•78 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም ዘዴ በዘር ተሸፍኗል
ደሴ፡– በአማራ ብሄራዊ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በመኸር እርሻ 461 ሺ 662 ሄክታር በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ 78 ሺህ ሄክታር ማሳ በኩታገጠም ዘዴ በዘር መሸፈኑን አመልክቷል፡፡
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ እንደገለጹት፤ በዞኑ 461 ሺ 662 ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 148 ሺ ሄክታር ማሳ በዋና ዋና ሰብሎች በኩታ ገጠም ዘዴ ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን፤ እስከ ሐምሌ 10 ድረስ በዘር ከተሸፈነው 200 ሺ ሄክታር ማሳ ውስጥ 78 ሺ ሄክታሩ በኩታ ገጠም ዘዴ በዘር ተሸፍኗል፡፡
ግቡን ለማሳካት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበር የተናገሩት አቶ ታደሰ፤ አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም/ክላስተር/ የማደራጀት፤ በየደረጃው ካሉ ፈጻሚ አካላት ጋር የመግባባት፤ ለአርሶ አደሮች፣ ለአመራሮችና ለባለሙያዎች ስልጠና የመስጠት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በጊዜው የማቅረብ ተግባርም ተከናውኗል፡፡
እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ፤ በዞኑ በዘር ይሸፈናል ተብሎ ከታቀደው ማሳ ውስጥ 98 በመቶው አንድ ዙር ታርሷል፤ 86 በመቶ ደግሞ ሁለት ዙር ታርሷል፡፡ 58 በመቶው ደግሞ ሦስት ዙር ታርሷል፡፡
ከግብዓት አንጻር ደግሞ 344 ሺ 898 ኩንታል ሁለቱም ዩሪያና ዳፒ ማዳበሪያዎች ዞን የደረሰ ሲሆን፤ ከደሴ ወደ ሁሉም ወረዳዎች የማድረስ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ 332 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ከዞን ለህብረት ሥራ ማህበራት የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 300 ሺ ኩንታል ደግሞ በአርሶ አደሮች እጅ ላይ ገብቷል፡፡
13 ሺ ኩንታል የሚሆን የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎና የቢራ ገብስ ምርጥ ዘሮች ዞን የደረሰ መሆኑንና ከዚህ ስምንት ሺህ ኩንታል ገደማ ምርጥ ዘር በአርሶ አደሮች እጅ ላይ መግባቱን የተናገሩት አቶ ታደሰ፣ በመንግሥት የሚቀርበው ምርጥ ዘር ብቻ በቂ ባለመሆኑ 86 ሺ 98 ኩንታል የሚሆን ምርጥ ዘር አርሶ አደሩ እርስ በእርስ እንዲለዋወጥ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ የ011 ቀበሌ የኩትር ጎጥ አርሶ አደር አቶ መሃመድ አበበ እንደተናገሩት፤ ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ማሳቸውን በማቀናጀት ኩታ ገጠም እርሻ ሲተገብሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ኩታ ገጠም አስተራረስ ከመጀመራቸው በፊት ሰብሎች በጋራ ስለሚዘሩ አንዱ የሌላውን ማዕድን በመሻማት ምርታማነት እንዲቀንስ ሲያደርግ ነበር የሚሉት አቶ መሃመድ፤ ኩታ ገጠም ግን ምርታማነት እንዲጨምር ከማስቻሉም ባሻገር አንዱ ሰብል ከሌላው ጋር በመቀላቀል ይፈጠር የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ መሐመድ ማብራሪያ፤ አንዳንድ ሰብሎች ቀድመው ሲደርሱ ከእህል መሐል ለማውጣት አዳጋች ይሆን ነበር፡፡ ቀድሞ የደረሰውን ሰብሎ ለመሰብሰብ በሰብሎች መካከል መመላለስ የሰብል ብክነትና እንዲከሰት ሲያደርግ ነበር፡፡ ኩታ ገጠም እርሻ ከተጀመረ ወዲህ ግን የአካባቢው አርሶ አደሮች በጋራ ስለሚዘራ፣ ስለሚታረም፣ ስለሚወቃ እና ለገበያ ለማቅረብ ስለሚያስችል ተመራጭ አድርገውታል፡፡
በ2010/11 የእርሻ ዘመን ከ32 አርሶ አደሮች ጋር ማሳቸውን በማቀናጀት 32ቱ አርሶ አደሮች 32 ሄክታር ላይ ገብስ ዘርተው በሄክታር 45 ኩንታል ገብስ ማምረትም ችለዋል፡፡ ከ32 አርሶ አደሮች ጋር በክላስተር በመደራጀት ዘንድሮም በ32 ሄክታር ማሳ ላይ ሙሉ ፓኬጅ በመጠቀም በክላስተር ሰንዴ ዘርተዋል፡፡
ሌላኛው የለጋምቦ ወረዳ የ011 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሳ መኮንን እንደሚሉት ከ15 አርሶ አደሮች ጋር ማሳቸውን በማቀናጀት ባለፈው ዓመት ስንዴ በዘሩበት ማሳ ላይ ዘንድሮም በኩታ ገጠም ገብስ ዘርተዋል፡፡ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ አራት ጊዜ በማረስ ማሳቸውን ሲያዘጋጁ በነበረው አንድ ሄክታር ማሳ ላይ 1 ኩንታል ዩሪያና ዳፕ ተጠቅመው በመስመር ዘርተዋል፡፡
በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ካሳ፤ እቅዳቸውን ለማሳካት ከባለሙያዎች የተሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦችን በሙሉ ተግባራዊ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በ2010/2011 የምርት ዘመን 10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን በ2011/12 የምርት ዘመን የምርት መጠኑን በ23 በመቶ በማሳደግ 12 ነጥብ ሁለት ሚሊየን ኩንታል ለማምረት መታቀዱን ከዞኑ የግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
መላኩ ኤሮሴ