ባህር ዳር፦ የአማራ የሱማሌ ክልሎች ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ከዛሬ (ሀምሌ 12/2011 ዓ.ም) ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በባህዳር ከተማ እንደሚካሄድ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ አሰመኸኝ አስረስ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የሚመራ ኡስታዞችን፣ የጎሳ መሪዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ያካተተው የልዑካን ቡድን ወደ ባህር ዳር ገብቷል፡፡
የአማራ ክልል ህዝብ ተወካዮች በሚገኙበት የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክሩ የተለያዩ ውይይቶችና ጉብኝቶች ይካሄዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አሰመኸኝ ገልጸዋል፡፡
‹‹የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች አብሮነት ታሪካዊ ነው›› ያሉት አቶ አሰመኸኝ፤ ሁለቱ ህዝቦች የአገር ሉዓላዊነት ለማስከበር በተደረጉ ትግሎች በጋራ መሰወታቸውን አንስተዋል፡፡ ሁለቱ ህዝቦች የተዋለዱ መሆናቸውንም አንስተው.፤ የህዝቡ አብሮነት የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አሰመኸኝ ማብራሪያ፤ የአማራ ክልል ከአጎራባች ህዝቦች ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የተለያዩ መድረኮችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም እንደገለጹት፤ ሀምሌ 15 የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤውን ይጀምራል፡፡ በጉባኤው የተለያዩ አጀንዳዎች ተቀርጸው ውይይት ይደረጋል፡፡ ከአጀንዳዎቹ መካከል የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ሹመት መርምሮ ያፀድቃል፡፡ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት በዓለ ሲመት ይካሄዳል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
መላኩ ኤሮሴ