አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባላት ከዚህ ባለፉት ዓመታት በያዙት አቋምና በሚያራምዱት ሃሳብ በድርጅት ይገመገሙ እንደነበር፤ አሁን ግን የሚገመገሙበት ሁኔታ አለመኖሩን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ገለጹ፡፡
አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቀደም ሲል አዋጅ አናፀድቅም ካሉ በማግስቱ ግምገማ ይካሄድባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም በሁለተኛው ቀን አዋጁ ወደ ምክር ቤቱ ይመጣና በሙሉ ድምፅ ይፀድቃል። በዚህ ሂደትም በተደጋጋሚ ያለመከሰስ መብት ይነሳ ሲባል አባላቱ አናምንበትም ብለው ከራክረው ጥለው ሲወጡ ቀን ግምገማ ይካሄድና ሳያምኑበት በቀጣዩ ቀን በሙሉ ድምፅ ይፀድ ቃል፡፡
‹‹ድምፅ ያልሰጡ የተቃወሙ እና የተለየ ሃሳብ ያራመዱ ሰዎች በግምገማ ተዋክበው ለቀጣይ ምርጫ መቅረብ የሚችሉ ሰዎች ምርጫ ውስጥ እንዳይገቡ ይደረጋል፡፡›› ያሉት አቶ ታገሰ፤ ከምክር ቤት ወጥተው የመንግሥት ሥራ ሲገቡ ብዙ መጉላላት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት ግምገማው ከኑሯቸው ጋር የተገናኘ በመሆኑ ህሊናቸው የሚያዛቸውን ሳያደርጉ ተገድበው መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በሚወስደው አቋምም ሆነ በሚያራምደው ሃሳብ የሚጠየቅበት ሁኔታ አለመኖሩን በማሳወቅ፤ ህገመንግሥቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት አባላቶች ህሊናቸው እንዳዘዛቸው እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ በዚህም በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ብቻ ሳይሆን በአብላጫ ድምፅ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ሁኔታ መፈጠሩን እና የተሻለ ለውጥ መመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
ምህረት ሞገስ