የጋራ እሴቶቻችንን በማጠናከርና መቻቻልን መርሁ ያደረገ ኢትዮጵያዊነት ማጎልበት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የፀጥታ ችግር መፍትሄ እንደሆነ ትናንት በአዲስ አበባ በተከበረው 13ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ይገልፃሉ፡፡
ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ባህላዊ ትርኢቶች የተከበረው የዘንድሮ በዓል የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠንከር ጉልህ ሚና እንደነበረውና ብዙ የባህል ልምድ ልውውጥ የተካሄደበት መሆኑም የበዓሉ ታዳሚዎች ያመለክታሉ፡፡
ወጣት ከተማ ፈዮ የኮሌጅ ተማሪ ሲሆን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጣ ነው። «በበዓሉ ላይ በመታደሜ የሌሎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል የበለጠ እንዳውቅ አድርጎኛል» በማለት ክብረ በዓሉ ያስገኘለትን በጎ ነገር ይገልጻል፡፡
«እኛ ኢትዮጵያውያን በባህል የታደልን ህዝቦች ነን›› የሚለው ተማሪ ከተማ፣እነዚህ በጎ ባህሎቻችን እርስ በርስ በመዋዋስ እና በመጠቀም ግንኙነታችን ማጠንከር እንችላለን ይላል፡፡ በተዋበ ባህላዊ ልብስ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኘው ተማሪ ከተማ የብዙ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር መሆን ከሁሉም ጠቃሚ ልምዶችና ባህሎችን በመውሰድ ለማህበረሰባዊ ለውጥ መጠቀም እንደሚቻል ያስረዳል፡፡
የበዓሉ መከበር ጠቀሜታ ሲያስረዳ፣«እዚህ በቆየሁባቸው ቀናት ብዙ ጓደኞችን አፍርቻለሁ፡፡ እኔ ከመጣሁበት ብሄረሰብ ውጭ ከመጡ ጋር ጥሩ መግባባትን ፈጥሬ ወደ እነሱ እንድሄድ ጋብዘውኛል፤ እኔም ጋብዣቸዋለሁ፡፡ ይሄም የእርስ በርስ ግንኙነታችን አጠንክሮልናል» በማለት ያስረዳል፡፡
ኢሳያስ መለሰ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነው። «በዓሉን በዚህ መልኩ በጋራ ማክበር ትክክለኛውን ትውፊት ለማሳየት ትልቅ አጋጣሚ ይፈጥራል» በማለት ጠቀሜታን ይገልጻል፡፡ በዚህ መልክ ባህላችንን ይዘን ቀርበን በጋራ ስንቆም ውበታችን ይጎላል፤ በማለት ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን በራሱ የተለየ ውበት መሆኑን ያስረዳል። ኢሳያስ በሀገሪቱ እየታየ ያለው ዘርፈ ብዙ ለውጥ የሚበረታታ መሆኑንና ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት ለለውጡ ዳር መድረስ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል ይላል፡፡
ወይዘሮ የሺ ታመነ ከሀረርጌ አካባቢ በዓሉን ለመታደም የመጡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች እየታየ ያለው የፀጥታ ችግር በማስመልከት ማህበረሰቡም የራሱን ሰላም በመጠበቁ በኩል ድርሻ ሊወስድ ይገባል ይላሉ፡፡
የበዓሉ ተሳታፊዎች ሰላም የለውጥ መሰረት መሆኑን ማሳወቅ የሚገባ መሆኑን ያስረዳሉ። «እዚህ የተገኘነው ከተለያየ ማህበረሰብ እንደመሆኑ ለመጣንበት ማህበረሰብ ወካይ ነንና የማህበረሰባችን ጥሩ ገፅታ አጉልተን ማሳየት አለብን። የበዓሉ አላማም የእርስ በርስ ትስስራችንን ማጠንከር ነው» ይላሉ።
«በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የሚታየው የፀጥታ ችግር ለማስቆምና ሰላም ለማስፈን የሁላችንም ተሳትፎ ወሳኝ ነው።» የሚሉት ወይዘሮ የሺ፤ ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን ነቅቶ መጠበቅ ይገባል ይላሉ፡፡ ወጣቱ ያለ ምክንያት ምንም ነገር ከማድረግ እንዲቆጠብና ሁሌም ምክንያታዊ ሊሆን ይገባል የሚል ምክርም አላቸው፡፡
ድምፃዊ አብረሃም አበበ ከደቡብ ክልል ከከንባታና ጠምባሮ ዞን የመጣ ነው፡፡ኢትዮጵያውያን በጋራ በአንድ አላማ በጋራ ስንቆም ያምርብናል፤ አንድነታችንም ከልዩነታችን ከፍ ያለ መሆኑን ይገልፃል። ሀገራችን በለውጥ ሂደት ላይ በሆነችበትና እኛም ጥሩ ተስፋ በሰነቅንበት ወቅት መከበሩ በዓሉ ልዩ ድባብ እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ ስለዚህም ማህበረሰቡ ለውጡ የፈጠረለትን መልካም ዕድል ተጠቅሞ ሀገራዊ ዕድገትና ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ይላል፡፡
ሰላምን ለማስጠበቅ ዋነኛ ድርሻ መውሰድ የሚገባው ህብረተሰቡ መሆኑን የሚናገረው ድምጻዊ አብረሃም፤ ለሰላሙ መጠበቅ ከሚሰሩ የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ መቆም የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡
ማህበረሰቡም ችግሮችን ለማቃለል መነጋገርና ውይይትን ባህሉ ሊያደርግ ይገባል የሚለው ድምፃዊ አብረሃም፤ በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም ይላል። «አንዱ ብሄረሰብ የሌላውን ብሄረሰብ ባህል ወግ በማክበር፣ በመጠበቅ፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠንከርና መቻቻልን መርህ በማድረግ አንድ ጠንካራ ሀገር መገንባት ወሳኝ ነው በማለት የሀገራዊ አንድነት ፋይዳውን ይጠቁማል።
ወጣት መህቡባ ከአፋር ክልል የመጣች የበዓሉ ታዳሚ ናት፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰሙ ወሬዎችና አንዳንድ አሉታዊ አስተሳሰቦች የዚህ በዓል ተሳታፊ በመሆኑ ከሌሎች የብሄረሰብ ተወካዮች ጋር በነበረኝ ቆይታ ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንዲኖረኝ አድርጎኛል ትላለች፡፡
«ኢትዮጵያዊነት ድምቀት ነው» በማለት ኢትዮጵያዊነት የህብር ቀለማት ጥምረት፤ የመቻቻል ማሳያ መሆኑን ትናገራለች፡፡ በጋራ በመቆም ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችንን ማቃለል እንደሚቻል ትገልጻለች፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2011
ተገኝ ብሩ