አዲስ አበባ፡- ዜጎችን በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረፀውን የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ተግባራዊነቱን በተጨባጭ ለማረጋገጥ የሚያስችል የማህበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት ሊቋቋም መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ መንግስት በ1997ዓ.ም የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ለዜጎች በርካታ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተገንዝቦ በሁሉም ክልሎች የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ በማውጣት እንዲተገበር አድርጓል፡ ፡
በዘርፉ ካሉት የልማት አቅጣጫዎች መካከል የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃግብርን በመቅረፅ አብዛኞቹ የገጠር አካባቢዎችና 11 ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይሁንና ዜጎች እያደገ ከመጣው ኢኮኖሚ አኳያ ተመጠጣኝ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙና የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የሚያስላቸውን ስራ ወደ መሬት በማውረድ ረገድ ሰፊ ክፍተት ይታያል፡፡
«የማህበራዊ ጥበቃ ስራን ምንም እንኳ ሚኒስቴሩ እንዲያስተባብር ከመንግስት ሃላፊነት ቢሰጠውም ብሄራዊ ይዘት ያለውና በሁሉም የመንግስት ተቋማት ቅንጅት የሚሰራ ነው» ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ረገድ አብዛኞቹ ተቋማት ስራው የእነሱ ጭምር መሆኑን የማይገነዘቡ መሆኑን፤ ቢገነዘቡም ደግሞ ፋይናንስ መድቦ በእቅድ የመስራት ዝንባሌ የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ተቋማቱ የሚያከናውኑት ልማት ለዜጎች መሆኑን ተገንዝበው ቅድሚያ የዜጎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመታተር ችግር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
እንደ አቶ ፈለቀ ማብራሪያ፤ የሚገነቡት መሰረተ ልማቶችም ቢሆን ዜጎች በሚፈልጓቸው መጠን ካለመሆናቸውም ባሻገር የተሰሩትን ስራዎችም ሁሉንም ዜጋ በፍትሃዊነት ያለመከፋፈል ሁኔታ ይስተዋል፡፡
በተለይም ሴቶችን ህፃናትና አካል ጉዳተኞችን ማዕከል በማድረግ የሚሰሩ ስራዎች ወደ ሌላ አካል የመግፋት ዝንባሌ አለ፡ ፡ ያልሰሩትን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ሰፊ ክፍተት ይታያል፡፡ ይህም የመንግስት ወጪ የሚወጣባቸው ህንፃዎች ግንባታ ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን በዚህም ምክንያት የአካል ጉዳተኞችን እንቅስቃሴ ገድቧል፡፡
በመሆኑም ፖሊሲው በተጨባጭ እንዲተገበርና ዜጎችን የላቀ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻል ዘንድ የማህበራዊ ጥበቃ ምክር ቤት እንዲቋቋም በመንግስት መወሰኑን አቶ ፈለቀ አስገንዝበዋል፡፡
ምክር ቤቱ በመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች የሚመራ እንደመሆኑ እያንዳንዱ ተቋም ተቆጥሮ የተሰጠውን ሃላፊነት ስለመተግበሩ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አመልክተዋል፡፡« ምክር ቤቱ ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ የሁሉም ክልሎች አመራሮች የሚሣተፉበት በመሆኑ፣ ተቋማቱ አፈፃፀማቸው በየጊዜ እየተገመገመ የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይታሰባል» ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፤ በሚቀጥለው አመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ አመልክተው፤ ይህም ዘርፉ ህጋዊ ማዕቀፍ ባለው መልኩ እንዲመራና ለአገሪቱ እድገት አወንታዊ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011
ማህሌት አብዱል