ለአካባቢው አርሶ አደሮች እፎይታን የሰጠው የሰላም ስምምነት

ዜና ሀተታ

ወይዘሮ አየለች በቀለ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በወለጋ ሆሮጉዱሩ ዞን ነው። የሚኖሩበት አካባቢ እጅግ በጣም ለምለምና ለግብርና ልማት ምቹ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ አየለች፤ በአካባቢያቸው ሰላም ባለመኖሩ ምክንያት አርሶና ምርትን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ይቅርና ወጥቶ መግባት ፈታኝ ነበር ፡፡ ይህም እንደምንም ለራስ ከመሆን ባለፈ ለሌሎች መትረፍ ሳይቻል ቆይቷል ይላሉ።

በአካባቢው በነበረው ግጭት ምክንያት ሰዎች ወጥተው መግባት፣ አርሶ ማምረት ፈተና ሆኖ መቆየቱን የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ ወጥቶ የመቅረት ክስተቶችም እንደሚያጋጥሙ አውስተዋል፡፡

“ዛሬ ምን ይፈጠር ይሆን?” በሚል ስጋት ውስጥ ከወደቅን ዓመታት ተቆጥረዋል የሚሉት ወይዘሮ አየለች፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት ለአካባቢው ነዋሪዎች የሰላም እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አካባቢያቸው አርሰው ምርታማ የሚሆኑበት፣ አርብተው ጥሩ ውጤት የሚያገኙበት ለምለም ምድር ነው የሚሉት ወይዘሮዋ፤ የተደረገው የሰላም ስምምነት ሰላምን የሚያጸና ከሆነ በስፋት በማልማት ምርቱን ወደ ለሌሎች አካባቢዎች ጭምር ለገበያ ማቅረብ ይቻላል ነው ያሉት።

የተደረገው የሰላም ስምምነት ሰላምን በማምጣት እና ለአርሶ አደሩ እፎይታን በመስጠት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የሚናገሩት ወይዘሮ አየለች፤ የክልሉ መንግሥት የተደረገው የሰላም ስምምነት እንዲጸና ቀበሌ ድረስ በመውረድ መሥራት አለበት ይላሉ።

አቶ ሃይሉ ቀንዓ ደግሞ የቄለም ወለጋ ዞን ወቀቤ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። እሳቸውም በአካባቢያቸው ሰላም ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረዋል ።ይህን ተከትሎም በርካቶች “የመንግሥት ደጋፊ” ናችሁ በማለት ከገንዘብ ክፈሉ ጀምሮ የተለያዩ ቅጣቶች ሲደርስባቸው እንደነበርም ይናገራሉ።

ነዋሪው ከመፈናቀል ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ሲደርስበት እንደነበረ የሚናገሩት አቶ ሃይሉ ፤ በግጭቱ ምክንያት የመንገድ መዘጋትና የመብራት አገልግሎት መቆራረጥ ያጋጥም ነበር፡፡ እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ሳይቻል መቅረታቸውንም ያወሳሉ።

ሰላም ከመጣ ምርታማ የሆነው ቄለም ወለጋ ምርቶችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመላክ በጋራ ተረዳድቶ መኖር እንደሚያስችልም ይናገራሉ። ልጆች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት እና ስጋት የሌለው ኑሮ ለመኖርም ሰላም መፈጠር ትልቅ ፋይዳ አለው ይላሉ።

የወለጋ ሆሮጉድሩ አቤ ደንጎሩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ደግሞ አቶ በቀለ አራርሶ በአካባቢያቸው በነበሩ ግጭቶች ሰላማዊ ሰዎች ይገደሉና መሠረተ ልማቶችም የከፋ ጉዳት ያጋጥማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ ። በዚህ ምክንያት ህብረተሰቡ መንገድ እና መብራት ጭምር በማጣት ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመውም ይናገራሉ።

አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት ለህብረተሰቡ እፎይታን የሚፈጥር መሆኑንም ይናገራሉ። በአካባቢው የሰላም አለመኖር ችግር ዋነኛ ተጎጂው አርሶ አደሩ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ በቀለ፤ ሰላም መፈጠሩ ለአርሶ አደሩ እረፍት በመስጠት እንዲሁም የተቋረጡ መሠረተ ልማቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው የገለጹት።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/ 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You