«የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ፍትሐዊነት በማስፈን አሳታፊና አካታች ሥርዓት እንዲኖር አስችሏል»- ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ

– ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ– የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በፌዴራል ተቋማት ስለሚከናወኑ ግዥዎችና የንብረት አስተዳደር ሥራዎች ዘመናዊ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣትም ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋት ላይ ነው ፡፡

በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት (ኢጂፒ) እና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት (ኢፊሊት ማኔጅመንት) የተሰኙ ሥርዓቶች/ ሲስተሞች አጎልብቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሥርዓቶቹ ዙሪያ ከባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ አያኖ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ እና የንብረት አስተዳደር ለማዘመን ምን እየተሠራ ነው ?

ወይዘሮ መሠረት፡– ባለሥልጣኑ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት (ኢጂፒ)እና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት (ኢፊሊት ማኔጀመንት) የተሰኙ ሲስተሞች በመተግበር ላይ ነው፡፡

የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት 2014 ዓ.ም በዘጠኝ ተቋማት ተጀምሮ፤ አሁን ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ተግባራዊ ተደርጎ፤ ወደ ክልሎች እየወረደ ነው፡፡ ይህም 270 የፌዴራል ተቋማት እና 65 ቅርንጫፎቻቸውን ይጨምራል ፤ ሁሉንም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያካትት ነው፡፡

ሲስተሙ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በየክልሎች ያሉ ነጋዴዎች በፌዴራል የግዥ ሥርዓት ላይ እኩል እንዲሳተፉ እድል የሰጠ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከ80ሺ በላይ የንግድ ፍቃዶች ያላቸው ከ22ሺ በላይ አቅራቢዎች በዚህ ሥርዓት ላይ ተመዝግበዋል፡፡

የኢፊሊት ማኔጅመንት ሥርዓት የምንለው ደግሞ ንብረትን የተመለከተ ነው፡፡ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች በመመዝገብ ለማወቅና ለማስተዳደር፤ የነዳጅ አጠቃቀምን ለመጠየቅ፣ ለመቀበል፤ ለመወሰን እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች የት ናቸው የሚሉትን ጉዳዮች ለማወቅና ለማስተዳደር የሚያስችል ነው፡፡ ሥርዓቱ የምዝገባ፣ ስምሪትና የነዳጅ አጠቃቀም ሁኔታ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሲስተሙ ለምቶ በ13 የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተጠናቅቆ የሙከራ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ለሁሉም የፌዴራል ተቋማት ተደራሽ በሚሆን ጊዜ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ምን ያህል ተሽከርካሪዎች አሉን? ምን ያህል ነዳጅ እንጠቀማለን? መኪናዎቻችንስ ዛሬ የት በምን ሁኔታ ናቸው ያሉት የሚሉትን እያንዳንዱን መሥሪያ ቤት በደንብ አውቆ ሀብቱን እንዲጠቀምበትና እንዲያስተዳድር የሚያስችል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የእነዚህ ሲስተሞች መኖር ያስገኟቸው ጠቀሜታዎች ምንድናቸው ?

ወይዘሮ መሠረት፡– ዘመናዊ የመንግሥት ግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት መኖሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ግልጸኝነት፣ ተወዳዳሪነትና ፍትሐዊነትን ማስፈን ነው፡፡ የግልጸኝነት ሥርዓት እንዲኖር፣ ፍትሐዊ የሆነ የውድድር ምህዳር እንዲሰፍን ፣ ሁሉንም አሳታፊና አካታች የሆነ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት እንዲኖር በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል፡፡

ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ጨረታ ቢያወጣ ሁሉም ሲስተሙ ውስጥ ያሉ አቅራቢዎች ወዲያውኑ ማየት ይችላሉ፡፡ ፍላጎቱ ካላቸውም መወዳደር ይችላሉ፡፡ በዚህም ግልጸኝነትና ተደራሽነት መፍጠር ተችሏል፡፡

አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የፌዴራል ተቋም የሚያወጣውን የግዥ ጨረታ ዶክመንት ለመግዛት በትራንስፖርት መጓጓዝን አይጠይቅም፡፡ ባለበት ቦታ ሆኖ ላፕ ቶፕ ሆነ ዲስክ ቶፕ ኮምፒዩተር በመጠቀም ለመወዳደር ማመልከት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ተደራሽነት በከፍተኛ ደረጃ ያሰፋል፤ በሰኮንዶች ውስጥ ሁሉም ዘንድ መድረስ ያስችላል፡፡

