ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላም

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የሰላም መንገድን በመረጡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች መካከል የሰላም ስምምነት መደረጉ ይታወሳል።በዚህ መሠረትም በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የሠራዊቱ አባላት ወደ ተዘጋጁላቸው ማዕከላት እየገቡ ይገኛል።ታዲያ በክልሉ ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላም ግንባታ መምጣት የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ 40ኛው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ክልሉን ከግጭት አዙሪት ለማውጣትና የጥይት ድምጽ የማይሰማበት ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ።

በኦሮሚያ ምድር ላይ የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ፣ የክልሉ ሕዝብ ሰላም ለሁሉም እንደሚያስፈልግ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን አውስተው፤ የአመለካከት ልዩነቶችን በቀደምት እውቀቶችና በምክክር መፍታት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

በግጭቶች ሳቢያ በርካቶች ተፈናቅለዋልና ሀብት ንብረታቸው መውደሙን ይናገራሉ።በዚህ ምክንያትም ጦርነት አክሳሪ እንጂ አማራጭ መሆን እንደማይችል መረዳት ተችሏል ይላሉ።የኦሮሞ ሕዝብ ጦርነት ይበቃናል ታረቁ በማለት ማረሻና ቀንበር በመያዝ

ይቅርታን ለምኗል ያሉት ኃላፊው፤ በአሁኑ ጊዜ የኦሮሚያ ክልልን ከግጭት ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ።

ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጠንካራ ቁርጠኝነት፣ከግልና ከቡድን ፍላጎት ወደ ሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ መሸጋገር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ ለዚህም ሂደት ጦርነትን ማቆም፣የቀድሞ ታጣቂዎችን ተሀድሶ በመስጠት ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀል፣የማህበራዊ ኑሮ ስብራትን በምህረትና በይቅርታ መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

የቀደምት እውቀቶቻችን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ስብራቶቻችንን ለመጠገን የሚያስችሉ ናቸው ያሉት አቶ ኃይሉ፤ የጦርነት ምዕራፍን በምህረትና በይቅርታ ለመዝጋት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ፍትሐዊነትን ለማስፈን፣ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበርና እኩልነትን ለማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኦሮሚያ የተጀመረው የሰላም መንገድ አዲስ ምዕራፍ መክፈት መቻሉን ነው የገለጹት።

የኦሮሞን ሕዝብ ሰላም ማረጋገጥ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ የበለጸገችና ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት መሆኑን ይናገራሉ።

የሰላም ስምምነቱ በክልሉ ቀጣይነት ያለው ሰላምን ለማረጋገጥና የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት መሠረት የሚጥል መሆኑን በመግለጽ፤ እሴቶችን በመጠቀም ማህበራዊ ስብራቶችን በይቅርታ ለማከም መሥራት የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም ክልሉን ከግጭት አዙሪት ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሕዝብ እየተመኘ ያለውን ዘላቂ ሰላም በማምጣት ወደ ልማት መሸጋገርና የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ያሉት ደግሞ በውይይቱ ላይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ደበላ ፊጡማ ናቸው።

ሕዝብ ተረጋግቶ፣ መንግሥት ወደ መደበኛ ሥራው ተመልሶ ልማትን ማረጋገጥ የሚቻለው ዘላቂ ሰላም ሲኖር ነው ያሉት አቶ ደበላ፤ ዘላቂ ሰላምን በማምጣት ወደ ልማት ለመሸጋገር የትጥቅ ማስፈታ እና መልሶ ማቋቋም ተግባር ወሳኝ ነው ይላሉ።

ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ፖለቲካዊ፣ወታደራዊ፣ሰላምና ጸጥታን ጨምሮ፣የሰብዓዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ጦርነት ተመልሶ እንዳይመጣ መፍትሔ የሚሆን መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰላም፣ ጸጥታ ፣ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ነው የገለጹት።

በመንግሥትና ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጣቂዎች ጋር ፖለቲካዊ መተማመን እንዲኖር ለማድረግ ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፤ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማምጣትና ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላም ሕዝብ የተረጋጋ ህይወት እንዲኖረው በር እንደሚከፍትና መንግሥትም ለመደበኛ ሥራዎቹ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም በሰላማዊ መንገድ ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ እንዲመሩ ያስችላል ነው ያሉት።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You