አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ‹‹የዜግነት አገልግሎት አዋጅ›› በአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣትና የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማረጋገጥ አገራዊ ስሜትን ለማዳበር የጎላ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡ በክልሉ የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ዙሪያ ህዝባዊ መድረክ ተካሂዷል፡፡
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ዙሪያ ህዝባዊ መድረክ መካሄዱን አስታውሰዋል፡፡
የዜግነት አገልግሎት ዋና ዓላማው በሥነ ምግባር፣ በክህሎትና በስነ ልቦና የዜግነት ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ ትውልድን መቅረጽ ሲሆን፤ የህዝቦችን እኩልነትና የጋራ ልማት በማረጋገጥ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማስፋት አገራዊ ስሜትን ለማዳበርም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
አዋጁ የክልሉን ህዝብ በግልም ሆነ በተደራጀ መልኩ ነጻ አገልግሎት የመስጠት ሥራ ባህልን በማዳበር መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ አንድነትና መተሳሰቡን ያሰፋል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ የትውልድ ቅብብሎሽን ሥርዓት ባለው መልኩ ማስቀጠል፤ በሁሉም ነገር የለማችና የበለጸገች ኦሮሚያን መገንባትና በዚህ ውስጥም ዜጎችን በማሳተፍ ተጠቃሚ ማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ህዝቡ በገዳ ሥርዓት ያደበረውን ቱባ እሴት በመጠቀም በጉልበቱ፣ በሀብቱና በእውቀቱ በተለያዩ ዘርፎች ለክልሉ ልማት ነጻ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚጠቅም አስታውቀዋል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ በዜግነት አገልግሎት አዋጁ መነሻነት አገራዊ ለውጡን ሁለንተናዊ ለማድረግ የዜጎችን ተሳትፎ ከማጠናከር አኳያ በኦሮሚያ ክልል በሰፊው እየተሰራ ይገኛል፡፡
ሥራዎቹ ወጥ እንዲሆኑና ቀጣይነት እንዲኖራቸው በተለይም ደግሞ ትውልድን በማነጽ በኩል የገዳ ሥርዓት የሚያዛቸው እሴቶችና ህግጋቶችን ለማስጠበቅ፤ ከህጻናት እስከ አዋቂ ያሉት ዜጎች አገራዊ ስሜትን አዳብረው በሚሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራ ውስጥ የጎላ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ለውጦች ለመመዘን፤ ችግሮች ሲከሰቱ በሰለጠነና በሰከነ መንገድ በውይይትና በመግባባት ለመፍታት አዋጁ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ይህንን ሥርዓት ወደ መደበኛ የመንግስት ሥራ በማምጣት የዜጎችን ተሳትፎ በማጠናከር ሁለንተናዊ ለውጡን በድል የታጀበ የማድረግ ሥራም እየተሰራ ነው፡፡
የቢሮ ኃላፊው የዜግነት አገልግሎት አዋጁ የተለየ ፖለቲካዊ አንድምታ እንደሌለውና መርሆውም ወደ ነባር ‹‹የኦሮሙማ›› እሴቶች መመለስ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም አቃፊነትን፣ አብሮነትን፣ ኃላፊነት መስጠትን፣ ሥነ ምግባር ማነጽን በመደበኛው የአገልግሎት ሥርዓት ውስጥ ተከታታይነት ባለው መልኩ በማስቀጠል አገራዊ ለውጡን እውን የማድረግ አቅጣጫን የያዘ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አዋጁን መነሻ ያደረጉና በአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት በተለይም በወጣቱና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ የህዝቦችን እኩልነትና የጋራ ልማት በማረጋገጥ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊያረጋግጥ የሚችል ግንዛቤ የሚሰጡ ውይይቶች በሰፊው መካሄዳቸውንም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎት አዋጅ ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጠው ውይይት ላለፉት ሁለት ቀናት በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖችና ከተሞች ህዝባዊ መድረክ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ውይይቱ በቀጣይ በመላው የክልሉ አካባቢዎች እንደሚካሄድም ከክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
አዲሱ ገረመው