ሌላው ደግሞ ፍትሐዊ ነው፡፡ አቅም ያለው፣ ሩቅ ያለ፣ ቅርብ ያለ የሚል ገደብ ሳይኖረው ሁሉም በአንድ ጊዜ መሳተፍ ያስችላል፡፡ ይህም በርካታ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በፌዴራል የግዥ ሥርዓት ተሳትፎአቸው እንዲያድግ አድርጓል።

ለምሳሌ አንድ ተቋም ዓለም አቀፍ ጨረታ ቢወጣ አንድ ውጭ ሀገር ያለ ተጫራች እዚህ ሀገር መጥቶ የጨረታ ዶክመንት መግዛት ሆነ መመለስ አይጠበቅበትም፡፡ ባለበት የትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ሆኖ የጨረታ ዶክመንቱን አይቶ መወዳደር እና ዋጋውን ማስገባት ይቻላል፡፡ የመጨረሻ ውጤቱንም ባለበት ሆኖ መስማት ይችላል፡፡ አሰራሩ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ይቆጥባል፡፡

በተጨማሪም የሰው ንክኪን ስለሚያስቀር ሰዎች ተገናኝተው የመነገጋርና የመደራደር እድል ስለማይኖራቸው ብልሹ አሠራርና ያልተገባ የጥቅም ግንኙትንም ያስቀራል። ለምሳሌ ቀደም ሲል ፕሮፎርማ የሚባለው ዋጋ ማቅረቢያ ግዥ ለተወሰኑ ሰዎች ተሰጥቶ እነርሱ ብቻቸውን የሚወዳደሩበት ሁኔታ ነበር፡፡

የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ ግን በአንድ ሰዓት ውስጥ በርካታ ሰዎች ይወዳደሩበታል፡፡ ውድድሩ በዋጋ ብቻ ይሆናል፤ የሰዎች ትውውቅ አይጠይቅም፤ የቦታ ተደራሽ መሆንን የግድ አይልም፡፡ ባሉበት ሆነው በአጭር ሰዓት ውስጥ ተወዳደረው ካሸነፉና የተባለውን እቃ ካቀረቡ ክፍያቸውን ይወስዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሥራ ቅልጥፍና በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡

ሥርዓቱ መንግሥትም በርካታ አማራጮች እንዲኖረው ያስቻለ ነው፡፡ ግልጸኝነት፣ ፍትሐዊነት፣ ሁሉን አሳታፊ ፣ ተደራሽና ቅልጥፍናንን ከማስፈኑም ባሻገር መንግሥት ሊያገኝ የሚገባው ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት እንዲችል ያደርጋል፡፡ ብዙ ተወዳዳሪዎች በሚኖሩ ጊዜ ቅናሽ ዋጋ ያለውን፣ ጥራት ያለውን እቃ ወይም አገልግሎት ማግኘት ያስችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ወስደን ስናይ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር ደግሞ ብልሹ አሠራሮችና ለመገደብ የሚያግዝ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት የክፍያ ሥርዓትንም ያካተተ ነው ?

ወይዘሮ መሠረት፡- ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት የክፍያ ሥርዓት የለውም፡፡ ክፍያው የሚፈጸምበት ገንዘብ ሚኒስቴር በዘረጋው ‹‹ኢፍሚስ›› በሚባል የክፍያ ሥርዓት ነው። ኢፍሚስ አጠቃላይ እስከ ክፍያ ያለው የመንግሥት በጀት የሚተዳደርበት ሥርዓት ነው፡፡

ኢጂፒ ወይም የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ከኢፍሚስ ጋር የተናበበ ነው፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት ለመግዛት ላቀደው የግዥ እቅድ ተመጣጣኝ በጀት አለው ወይ የሚለውን? የእኛ ሲስተም የሚያነበው ከኢፍሚስ ላይ ነው፡፡ በጀት ከግዥ ጋር ተቀናጅቷል፡፡ ግዥ ተካሂዶ፤ አሽናፊው ተለይቶ፤ እቃው ወይም አገልግሎት ቀርቦ አልያም ግንባታ ተካሂዶ ክፍያ በሚታዘዘበት ጊዜ ክፍያውን የሚፈጸሙ የፋይናንስ ኃላፊዎች ኢጂፒ ሥርዓት ላይ ገብተው ትክክለኛው ሂደት ጨርሶ ለክፍያ ዝግጁ የሆነ ዶክመንት መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ በኢፍሚስ በኩል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ድረስ ምን ያህል ተቋማት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሲስተሙ ገብተዋል?

