ኢትዮጵያ የኩፍኝ በሽታን በመከላከል ረገድ ስኬት ማስመዝገቧ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ኩፍኝ እና የኩፍኝ በሽታዎችን በመከላከሉ ረገድ ስኬት ማስመዝገቧን የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ አስታወቁ፡፡

ዶክተር መልካሙ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ካለፉት አሥር ዓመት ወዲህ ውጤታማ የክትባት ዘመቻዎችን ተግብራለች፡፡ ክትትል እና ቁጥጥርን በማጎልበት ለወረርሽኙ ፈጣን ምላሽ መስጠት ተችሏል፡፡ ኩፍኝ እና የኩፍኝ በሽታዎችን የማስወገድ ስትራቴጂ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመተግበሯም የኩፍኝ በሽታን በመከላከል ረገድ ስኬት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ስኬቱ መመዝገብ የቻለው ኢንስቲትዩቱ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሀገር ለኩፍኝ ወረርሽኝ በሰጠው ፈጣንና ተከታታይ ስልታዊ ምላሽ ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እኤአ ከነሐሴ 2021 እስከ ታህሳስ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ 78 ሺህ 106 የኩፍኝ በሽታ ተጠቂዎች የነበሩ መሆናቸው ሪፖርቶች ማመላከታቸውን ጠቅሰው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሞቱ መጠንም ዜሮ ነጥብ 81 መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ዶክተር መልካሙ ገለጻ፤ በኩፍኝ ወረርሽኝ ለተጠቁ እና ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ እንደ መቅደላ ያሉ አካባቢዎች ትኩረት በመስጠት ተከታታይነት ያላቸው በርካታ ቅንጅታዊ የክትባት ዘመቻዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም በማስወገድ ሥራ ሂደት በከፍተኛ ደረጃ ለዘመቻው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ እጥረት ገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኩፍኝ ወረርሽኝን ለመከላከል ረገድ ትልቅ እንቅፋት ከሆኑት መካከል አንዱ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ግብዓት መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩ የሚፈታበት አማራጭ መንገድ እየፈለጉ በመሄድ በኢትዮጵያ እኤአ ከነሐሴ 2024 ጀምሮ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ እና ገዳይነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረግ መቻሉ መረጋገጡን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ የኩፍኝ እና እንደትኩሳት ያሉ ኩፍኝ ያልሆኑ በሽታዎች (NMFR) ከአራት ነጥብ ዜሮ በመቶ ወደ ሁለት ነጥብ አራት በመቶ ዝቅ ማድረጓን አስታውቀዋል፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ ኩፍኝ በከፍተኛ መጠን የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፣ ትኩሳት፣ ሽፍታ፣ ሳል፣ የዓይን መቅላት እና እንባን የሚያስከትል ከባድ በሽታ ነው። በዋነኛነት የሚተላለፈው ኩፍኝ የያዘው ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ በአየር አማካኝነት ወደ ሌላው ሰው የሚዛመት መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/ 2017 ዓ.ም

Recommended For You