•ህዝቡ በችግኝ ተከላ መርሐግብሩ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል
አዲስ አበባ፡– የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በክረምቱ በተያዘው ሀገራዊ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በሐምሌ 22 ቀን 2011 ለሚካሄደው ‹‹የአረንጓዴ አሻራ›› መርሐ ግብር 250 ሚሊዮን ጉድጓዶች መዘጋጀታቸው ተገለጸ። የክልሉ ህዝብን በመርሐ ግብሩ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል።
የኦሮሚያ ክልል የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ‹አረንጓዴ አሻራ› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ መርሐግብር አስመልክተው ትናንት በኢሊሌ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ክልሉ በራሱ ያስቀመጠውን ግብ ጨምሮ በፌዴራል መንግሥት
ከተሰጠው126 ሚሊዮን ችግኝ ጋር ወደ ሦስት መቶ ሚሊዮን የተለያየ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ለመትከልና በሰውም 65 ችግኞች እንዲተከሉ ቅድመ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ለዚህም አስከአሁን 250 ሚሊዮን ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ለችግኝ ተከላ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እና ለውሎውም የሚመገበውንም ይዞ በመውጣት በመርሐግብሩ ላይ እንዲ ሳተፍ የቢሮ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ ዳባ እንዳሉት፣ የችግኝ ተከላ መርሐግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ እስከ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኙ በምሥራቅ ሸዋ፣ደቡብ ምሥራቅ ሸዋ፣ኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ሰሜን ሸዋን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሚከናወን ሲሆን፣ ተከላ የሚከናወንባቸው ከአንድ ሺ 900 በላይ ቦታዎችም በአየር ካርታ ተለይተዋል፡፡
በሁለቱ የክረምት ወራት ጊዜ ውስጥ በሀገር አቀፍ ከተያዘው አራት ቢሊየን የችግኝ ተከላ መርሐግብር ውስጥ በክልሉ ሁለት ቢሊዮን እንደሚከናወን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፣ እስከአሁን አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውንና የተቀረውን በግዥና በተለያየ መንገድ በማሟላት እቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ክረምቱ ከገባም ጀምሮ እስከአሁን ወደ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የቢሮው ምክትል እና የተፈጥሮ ሀብት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈራ በበኩላቸው በአጠቃላይ በክልሉ ለሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐግብር ችግኝ ከማጽደቅ እስከ ተከላው ድረስ ወጪው በገንዘብ እስከ አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚገመትና ከዚህ ውስጥም 60 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ተሳትፎ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አቶ እንዳልካቸው እንዳሉት ከዚህ ቀደም በክልሉ በተከናወኑት የችግኝ ተከላ መርሐግብሮች ያለፉት አራት ዓመታት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የችግኞች የመጽደቅ መጠን 58 በመቶ ላይ ይገኛል። በጋራ ከሚተከለው ችግኝም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የተሻለ መሆኑም ተረጋግጧል። በጋራ በሚተከለው ላይ ዓላማውን ካለመገንዘብና የባለቤትነት መንፈስ ላይ የታየውን ክፍተት በመለየት እንዳይደገም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የክልሉ የደን ሽፋንም ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው ሦስት በመቶ ወደ 15 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ አሁን በሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሐግብር 25 በመቶ እና ከዚያ በላይ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ አቶ እንዳልካቸው ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
ለምለም መንግሥቱ