ወይዘሮ መሠረት፡– 270 የፌዴራል ተቋማት እና 65 ቅርንጫፎቻቸው የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱን ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡ የፌዴራል ተቋማት ስንል ሁሉንም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ይጨምራል፡፡ ከፌዴራል ተቋማት ቅርንጫፎች እስካሁን የገቡት 65ቱ ናቸው፡፡ እነዚህ በአዲስ አበባ ከተማና በ100 ኪሎ ሜትር ቅርበት ላይ ያሉ ቅርንጫፎችን ያካትታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሲስተሙ ያልገቡ ተቋማትስ አሉ ወይ?

 ወይዘሮ መሠረት፡- ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ወደ ሥርዓቱ ቢገቡም፡፡ ቅርንጫፎቻቸውን ያላስገቡ አሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ራቅ ብለው በየክልሉ ቅርንጫፍ ያላቸው ያልገቡ አሉ፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ደግሞ ቀሪዎቹን ቅርንጫፎቻቸውን አሰልጥነን እናስገባለን፡፡

ክልሎች ራሳቸውን የቻሉ ስለሆነ የራሳቸው ሲሰተም ይኖራቸዋል፡፡ እስካሁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጥሩ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ የእኛ ሲስተም ካለማው አካል ጋር ስምምነት አድርገው የሲስተም ልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡም ይህን ሥርዓት ተግባራዊ ያደረጋሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሌሎች እየተዘጋጁ ያሉም አሉ፡፡ ባለሥልጣኑ ራሳቸውን ችለው ሲስተም ተዘጋጅቶላቸው ከፌዴራል መንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሲስተም ጋር የተናበበ ሥርዓት እንዲኖራቸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ወደ ሥርዓቱ ያልገቡት ወደ ሥርዓት ለማስገባት በቅርቡ ውይይት ተደርጓል፡፡ በተቋሙ በኩል ወደ ትግራይ ክልል፣ ወደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ወደ ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ወደ ቤንሻንጉል ክልል ተንቀሳቅሶ ኃላፊዎችን፣ አቅራቢዎችንና ባለድርሻ አካላትን አወያይቷል፡፡ በተመሳሳይም ከአንድ ሳምንት በፊት ሁሉንም ክልሎች በመሰብሰብ ተሞክሮ በማቅረብ አወያይቶ ወደዚህ ሥርዓት እንዲገቡ፤ ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ተገልጾላቸዋል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፈውን አዲሱ አዋጅ በማስተዋወቅ እነርሱ የሚያወጡት አዋጅ ከዚህ ጋር የተናበበና የተጣጠመ እንዲሆን መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ክልሎችም በፈጠነ ሁኔታ ወደ እነዚህ ሥርዓቶች የመግባት ፍላጎቱ ስላላቸው የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የፌዴራል ተቋማት ሆነው ከኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ውጭ ግዥ ሲፈጽሙ የተገኙ ተቋማት አሉ? ካሉስ ምን ዓይነት ርምጃ ተወስዶባቸዋል?

ወይዘሮ መሠረት፡– የፌዴራል የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ከኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ውጭ ግዥ እንዳይፈጸሙ በባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ሰርኩላር ደርሷቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ግዥን እየፈጸሙ ያሉት በመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዥን ሥርዓት ነው፡፡ የባለፈው ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው 65 በመቶ ያህል ግዥ የተፈጸመው በመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ነው፡፡ የተቀረው 35 በመቶ ያህሉ ደግሞ በማንዋል የተፈጸመ ነው፡፡ በማንዋል በተፈጸመው ግዥ አንዳንዶች አስፈቅደው የገዙ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ደግሞ የፌዴራል ተቋማት ሆነው ተደራሽ ያልሆኑ ቅርንጫፎች ሊሆን ይችላሉ፡፡

