ጂማ:- በጂማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው አራተኛው ዓለም አቀፍ የኦሮሞ ጥናት ኮንፈረንስ ላይ እንደተገለጸው፤ ነባሩ የኦሮሞ መንግሥት አስተዳደር በኢትዮጵያና አፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚታየውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የማስወገድ አቅም እንዳለው ተገለጸ።
‹‹የኦሮሚያ መንግሥት አስተዳደር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ›› በሚል መልዕክት በተዘጋጀው ኮንፈረንስ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጂማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ፤ የኦሮሞ ህዝብ ቀደምት መንግሥታዊ መዋቅር ያለው መሆኑን፤ ይህም ተጠናክሮ ቢስፋፋ የኦሮሞን ብቻ ሳይሆን የመላ አገራችንንና የቀጣናውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅም እንደሆነ ተናግረዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ምሁራን እንደገለጹት፤ ኦሮሞ መንግሥት አልባ እንዳልነበር፤ ነገርግን በንጉሥና በሊቀመንበር የሚመራ ሳይሆን በዴሞክራሲ ስርዓት በሚመረጡና እስከተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ድረስ ህዝባቸውን አገልግለው ስልጣን የሚያስረክቡ መሪዎች እንዳሉት አስረድተዋል።
ኦሮሞ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በተለያዩ እሴቶች የበለጸገ ሰፊ ህዝብ መሆኑን የጠቀሱት አጥኚዎቹ፤ በተለያዩ ስርዓተ መንግሥቶች ተሸርሽሮ የነበሩትን እሴቶቹንም የበለጠ ለማጠናከር ምሁራን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።
የኦሮምኛ ቋንቋ ካለው ሰፊ ማህበራዊ አገልግሎት አንጻር የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ ሆኖ ማገልገል ቢችል ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ሊፈታ እንደሚችልም በጥናቱ ተመላክቷል። አሁን በአገራችን እየታየ ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለመታደግና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ቀደምት የኦሮሞ መንግሥት አስተዳደር ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል አስረድተዋል።
ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በጂማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ጥናት ተቋምና በዩናይትድ ኪንግደም ኦሮሞ ኔትወርክ አስተባባሪነት የተጀመረው ይህ ኮንፈረንስ የሁለት ቀናት ቆይታ ሲኖረው፤ ከ20 በላይ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡበትም ታውቋል። በኮንፈረንሱ ላይ ከአሜሪካን፣ ከሲዊዲን፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከኤዢያ እና ከአፍሪካ የመጡ የውጭ ዜጎችም ተሳትፈዋል።
የኦሮሞ ጥናት ኮንፈረንስ ቀደም ሲል << <ገዳ> በዕውቀት የሚመራ አገር በቀል የኦሮሞ ስርዓት>>፣ << የኦሮሞ ስርዓትና የአተገባበር ጥበብ>> እና << የኦሮምኛ ቋንቋ ስነጥበብ፣ ልማድና ታሪክ>> በሚሉ ርዕሶች ተካሂዶ እንደነበር ይታወሳል። በቀጣይም አምስተኛውን የኦሮሞ ጥናት ኮንፈረንስ በፊንፊኔ ከተማ ለማድረግ እንደታሰበ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
ኢያሱ መሰለ