–በማስፋፊያው ቦታ ላይ ህገ ወጥ ግንባታዎች እየተካሄዱ ናቸው
አዲስ አበባ፡– በ2010ዓ.ም ከፈረንሳይ የል ማት ድርጅት ተቋም በተገኘ የ70 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ይሰራል የተባለው የቄራዎች ማስፋፊያና ማዘመኛ ፕሮጀክት እስካሁን ሥራ አለመጀመሩ ታወቀ። ለማስፋፊያና ማዘመኛ ተብሎ በታሰበው ሥፍራ ላይም ህገ ወጥ ግለሰቦች እየሰፈሩ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የቄራዎች ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ድርብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የተቋሙን የማስፋፊያና ማዘመኛ ፕሮጀክት ለማከናወን በ2010ዓ.ም ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት ተቋም የ70 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ስምምነት ቢደረግም፤ ከተነሺዎችና ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር በነበረው ማነቆ ሥራው ዘግይቷል። ከዚህ ቀደም ህገ ወጥ ናቸው ተብለው የተነሱ በርካታ ግለሰቦችም በማስፋፊያ ቦታው ላይ ዳግም ሰፍረዋል፡፡
ሥራውን ለመጀመር አማካሪ ያስፈልግ ነበር ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ከአማካሪ ጋር በተያያዘ በ2010ዓ.ም ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ በርካታ ተቋማት ተወዳድረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ሦስት ተቋማት ለመጨ ረሻው የጨረታ ውድድር መድረስ እንደቻሉ አስታወሰው፤ ይህም ሲደረግ በቴክኒካል መለኪያ 70 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጣው አንድ ተቋም ብቻ ሆኖ በመገኘቱ ከተጫራቹ ተቋም ጋርም ወደ ውል ለመግባት ሲታሰብ ከግብር ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሰጣ ገባ ችግር ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በወቅቱ ጨረ ታውን ያሸነፈው ተቋም በአገሪቷ የግብር ጉዳይ ላይ ብዙ መረጃ አልነበረውም፡፡ የኮንትራት ሂደቱን መፈራረም ሲጀመር ግብሮችን ለመክፈል ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ‹‹ቄራዎች ድርጅት ራሱ ይክፈል›› የሚል አቋም ስለነበረው ከገቢዎች ጋር ምክክር ሲደረግ ቄራዎች ክፍያውን የሚያካሂድበት የህግ መሠረት አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡
በወቅቱ ከተቋሙ ጋር ድርድር በማድረግ ሀሳቡን ለማስቀየር ቢሞከርም ፍቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ ጨረታው ውድቅ እንዲሆንና ሁለተኛ ጨረታ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በዚህ አግባብ በ2011ዓ.ም ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ አሁን ላይ የጨረታ ግምገማው አልቆ ጫፍ ላይ ተደርሷል፡፡ የቀረው የስራ አመራር ቦርድ ውሳኔ ብቻ ነው፡፡
በማስፋፊያ ቦታው ላይ እስከ 55 የሚደርሱ ህጋዊ ባለ ይዞታ የሆኑ ተነሺዎች መኖራቸው ሁለተኛውና መሠረታዊ ማነቆ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ በከተማው ውስጥ የሚመለከተው ሴክተር መስሪያ ቤት ግለሰቦቹን ለማስነሳት ጊዜ እንወሰደበትና ይህም በተለይ በአገሪቷ ከተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተከሰተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አክለውም በርካታ ሰዎች ቀደም ሲል ቦታው ላይ የነበሩና ህገ ወጥ ተብለው ከቦታው ላይ እንዲነሱ የተደረጉ ቢሆንም፤ ግለሰቦቹ ጊዜ ጠብቀው ምቹ ሁኔታ ሲያገኙ ቦታው ላይ መስፈራቸውንና በአሁኑ ወቅትም ህጋዊ ብቻ ሳይሆኑ ህገ ወጦችም በቦታው ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
የአማካሪው ጉዳይ እያለቀ በመሆኑ ችግሩ እንደሚፈታ ተስፋ ቢሰነቅም ፕሮጀክቱን ለመጀ መር የተቆረጠለት ቀን አለመኖሩን፤ ለዚህም ትልቅ ፈተና የሆነው በቦታው ላይ ያሉት ህጋዊም ሆኑ ህገ ወጥ ግለሰቦችን ከቦታው መቼ ይነሳሉ የሚለው ጉዳይ መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
ገንዘቡን ያበደረው ተቋም ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጋር ውይይት ማድረጉን የጠቆሙት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በቦታው ላይ ያሉትን በስድሰት ወራት ውስጥ እንደሚያስነሳ ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ከሆነ አማካሪው ወደ ሥራ መግባት እንደሚችል ጠቅሰው ሥራውም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የቄራዎች ድርጅት ማስፋፊያና ማዘመኛሥራው ይከናወናል የተባለው ሃና ማርያም በተለምዶ ቀርሳ ኮንቲማ የሚባል አካባቢ ሲሆን፤ ሥራው በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጠናቆ በሙከራ ደረጃ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ መታቀዱ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
አዲሱ ገረመው