በዘንድሮ ዓመት ግን ሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እና 65ቱ ቅርንጫፎቻቸው የግዥ እቅዳቸው የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ መሠረት አቅደዋል፡፡ እስካሁን ባለው ክትትል የግዥ ሂደታቸውን አብዛኛዎቹ የመንግሥት በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት በኩል እየተፈጸሙ ነው፡፡

በግዥ ሂደት ውስጥ የተለየ ችግር የሚገጥማቸው ይኖራሉ፡፡ በሲስተም ችግር፤ ባላቸው የኔትወርክ ችግር አልያም በግዥው ልዩ ባህሪ ምክንያት፤ በመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ግዥን ለመፈጸም የተቸገሩ ካሉ ልዩ ፍቃድ እየጠየቁ እና እየተፈቀደላቸው በማንዋል የሚገዙ አሉ፡፡

ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ ካለ ልዩ ፈቃድ በራሳቸው ፍቃድ የገዙ ካሉ ግን በኦዲት ይረጋገጣል፡፡ በማንዋል የተፈጸመ ግዥ ግልጽ ስላልሆነ እዚህ ሆኖ ሊታይ አይችልም። እዚህ ሆነን ማየት የምንችለው በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ የተከናወነውን ብቻ ነው፡፡ በማንዋል የሚሠራ ነገር ካለ ሰነድ በመፈተሽ ይረጋገጣል፡፡ በፕሮግራማችን መሠረት ወደ ተቋማቱ ሄደን ኦዲት በምናደርግበት ጊዜ በማንዋል የተፈጸመ ግዥ ካለ ይረጋገጣል፤ ሕጋዊ ተጠያቂነትም ያስከትላል፡፡

ባለሥልጣኑ በማንዋል መግዛት ትክክል እንደማይሆን ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካለ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ባለሥልጣኑን ማስፈቀድ እንደሚያስፈልግ ሕጉ ያዛል፡፡ በዚህ መሠረት ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው አዲሱ አዋጅ 1333/2016 የሚያዘው ሲስተሙን የሚያስተዳደረው ባለሥልጣኑ እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ባለው አካሄድም ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካለ ሊፈቀድ ይቻላል፤ ከዚያ ውጭ ግን በማንዋል መግዛት የተከለከለ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓቱ ያልተካተቱ የግዥ ዓይነቶችስ አሉ ?

ወይዘሮ መሠረት፡- የሉም፡፡ የፌዴራል ግዥዎች በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ውስጥ መፈጸም ይችላሉ። መድኃኒትም ይሁን ሌሎች ግዥዎች (የእቃ ፣ የአገልግሎት፣ የምክር፣ ከምክር ውጭ የሆኑ አገልግሎቶች እና የግንባታ ግዥ ጨምር) በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት መፈጸም ይቻላል፡፡ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ሁሉንም ዓይነት ግዥዎች በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት መፈጸም ይችላሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመጀመሪያ የሩብ ዓመቱ የኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሂደት ምን ይመስላል?

ወይዘሮ መሠረት፡- በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ሊወጣ የሚችለው ሪፖርት የግዥ እቅድ ነው፡፡ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት የግዥ እቅዳቸውን በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ መሠረት አቅደው አስገብተዋል፡፡ ይህ ማለት በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ ላይ የሁሉም ተቋማት እቅድ ይታያል፡፡

በዚህ በበጀት ዓመቱ ምን ምን እንደሚገዙ፣ ግዥዎች ለመፈጸም ምን ያህል በጀት እንደያዙ፣ በምን ዓይነት የግዥ ሥርዓቶች እንደሚገዙ፣ የትኞቹ ግዥዎች በየትኛው ጊዜ በዓመቱ ውስጥ እንደሚያከናወኑ የሚያሳይ ዝርዘር የግዥ እቅድ በኢጂፒ ሥርዓት ውስጥ ይታያል፡፡ ሩብ ዓመቱ ሊገመገም የሚችለው ይሄ ነው፡፡ ይህንም መቶ በመቶ ፈጽመዋል፡፡

