ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አላገኘም።
በመንግሥት በኩል ስለ ፍሎራድ ውሃ አደገኛነት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ሙሉጌታ፤ የኦሮሞ ራስ አገዝ ድርጅት አጥንት በማቃጠል ዘዴ /ቦን ቻር/ እና በሶዳ ንጥረ ነገር ውሃውን ለማከም በአካባቢው እየሥራ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁንና በአንድ ተቋም የውሃ አውታር ግንባታ መላውን የስምጥ ሸለቆ ነዋሪ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ማስቻል ከባድ በመሆኑ የችግሩን ግዝፈት ያመዛዘነ ሥራ በመንግሥት እና በተለያዩ ድርጅቶች ሊከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የኦሮሞ ራስ አገዝ ድርጅት የሞጆ የፍሎራይድ ማጥፊያ ቴክኖሎጂ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ኃይሌ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት ከዜሮ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊግራም የሆነ ፍሎራይድ በአንድ ሊትር ውሃ ውስጥ የሚል ነው። የፍሎራይድ መጠኑ ከሦስት ሚሊ ግራም ከበለጠ ችግር አለው።
በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በርካታ የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶችም ከተቆፈሩ በኋላ የፍሎራይድ መጠናቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተዘጉ አሉ። ይሁንና አብዛኛው የአካባቢው ውሃ አካላት አሁንም ብዛት ያለው የፍሎራይድ ችግር አለባቸው። እንደ ሻላ ሐይቅ አካባቢ ደግሞ እስከ 140 ሚሊ ግራም ፍሎራይድ በሊትር የደረሰ ውሃ በመኖሩ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።
በፍሎራይድ የተጠቃ ውሃን መጠጣት ለአጥንት መጉበጥ፣ ለስርዓተ ምግብ መፈጨት ችግር እና ለካንሰር ህመም መንስኤ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ ከዚህም በተጨማሪ የጥርስ መበለዝን እንደሚያስከትል ገልጸዋል። በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች በአብዛኛው የችግሩ ተጠቂ የመሆናቸውን ያህል ደግም ሥራው አልተሠራም ማለት እንደሚቻል አብራርተዋል።
የኦሮሞ ራስ አገዝ ድርጅት ‹‹ቦን ቻር›› የተሰኘውን ቴክኖሎጂ እና ሃይድሮክሲል አፓቲት የተሰኘ ንጥረ ነገር በማቀነባበር ውሃውን ለማጣራት እየሠራ መሆኑንም ጠቁሟል። ይሁንና ድርጅቱ ከመንግሥት እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ባከናወነው ሥራ እስከአሁን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያገኙት 100 ሺ ዎቹ ብቻ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ቀሪውን ህዝብ ከችግሩ ለማላቀቅ ሰፊ ሥራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ፍሎራይድ በብዛት ያለባቸው ውሃዎች በደብረታቦር፣ በቦረና እና ጊቤ ወንዝ አካባቢዎችም መገኘታቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታሁን፣ ጥናት ቢደረግ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎችም የችግሩ ተጠቂዎች ሊኖሩ እንደሚችል አመልክተዋል።
በውሃ ልማት ኮሚሽን የፍሎራይድ መከላከል ዳይሬክተር አቶ በላይ ስዩም እንደገለጹት ደግሞ፤ በፍሎራይድ የተጠቃ ውሃ ከተገኘ እና ማከም ካልተቻለ ሌላኛው አማራጭ ከሌሎች ቦታዎች ንጹሕ ውሃ በቧንቧ መስመር ማቅረብ ይመረጣል። በዚህ ረገድ ከተሞች በተለይም እንደ አዳማ እና ሐዋሳ የተሻለ የመጠጥ ውሃ ያገኛሉ።
ነገር ግን የገጠር አካባቢዎች አሁንም የችግሩ ተጠቂ ናቸው። በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያለውን የፍሎራይድ ውሃ አስመልክቶ እየተሠራበት ቢሆንም የችግሩን ስፋት ያክል ግን ምላሽ አልተሰጠም ማለት ይቻላል።
በሀገር ደረጃ ለፍሎራይድ ውሃ ማከም ሥራ 47 ሚሊዮን ብር የሚመደብ ቢሆንም አቅም በማጠናከር በፕሮጀክት መልክ ብቻ ሳይሆን ፕሮግራም ቀርጾ እስከ ወረዳ እና ቀበሌዎች ላይ እያስፈጸሙ የመጠጥ ውሃ ግንባታ ማከናወን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የችግሩን ግዝፈት ያክልም ዕርዳታ ድርጅቶችም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት በሰፊው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
ጌትነት ተስፋማርያም