አገልግሎቱ የውጭ ሀገር ዜጎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት እየጎለበተ መሆኑን ገለጸ

– የውጭ ሀገር ዜጎችን በሙሉ ለመመዝገብ ዝግጅት እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፡እንደሀገር የውጭ ሀገር ዜጎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት (ሲስተም) እየጎለበተ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የኢሚግሬሽን የውጭ ዜጎች ምዝገባና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አዳነ ደበበ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እስካሁን እንደሌሎች ሀገራት የውጭ ሀገር ዜጎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የተደራጀ ሥርዓት አልነበራትም፡፡

የተደራጀ ሲስተም አለመኖሩ በሕገወጥ መንገድ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ለመቆጣጠር አላስቻለም፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዲስ ሥርዓት እየጎለበተ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሕገ ወጥ መንገድ ገብተው የሚኖሩ ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች መኖራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ በሕገወጥ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችን ለመቆጣጠር ባለመቻሉ ብዙ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች አሉ የሚሉት አቶ አዳነ ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ገብተው የሚኖሩ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ የሆኑ ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች ሳይቀር ባልተፈቀደላቸው ሥራ ላይ የተሠማሩ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በጥቁር ገበያ እና በመሰል የወንጀል ተግባራት የሚሳተፉ ብዙ የውጭ ሀገር ዜጎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የሱዳን፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ የናይጄሪያ፣ የላይቤሪያ ፣ የጂቡቲ፣ የመን እና የሶሪያ ዜጎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ከላቲን አሜሪካ ሀገራት፣ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ዜጎች በተወሰነ መልኩ እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡

በሕገወጥ ድርጊቶች ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገር ኢኮኖሚና ደህንነት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ነው የሚሉት አቶ አዳነ፤ የዜጎች የመኖር ህልውና እንዲናጋና በብዙ መልኩ የኢኮኖሚው እንቅፋት እየሆኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ሕገወጥ ዜጎች እንዲኖሩ ያደረገው የሕግ ክፍተት ሳይሆን ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖሩ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ዜጎች ከመጡበትና ከተፈቀደላቸው ውጭ ሌላ አላማ ሲያራመዱ የምንቆጣጠርበት ሲስተም አለመኖሩ ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገር ውስጥ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎችን የመመዝገብ ሥራ ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰው፤ ቁጥራቸው በጣም ብዙ በመሆናቸው በሙሉ ለሙሉ ለመመዝገብ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት ግን በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎች በሙሉ ለመመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

እየጎለበተ ያለው ሲስተም ወደ ሀገሪቱ የሚገቡና የሚወጡ ዜጎች ላይ ለመቆጣጠር ያስችላል የሚሉት አቶ አዳነ፤ በቀጣይ የውጭ ሀገር ዜጎች ለመመዝገብና ሕጋዊ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ሥርዓቱ ተግባራዊ ሲደረግ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ሀገሪቷ ውስጥ የተፈቀደለት ጊዜ ሲያልቅ እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሕገ ወጥነት እንዳይስፋፋና ሕጋዊነት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፤ አሁን ላይ ሥርዓቱ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ በአሠራር ሁሉም ነገሮች መስመር ለማሲያዝ እየተሠራ እንደሆነ አመልክተው፤ ሥርዓቱ ማንኛውም ሰው ከተፈቀደለት ጉዳይ ውጪ ሌላ ነገር ላይ እንዳይሰማራ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።

ሕገወጥ የውጭ ሀገር ዜጎች ከመቆጣጠር አንጻር ከሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/ 2017 ዓ.ም

Recommended For You