በግዢው ሂደት ምን ያህል እንደገዙ የሚታየው ደግሞ የግዥ ሂደቶች ሲያልቁ ነው፡፡ ለምሳሌ መስከረም ላይ የነበረ ግዥ አሁን ሂደት ላይ ነው፡፡ የስድስት ወሩ ሲገመገም ሲስተሙ ላይ የተቋማቱ ሪፖርት ስለሚገኝ ዘንድሮ ምን ምን ተገዛ፤ የስንት ብር ግዥ ተፈጸመ?፣ የትኛው የግዥ በጊዜ ሂደት ተጠናቅቋል? የሀገር ውስጥ ጨረታ ምን ያህል ነው?፤ ዓለም አቀፍ ጨረታ ምን ያህል ነው፡፡ ውስን ጨረታ ምን ያህል ነው የሚሉት ዝርዝሮች ሁሉ ሲስተሙ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ ባለሥልጣኑ የሚያገኘው መረጃ በኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት የተገዛውን ብቻ ነው፡፡

በማንዋል የተገዛው ግዥ በማንዋል ሪፖርት የሚታይ ነው፡፡ በሪፖርቱ ላይ በማንዋልና በኤሌክትሮኒክስ የፈጸሞቸውን የግዥ ዓይነቶች ይልካሉ፡፡ በማንዋል የተፈጸሙ ግዥዎች ሁሉ ሕገወጦች ሊባል አይችልም፤ ተፈቅዶላቸው የተገዙ ከሆኑ ሕጋዊ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ተደራሽ ያልሆኑባቸው ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ላይ የተፈጸመ ግዥም ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ አይቶ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለው በደንብ ኦዲት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ያለው ሂደት ግን በጣም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነ ነው። ከአሠራሩ ጋር ከተቋማት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርገናል፡፡ አዳዲስ የሲስተም ማሻሻል በማድረግ ቀላልና ይበልጥ ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን የማድረግ ሥራዎች ላይ ለፌዴራል ተቋማት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ለዩኒቨርሲቲዎችን ሁለተኛ ዙር ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

ሥርዓቱ በእነዚህ ሁሉ በጣም ውጤታማ የሆነ በሀገሪቱ ላይ በሞዴልነት የሚወሰድ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አልሚ ያለማው ኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ነገር ካለ በጋራ እየተነጋገርን በማሻሻል ውጤታማነቱን ይበልጥ እያጎለበትን እየሄድን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሲስተም መኖር የመንግሥት በጀት ከብክነት ከመታደግና፣ ሙስናን ከመከላከል አንጻር ምን ዓይነት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው?

ወይዘሮ መሠረት፡- ወጪን ከማስቀረት አንጻር አንድ አቅራቢ (ተጫራች) ግዥ ላይ ለመሳተፍ ያውጣ የነበረው የጊዜ፣ የገንዘብና የጉልበት ወጪ የሚቆጥበለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የፌዴራል ተቋም ጨረታ ቢያወጣ ባህር ዳር ላይ ያለ አንድ አቅራቢ (ተጫራች) ከባህር ዳር በአካል መጥቶ የጨረታ ሰነድ መግዛት አለበት፡፡ ከወሰደም በኋላ ለመመለስ ደግሞ ተመልሶ አዲስ አበባ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ወጪው በዚህ ረገድ የሚታይ ነው፡፡ ሲስተሙ ይህን ወጪ ዜሮ አድርጎታል። በሲስተሙ ባለበት ቦታ ሆኖ ጨረታውን አይቶ የጨረታ ዶክመንቱን በማስገባት የሚጨርሰው ነው። ስለዚህ ወጪው ዜሮ ሆኗል ማለት ነው፡፡

ለመንግሥት ተቋማት ቢሆን በጣም ብዙ የወረቀት ሥራዎች የሚያስቀር ነው፡፡ ሲስተም ላይ የሚሠራ እንደመሆኑ የሚቀመጠው ሲስተም ላይ ነው፡፡ ሲስተሙ ለተከታታይ 10 ዓመታት ዶክመንትን በአስተማማኝነት ጠበቆ የማስቀመጥ አቅም ያለው ነው፡፡ በዚህም በወረቀት ሥራ ለአንዲት ጨረታ ብቻ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ዜሮ አድርጓል ማለት ነው፡፡ ከተጫራቹም በኩል በመንግሥት ተቋማት በኩል ወጪን ያስቀራል፡፡

