አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ከተከሰተው የሰላም እጦት ስጋት ለመላቀቅ መንግሥት በላቀ እርጋታ የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ መፍትሔ እንዲያፈላልግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ፅህፈት ቤት ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም አባተ ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግላጫ፤ አገሪቱ የሰላም እጦት ስጋት ውስጥ መውደቋን በመግለጽ፤ ከዚህ ስጋት ለመላቀቅ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላቀ እርጋታና የኃላፊነት ስሜት ህዝብንና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ያሳተፈ መፍትሔ ማፈላለግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት በርካታ አበረታች አዎንታዊ ዕርምጃዎች ቢወሰዱም፤ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ኢትዮጵያን በሀገር ውስጥ ስደተኞች ቁጥር በዓለም ቀዳሚ አድርጓታል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የዜጎች በሰላም የመኖር፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና በፈለጉበት የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ኑሮን የመመስረት፣ ሃሳብን የመግለጽና የፈለጉትን የፖለቲካ አመ ለካከት የማራመድ መብቶች ሲጣሱ መቆየ ታቸውንም ዳይሬክተሩ አመላክ ተዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ያሉ አገራዊ ችግሮች ካልተቀረፉ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ከማዳከም ባለፈ ሀገሪቱ አግኝታው የነበረውን ዝና በእጅጉ እንደሚጎዳውም አስገንዝበዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ሰላምን ያመጣሉ በሚል የተቋቋሙት የሰላምና የእርቅ እንዲሁም የማንነትና የድንበር ኮሚሽን በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ፤ በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት መዘጋት ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011
ተገኝ ብሩ