አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በ12 ሰዓታት ውስጥ 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል በህንድ የተያዘውን ክብረወሰን ለመስበር በምታደርገው ጥረት የእምነት ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋገጡ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኡስማን አደም ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ በእስልምና ሃይማኖት ዛፍ መትከል ትልቅ ክብር እና ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡
ዛፍ መትከል በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ግምትና ቦታ ያለው ብሎም እንደ ‹‹ጅሃድ›› አሊያም ለአንድ ነገር ትልቅ ሽልማት ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ የላቀ ትርጉም አለው፡፡ በዚህም መሠረት የእምነቱ ተከታዮች የጠቅላይ ሚኒትሩን ጥሪ ተቀብለው በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸው አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ እንዲጀመር ካሳሰቡበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስካሁን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በመስጂዶች በሙሉ ችግኞች እየተተከሉ ነው፤ የቀሩትም ጥቂት ስፍራዎች ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ60 ዓመት በፊት የነበረው ደን በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ በየዓመቱ ከአምስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ ለድርቅ እየተጋለጠ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ደን በመትከል ችግሩን መግታት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ መላው የእስልምና እምነት ተከታዮችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አግደው ረዴ በበኩላቸው፤ ቤተክርስቲያኗ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብላ ቀድም ብላ ወደ ተግባር መግባቷን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ያገኘችውን ጨምሮ 100 ሚሊዮን ብር ለዚሁ መርሐ ግብር መበጀቷ አስገንዝበዋል፡፡
በአብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትም ውስጥ በሰፊ የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያክን ጨምሮ ጳጳሳትና የሃይማኖት መሪዎች በሰፊው በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚሁም መሰረት መርሐ ግበሩ ይፋ ከተደረገበት ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በአካባቢው በሚገኙ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በመከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ይህ የሚጠናከር ሲሆን በችግኝ ተከላ የዓለም ክብረወሰን ለመስበር በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠው፤ ህዝቡም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ህንድ በ24 ሠዓታት ውስጥ 50 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል የዓለም ክብረወሰን ይዛለች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በ12 ሠዓታት ውስጥ 200 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ይህን ክብረወሰን ለመስበር ማቀዷ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር