አዲስ አበባ፡- የሲዳማ ወጣቶች ሀገር እንዳትረጋጋ ፍላጎት ካላቸው ሀይሎች ራሳቸውን በመጠበቅ የህዝበ ውሳኔውን ቀን በትዕግስት እንዲጠባበቁ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ /ሲአን/ ሊቀ መንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ አሳሰቡ፡፡
ሊቀመንበሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ አሁን ላይ በአንዳንድ የሲዳማ ዞን አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረስ ችግር መኖሩንና በአንዳንድ ቦታዎች የሰው ህይወት አልፏል፡፡ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና የምርጫ ቦርድ ስራቸውን በወቅቱ ሰርተው ተገቢውን ምላሽ በተጠበቀው ጊዜ አለማቅረባቸውና በጉዳዩ ላይ ህዝቡ በጥልቀት ሊወያይበት ባለመቻሉ ጉዳዩ እንዲባባስ አድርጎታል፡፡
የሲዳማ ህዝብ ከዚህ ቀደም ታግሶ እንደጠበቀ አሁንም በትዕግስት መጠበቅ እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ዱካሌ፤ በሰከነ መንፈስ በማሰብ እራሱን ማረጋጋት እንዲሁም ከግጭትና ሁከት ራሱን በመጠበቅ ወደማያስፈልግ ሁኔታ እንዳይገባ አሳስበዋል፡፡ የሲዳማ ህዝብ እራሱን ከግጭት ጠብቆ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚገባም ጠቁመው፤ ህዝቡም ለዘመናት አብሮት በቆየው ባህላዊ አስተዳደር እራሱን ማረጋጋት እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡
ወጣቶች በዚህ አጋጣሚ ሀገር እንዳትረጋጋ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች እንዳሉ አውቀውና ተረድተው በተረጋጋ መንፈስ በማስተዋል ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስ ቀድሞ እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም ተረጋግተው መጠበቅ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ በእልህ ተነስተው ምንም ማድረግ የለባቸውም ፤ መጎዳዳት በፍፁም አያስፈልግም ሲሉ አቶ ዱካሌ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
በተያያዘ ዜና ከትናንት በስቲያ በሀዋሳ ከተማና አካባቢው ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በግጭቱ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ትናንት ከተማዋ ላይ አንጻራዊ ሰላም እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ግጭቱ በታቦር ክፍለ ከተማ መንገድ በመዝጋት መጀመሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ ሲሆን በግጭቱ የደረሰው የጉዳት መጠን እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል።
የፀጥታ ችግሩ ከተማዋን መነሻ አድርጎ ወደ ሲዳማ ዞን ወረዳዎች መዛመቱን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ መንገዶች በመዘጋታቸው የጸጥታው ሀይል በፍጥነት መድረስ አለመቻሉን አስታውሰው፣ ነገር ግን አካባቢዎቹን የጸጥታ አካላት እያረጋጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል የህግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ ማቅረብ እንደሚኖርበት የጠቀሱት ኮሚሽነር ቴዎድሮስ፤ በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች ሰላም መሆኑን አስረድተዋል።
ህብረተሰቡም የሀዋሳ ከተማና አካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት ለማስጠበቅ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በቅንጅት እንዲሰራና አካባቢውን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ የሲዳማ ዞን የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የማደራጀት ጥያቄ ከክልሉ ምክር ቤት ለቦርዱ የደረሰው ህዳር 12/2011 ዓ.ም መሆኑና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47/3/ለ/ ለክልሉ የተሰጠው “ጥያቄው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ አመት” የሚለው የማደራጀት ጊዜ ገደብ በቦርዱም ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዚሁ መሰረትም በህገ መንግስቱ የተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በቀሩት አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔውን ለማከናወን የመጀመሪያ ደረጃ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በህገ መንግስቱና በምርጫ አዋጁ የተሰጠውን ሃላፊነት ዓለም አቀፍ የምርጫ መሰረታዊ መርሆዎች ጋር በማጣመር ሃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም መግለጹ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
ሃይማኖት ከበደ