ተግባራዊነት የራቀው የወል ስምምነት

ዜና ትንታኔ

በዓለም በተለያዩ ጊዜያት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የተለያዩ ስምምነቶች ቢደረጉም የረባ ለውጥ ሲመጣ አይታይም፡፡ ይባሱንም ዓለምን ከድጡ ወደ ማጡ እያስገባ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የዘላቂ ልማት እሳቤን ለማዳበር የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ማስቀረት አስቸኳይ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአየር ንብረት ለውጥ እየተሰጠ ያለው ምላሽ አጥጋቢ ባለመሆኑ አፍሪካውያን አስፈላጊ መፍትሔ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም መጠቆማቸው የሚታወስ ነው፡፡

ለዚህም የአፍሪካ ሀገራት ሀብቶቻቸውንና ልማቶቻቸውን ከአየር ንብረት ለውጥ የጸዳ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ያደጉ ሀገራት በየኢንዱስትሪያቸው የሚፈጠረው የአየር ብክለት ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል አለባቸው የሚለው ትክክል መሆኑ ብቻ ሳይሆን እነርሱም ያምኑበታል፡፡ ይሁን እንጂ ለመቀነስ ወደ ተግራዊነት ከመግባት ለአንዱ ወገን ማላከካቸው እንዲሁም በየጊዜው የሚገቡት ቃል ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› አይነት መሆኑ የብዙሃኑ እውነት ነው፡፡

ባሳለፍነው ህዳር ወርም 29ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ29) በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋሚያ 300 ቢሊዮን ዶላር ቢመደብም በርካቶች ውሳኔውን ተቋውመውታል፡፡ ከዚህ ቀደም ይሰጥ ከነበረው 100 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት ሳይቻል አሁን ደግሞ ሌላ የማይጨበጥ ተስፋ በሚል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የበለጸጉ ሀገራት በሚፈጥሩት የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ዳፋውን የሚቀበሉት ታዳጊ ሀገራት ሁኔታውን ለመቋቋም ቢያንስ አንድ ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የምድር እጣ ፈንታ በሚቀጥሉት አምስትና 10 ዓመታት በኮፕ29 ጉባዔና በሀገር ደረጃ በሚወሰድ ርምጃ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለአካባቢ ብክለት አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያበረክቱ ሀገራት ከራስ ወዳድነት እሳቤ መውጣት እንዳለባቸውና የአየር ንብረት ለውጥ መቀነስ ብሎም የተረጋጋች ዓለም ለመፍጠር ተግባር ተኮር እንቅስቃሴ መጀመር የግድ እንደሚላቸው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ያደጉ ሀገራት ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ሕጎችና መመሪያዎች በልካቸው መቀየር ላይ ተጠምደዋል፡፡ ያደጉ ሀገራት የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ቅድሚያ ከመስጠታቸው በተጨማሪ በአየር ንብረት ለውጥ ለሚፈጠረው ጉዳት እራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ሲጥሩ ይስተዋላል የሚሉት የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋችና ተመራማሪ ኑሃሚን ጥበቡ ፤ እራስን ብቻ የማዳን አካሄድ ባላደጉ ሀገራት ላይ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል ይላሉ፡፡

እንደ ተመራማሪዋ ገለጻ፤ ባደጉ ሀገራት መካከል ትብብር ባለመኖሩ በዋናነት በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ  በሚያስከትለው ጉዳት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሕዝቦች በአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ሆነዋል፡፡ እንደ ኮፕ29 ያሉና ሌሎች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚካሄዱ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ከወረቅት የዘለሉ አይደሉም፡፡ አፋጣኝ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅም በኢኮኖሚ ሽፋን ለማለፍ ተጨባጭ ባልሆነ ድርጊት አግበስብሰው ተግባራዊነቱም የውሃ ሽታ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ሀገራት የተለያዩ ንቅናቄዎች መጀመር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራና በታዳሽ ኃይል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለችግሩ መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ መሪዎችና የተለያዩ ተቋማት በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር በዘርፉ ያላቸው ልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እንዲሁም ተግባር ተኮር ድርጊት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎችና ተፅእኖ ፈጣሪ አካላት ያደጉ ሀገራት ትኩረት እንዲሰጡና ቃላቸውን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ የማሳመን ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ላይ በመሥራት የተረጋጋችና ፍትሃዊነት የሰፈነባት ዓለም ለመፍጠር መትጋት አለበት ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ የኮንሰርተም የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ዳይሬክተርና ባለሙያ አቶ ዮናስ ገብሩ በበኩላቸው የሚደርሰው ጉዳት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያደጉ ሀገራት ተገቢውን ኃላፊነት ካለመወጣታቸው የመነጨ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎቻቸው ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያበረክቱት አሉታዊ ተጽዕኖ ሀገራቱ ተመጣጣኝ ካሳ መክፈል እንዳለባቸውም ነው የገለጹት፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ባደጉ ሀገራት ጉዳት በሚያደርስበት ጊዜ የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ ልዕልና ያላቸው በመሆኑ በትክክል እንደሚቆጣጠሩት አስታውሰው፤ ያላደጉ ሀገራት በተቃራኒው በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ እየሆኑ ነው፡፡ ለአብነትም ከአንድ መቶ ሺህ በላይ በቅርብ ጊዜ በተሠሩ ጥናቶች 80 በመቶ የሚሆነው የዓለም መሬትና ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ሕዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡

ባደጉ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች እንደ ብድር መታየት የለባቸውም የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊነታቸው ደካማ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ተጎጂ የሆኑ ሀገራት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች የተገባላቸውን ቃል ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ አስፈላጊው አማራጭ መከተል እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

አየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ቃል የተገቡ ድጋፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ብሎም ተጠያቂነትን ለማስፈን አፍሪካም ሆነ ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በጋራ ድምጻቸውን ማሰማት የግድ እንደሚላቸው ይናገራሉ፡፡ የፋይናንስ ድጋፉ እንደ ስጦታ ብቻ ሳይሆን እንደ ግዴታም መታየት አለበት ባይ ናቸው፡፡

አፍሪካ በዓለም አየር ንብረት ለውጥ የምታደርሰው ጉዳት ዝቅተኛ ቢሆንም በከፍተኛ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ የምትጎዳ አሕጉር መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እኤአ በ2022 በአፍሪካ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕዝቦች በቀጥታ በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ሆነዋል፡፡ በዚህም ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት በኢኮኖሚው ላይ ደርሷል፡፡ እንዲሁም አምስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በድርቅና ጎርፍ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህን አሳሳቢ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና ለመቀነስ የበለጸጉ ሀገራት የገቡን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ግፊት ከማድረግ ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ አረጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ምሁራኑ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/ 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You