ሌላው ረጅም ጊዜን ይወስድ የነበረን የጨረታ ሂደት በተወሰኑ ደቂቃዎች በማከናወን ይባክን የነበረውን ጊዜ ይቆጥባል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ባለሙያዎችና ሠራተኞችም ወረቀት ለማስተካከል፤ ለማመላላስ እና ለመጻጻፍ የሚኖረውን ድካምና ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነው፡፡

ብልሹ አሠራር የሚጀመረው ከመገናኘት ነው። ብዙ ሰዎች በተገናኙ ቁጥጥር ለመነጋገር፤ ለመደራደር እድል ያገኛሉ። ሲስተሙ ግን እንደዚህ ዓይነት ግንኙነቶች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡ የሰው ግንኙነት በቀነሰ ቁጥር ብልሹ አሠራር ይቀራል፡፡ አሠራርን ለሁሉም ግልጽ ያደርጋል፡፡

አንድ መሥሪያ ቤት ያወጣውን ግዥ ሁሉም ሰው ያየዋል። በተወሰኑ ሰዎች አጥር ውስጥ ብቻ ያንን ነገር ለማዘዋወር እድል አይሰጥም፡፡ ግልጽ የሆነ ነገር በባሕሪው ለብልሹ አሠራር ለመጋለጥ እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ግልጽ በሆነ ቁጥር ለሰው እይታ ተጋላጭ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ተጠያቂነት ለማስፈን እድል ይሰጣል፡፡ የሆነ ስህተት ቢኖር እንኳን ስህተቱን ተከታትሎ ለማረም ያስችላል፡፡ ሲሰተሙ ውስጥ ገብቶ ሁሉንም ነገር ማየትም ያስችላል፡፡

ሲስተሙ ለውስጥ ሆነ ለውጭ ኦዲተሮች ክፍት የሆነ ነው፡፡ ድሮ ኦዲተሮች የቀረበላቸው ዶክመንት ፈትሸው ፋይል አገላብጠው የቻሉትን ያህል ነው የሚያዩት፡፡ አሁን ግን ሙሉ ሥርዓቱ ግልጽ ሆኖላቸዋል፡፡ ሪፖርት ቢፈልጉ ሲስተሞ ሪፖርቱን ያወጣላቸዋል፡፡ ሁሉንም የግዥውን ሂደት የሚያሳይ ነገር ሲስተሙ ላይ ስላለ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ፡፡ በቀላሉ ማየት፣ ማገላበጥና መመርመር ይቻላሉ፡፡ ለምሳሌ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሲስተም ላይ ያለውን ሪፖርት አይቶ ያልተገባ ነገር አለ ብሎ ቢያስብና ምርመራ እንዲደረግ ቢፈልግ በቀላሉ የተደራጀ መረጃ ያገኛል፡፡

ከበጀት ውጭ ግዥ እንዳይፈጸም ሲስተሙ በራሱ ይከለክላል፡፡ በጣም ትልልቅ የሆኑ እና ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግዢዎች ትክክለኛውን ግምገማና የፍተሻ ሂደት አልፈዋል ወይ የሚለውን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ሪፖርታችንን ስናየው በጣም የተጋነነ ነገር የምናይ ከሆነና አንድ ዓይነት የግዥ ሁኔታና ተመሳሳይ አቅራቢ የሚደጋገምበት ሁኔታ ሲያጋጥም ለምን የሚል ጥያቄ እንድናነሳና እዚያ ተቋም ላይ ኦዲተር ገብቶ ችግር እንዲያይ ለማዘዘ እድሉን ይሰጣል፡፡

ብልሹ አሠራር ይቀንሳል ስንል የሰው ንኪኪን ይቀንሳል፤ ጉዳዩን በሙሉ ለሁሉም ሰው ግልጽ ያደርጋል ቁጥጥርና ኦዲት ለሚያደርጉ አካላት ግልጽ የሆነና የተመቸ መረጃ ይሰጣል፡፡ በዚህ ምክንያት ብልሹና ያልተገቡ አሠራሮች የመቀነስ ድርሻ አለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትግበራው ምን ያህል ውጤታማ ነው?

