አዲስ አበባ፡– በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 12 ሺህ 200 ሰዎች ከኤች አይቪ ኤድስ ጋር እንደሚኖሩ ሳያውቁ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት በጥናት መረጋገጡን የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አስታወቀ። ሆስፒታሉ ከቻይና መንግሥት በ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በስጦታ ተበርክቶለታል፡፡
የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ጂብሪል አባስ ትናንት ሆስፒታሉ ከቻይና መንግሥት የህክምና ቁሳቁስ ስጦታ በተበረከተለት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ ምጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ከተስፋፉባቸው ከተሞች ውስጥ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ 3 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎቿ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ከተያዙት ውስጥ 12 ሺህ ያህሉ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ እንደማያውቁም ናሙና ተወስዶ በጥናት መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ሆስፒታሉ ከቻይና መንግሥት በ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በስጦታ የተበረከቱለት ሲሆን፤ እንደ ዶክተር ጂብሪል ገለጻ፤ የህክምና ቁሳቁስ ስጦታው የኢትዮጵያና ቻይና መንግሥታትን 45 ዓመታት የህክምና ግንኙነት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የተከናወነ ነው፡፡
ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ የቻይና መንግሥት የህክምና ልዑኮችን ወደ ኢትዮጵያ ሲልክ የቆየ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም 21ኛው ልዑክ ወደ ሆስፒታሉ መጥቷል ብለዋል፡፡ ስፔሺያሊስቶቹ በሆስፒታሉ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ መሆ ናቸውን የገለጹት ዶክተር ጂብሪል፤ እያንዳንዱ ስፔሺያሊስት የልብ፣የነርቭ፣ የሕፃናት እንዲሁም የሰመመን ህክምና ሆስፒታላቸው ውስጥ አገል ግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ጂብሪል እንዳሉት፤ የህክምና ልዑካን ቡድኑ በየዓመቱ የሚመጡ ሲሆኑ፤ እነሱ ሲሄዱ ደግሞ ሌሎች በመምጣት የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
ዳግማዊት ግርማ