አዲስ አበባ፡- በተያዘው በጀት ዓመት ከአስር ላኪዎች ብቻ 110 ቶን ቡና መቀሸቡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ኡመር በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ለባለስልጣኑ ከላኪዎች በደረሰው መረጃ መሰረት ከመነሻው ተረጋግጦ ወደ ውጭ ከተላከው ቡና 110 ቶን የደረሰበት ሳይታወቅ ጎድሎ ተገኝቷል።
ጉድለቱ በቅሸባ ተውስዶ እንደሆነ ይገመታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም የሚፈጸመው በሚጓጓዝበት ወቅት ሲሆን አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደብ ላይ ሊሆን ይችላል የሚልም ጥርጣሬ መኖሩን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ በባለ ስልጣኑ በኩል መረጃው ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ ከፌ ዴራል ፖሊስ ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም በመግለጽ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከጉምሩክ ከጸጥታ ክፍል ሠራተኞችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ በበኩላቸው በቡና ቅሸባ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ከሁለት ሚሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ ገጥሟል ተብሎ እንደሚገመት በመጠቆም ጉድለቱ በቀጥታ የውጭ ምንዛሬ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥር እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ ቡናው ወጪ ከደረሰ በኋላ ጎድሎ ሲገኝ ላኪዎቹ እንዲከፍሉ ይደረጋል። የሚከፈለው ደግሞ በዶላር በመሆኑ ለላኪዎች የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ሌላ ችግር ሆኗል። ቢያገኙ እንኳ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ እየተባለ ባለበት ወቅት ይህን ያህል ገንዘብ በዶላር መከፈል በአገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ዛሬም ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያን ቡና ከአውሮፓ የሚገዙ የአሜሪካና የቻይና ኩባንያዎች አሉ። የሚሉት ሥራ እስኪያጁ ይህን የሚያደርጉት ራሱን ቡናውን ከኢትዮጵያ ለመግዛት እምነት በማጣት ነው። በመሆነም መንግሥት አስፈላጊውን ክትትልና ዕርምጃ በመውሰድ ማስተካከል ካልቻለ የቡናው ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ሚና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