ወይዘሮ መሠረት፡- እነዚህ ሲስተሞች ሀገር በቀል በሆኑ የቴክኖሎጂ ድርጅት በኢትዮጵያውያን ያለሙ ናቸው፡፡ ይህ ሲስተም እንደ ኢትዮጵያው ልንኮራበት የሚገባ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ በሀገራችን ካሉ ሲስተም ልማት ሥራዎች ብዙ ሰው በማሳተፍ ትልቁ ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም ነጋዴዎች የሚያሳትፍ እና ሁሉንም ግዥ ፈጻሚ መሥሪያ ቤት የሚያሳተፍ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ ከባንኮችና ኢንሹራንሶች ጋር እንዲተሳሰር ተደርጎ የባንክ ጋራንቲ የሚባሉ ነገሮች በሙሉ ኦንላይን እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ነው፡፡

ከገቢዎች፣ ከንግድ ሚኒስቴር ሲስተም፣ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተቀናጀ የሚሄድ ትልቅ ሥርዓት ነው፡፡ ብዙ ተሳታፊዎች ብዙ ዶክመንቶች ያሉት ሲሆን በአንድ ጊዜ እስከ ስድስት ሺ ዓይነት ጨረታ የሚወጣበት ነው፡፡ ብዙ ባለድርሻ አካላትና ተጠቃሚ ያለው፤ ብዙ አካላትን በአንድ ያቀናጀ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ሥርዓት ኢትዮጵያ ላይ እውን ሆኖ ውጤታማ ሆኗል። ይህንን ውጤታማ የሆነ ሥርዓት ያለማው ኢትዮጵያዊ ድርጅትና ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሎ መናገር በራሱ ትልቅ ኩራት ነው፡፡ ሲስተሙ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ያስገኛቸው ጠቀሜታዎችና ውጤት በተመለከተ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያደረገ ሲሆን ጥናቱ ሲጠናቀቅ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሲስተሞቹ ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?

ወይዘሮ መሠረት፡– ያጋጠሙ ችግሮች በዋናነት የግንዛቤና የክህሎት ክፍተቶች ናቸው፡፡ ሲስተሙ አዲስ እንደመሆኑ ፤ ሲስተሙን አውቆ የመጠቀም የክህሎት ክፍተት አለ፡፡ ይህ ክፍተት ለመፍታት በሳምንት አንድ ቀን ረቡዕ ጠዋት ለማንኛውም አቅራቢ፣ ተጫራችና የንግዱ ማህበረሰብ ሥልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ መማርና ማወቅ እፈልጋለሁ የሚል ማንኛውም ሰው በቀን ከ30 እስከ 40 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እየመጡ እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም ሲስተሙ በራሱ እንዲያስተምርና መረጃ እንዲሰጥ እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ሌላው ደግሞ በተከታታይ የሚመጡ ጥያቄዎች ተሰብስበው ጥያቄዎቹና መልሶቻቸው በሲስተሙ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ እኒዚህን በማየት ሰዎች እንዲገለገሉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ገዥዎቹም ራሳቸው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የተለያዩ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ሆኑ ባለሙያዎች ሲስተሙን ከመጠቀም አንጻር የክህሎትና አንዳንድ ጊዜም የግንዛቤ ክፍተቶች ያጋጥማሉ፡፡ አጠቃላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት ገለጻዎች በማድረግ፤ የሥራ አሠራር በማሳየት ያጋጠሙ ችግሮች በማቅረብ ውይይቶች በማድረግ ማስተካካያዎች እየተደረጉ ነው። በዚህም ጥሩ መግባባቶች እየተፈጠሩ መጥተዋል፡፡

የክህሎት ክፍተቱን ለመሙላት የኦንላይን ሥልጠና “ኦንላይን ለርኒንግ” ለመስጠት የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ በኦንላይን ሥልጠናው ማንም ሰው ባለበት ሆኖ ስለመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ትምህርት ማግኘት የሚችልበት ፕላትፎርም ለምቷል፡፡ አሁን ላይ ትምህርቱ እየተዘጋጀ ሲሆን የጽሑፍ ሙጅሎችን በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በድምጽና በቪዲዩ ለመስጠት ባለሙያዎች ዝግጅታቸው እያጠናቀቁ ነው፡፡

