“ምክር ቤቱ የንግዱን ማህበረሰብ የሚመጥን ቁመና ላይ አይደለም”- የዳይሬክተሮች ቦርድ

አዲስ አበባ፡በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ማህበረሰብ የሚመጥን ቁመና ላይ አይደለም ሲል የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ ቦርዱ የሰጠውን ውሳኔ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያቀረበውን ውሳኔ መቀበላቸውን ገልጸው፣ በምክር ቤቱ የተስተዋለው የውጭ ጉዞና የተጋነነ ምንዛሬ መኖሩ አንዱ ችግር ነው ማለቱ ትክክል ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግዱን ማህበረሰብ ሀብት በማባከኑ፤ የተጋነነ የውጭ ምንዛሬ የስተዋለበት፤ ትላልቅ የግዢ ፖሊሲዎች ጥሰት የተፈጸመ መሆኑ የንግዱን ማህበረሰብ የማይመጥን አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ ያላወቀው አዳዲስ ቅጥር፤ የውስጥ እድገት አሠራርና የትልልቅ ግዢ የፖሊሲ ጥሰት መፈፀሙን፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በምክር ቤቱ መኖራቸውን ቦርዱ መግለጹ ተገቢ መሆኑንም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

የዳይሬክተሮች ቦርድ ለበርካታ ወራቶች ባደረጉት ውይይትና ግምገማ ምክር ቤቱ የንግዱን ማህበረሰብ የሚመጥን ቁመና ላይ አመለሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል በመግለጫቸው።

የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የፖሊሲ፣ የሕግና የአሠራር ጥሰት በፈጸሙ ኃላፊዎች አስተዳደራዊ ርምጃ የመውሰድና ክስ ለመመስረት ዝግጅት እያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ቦርዱ የምክር ቤቱን አፈፃጸም ገምግሞ የንግዱን ማህበረሰብ የሚመጥን ምክር ቤት ለማድረግ የሪፎርም ሥራዎች እንዲደረግ ውሳኔ ማሳለፉንና ምክር ቤቱም ለውጡን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱን የቀደመ ሥራና ቁመና ለመመለስ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጿል።

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እያካሄደ የሚገኘው ስር ነቀል ለውጥም የንግዱን ማህበረሰብ የሚመጥን፤ የሚያበረታታ፣ ኢንቨስትመንትን የሚስብ፣ የተጣሱ ደንቦችን የሚያስከብር እና የፖሊሲ ክፍተቶችን የሚያሻሽል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የትልልቅ የግዢ ፖሊሲዎች ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተስተውለዋል በሚል በ23 ጥቆማዎች ሳቢያ የኦዲት ኮሚቴ ከቦርድ አባላት ተዋቅሮ ምርምር እንዲካሄድ መወሰኑ የሚታወቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ታደሰ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/ 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You