ይህ ዝግጅት ሲጠናቀቅም ሁሉም የሚማርበትን እድል ይፈጥራል፡፡ ማንኛውም አቅራቢም ይሁን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ ያለ ግዥ የሚፈጸም አካል የሚቸግረው ነገር ካለ ባለበት ሆኖ ጠይቆ መልስ የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ አሁን ላይ በስልክና በአካል ድጋፍ መጠየቅ የሚቻል ሲሆን በኢሜል፣ በመልዕክት፣ በማንኛውም መንገድ ድጋፍ ማግኘት የሚችልበት ሥርዓት/ ሲስተም ተዘርግቷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ጊዜያት ሊሠሩ የታሰቡና የታቀዱ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

ወይዘሮ መሠረት፡–  በ2017 በጀት ዓመት አቅደን እየሠራ ያለ ነው አንደኛውና ዋነኛው ይሄ ሲስተም ይህን ሁሉ ሥራዎች እየሠራ እንደመሆኑ ግልጽና ለአጠቃቀም ምቹ ሆነ ሪፖርት እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ሌላው ለተገልጋዩ ኦንላይን ሆነ ባሉበት ሆነው አገልግሎት ሆነ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ ይህንን በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋል፡፡

ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የሚመጡ የሙያ አስተያየትና ጥያቄዎች በኦንላይን ባሉበት ሆነው በሲስተም ልከው ምላሹን በሲስተሙ እንዲያገኙ በማድረግ ተደራሽነት ለማስፋት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ ይሄም በሙከራ ሂደት ላይ ነው፡፡ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት እናደርጋለን፡፡

ሌላው መሥሪያ ቤቶች የሚያወጡት ጨረታ ሂደት ላይ የተሳታፊ አቅራቢዎች ቅሬታ በሚኖር ጊዜ ቅሬታቸውን ለመሥሪያ ቤቱ አቅርበው በዚያ ምላሽ ያልረኩ ካሉ ይግባኝ ይጠይቃሉ፡፡ ይህን የይግባኝ ጥያቄ ባሉበት ሆኖ ለባለሥልጣኑ መላክ እንዲችሉና የቦርዱን ውሳኔ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ የሲስተም ልማት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህንን በሙከራ ሂደት ላይ ያለ ነው፤ በቅርቡ ለአጠቃቀም ክፍት ይደረጋል፡፡

በተጨማሪም መሥሪያ ቤቶች ጥፋተኛ የሆነን አቅራቢ ሪፖርት ሲልኩ በሲስተሙ ተጠቅሞ እንዲልኩና ምላሹን በሲስተም እንዲያገኙ እየተሠራ ነው፡፡ ይህም በቅርቡ ተጠናቅቆ ለአጠቃቀም ክፍት ይሆናል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሲስተሙን የተሟላ እንዲሆን የኮንትራት ማኔጅመንት እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ግዥው ከተፈጸመ በኋላ እዚያው ሲስተም ላይ ውል የሚገቡበት፣ በሲስተም የሚያስተዳደሩበት ሥርዓት ለመዘርጋት በሙከራ ሂደት ላይ ነን ፡፡

በተመሳሳይ በዘንድሮ ዓመት የንብረት ሽያጭን በሲሰተም እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በዚሁ ሲስተም ላይ ንብረት ሽያጭን ለመጀመር የሲስተም ልማት ሥራው እየተሠራ ነው፡፡ በኢፊሊት ማኔጅመንት ሲስተም አምና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለምቷል፡፡ ዘንድሮም በ13 ተቋማት ሙከራ የዝግጅት ሥራዎች ተሠርቶ አሁን ላይ የሙከራ ትግበራ ላይ ናቸው፡፡ ከተቋማቱ ጋር ውይይት ተደርጓል፤ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህ ውጤታማነት ሲረጋገጥ ወደ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ደረጃ በደረጃ እያሰፋን የምንሄድ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል በዘንድሮ ዓመት አዋጁን ማስተዋወቅ ሥራ በጥሩ ሁኔታ ተሠርቷል፡፡ ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችሉ የማስፈጸሚያ መመሪያዎች ዝግጅት ተጠናቅቆ አስተያየት ማሰባሰብ ሂደት ላይ ደርሰናል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሠግናለሁ።

ወይዘሮ መሠረት፡- እኔም አመሠግናለሁ።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You