አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት በመደመር አስተሳሰብ አንድ ላይ እንሥራ የሚል ሃሳብ እያቀረበች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኝ ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንደተናገሩት፤ በጎረቤት ሀገራት መካከል ቀደም ሲል የመጠራጠርና በጠላትነት የመተያየት ሁኔታ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ሁኔታ በመቀየር የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አብረን እንሥራ፤ እንተባበር እያለች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና የማንነት ተመሳሳይነት አላት፡፡ ይህን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ መሥራት የሚቻልባቸው ነገሮች ላይ አብራ ማጥናት እና መሥራት እንደምትፈልግ አመልክተዋል፡፡ ከሌሎች ተመሳሳይ ፍላጎት እና ምላሽ ቢገኝ ጥሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ መሥራት የሚቻልባቸው ነገሮች ላይ በተለይም ሰላም ከማምጣት አንፃር ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ አላስፈላጊ ሲሆንም ራስን የማግለል እርምጃ ይወሰዳል፡፡
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ሰላም አስተዋጽኦ የምታደርገው በሰው ሀገር ውስጥ ሆና ነው፡፡ ይህም የመሳካት ዕድሉ የሚወሰነው በአብዛኛው በኢትዮጵያ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በዚህ ሀገር ፍላጎት ጭምር ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ለአብነት በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመጣ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ መወጣቷን ጠቅሰዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ጥሩ ተደማጭነት ያለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላም በኩል በሌሎችም የጎረቤት ሀገራት ሰላም ለማምጣት ብዙ ጥረት ተደርጓል ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ለአብነት ሱዳን ወደ ጦርነት ከመግባቷ አስቀድሞና ከገባች በኋላም፤ ኢትዮጵያ ብዙ ጥረት አድርጋለች። ነገር ግን ሱዳን ላይ ሰላም እናመጣለን የሚሉ ብዙ ተዋናዮች በመግባታቸው ተጨማሪ ራስ ምታት ላለመሆን ለሌሎች ዕድሉን መስጠቷን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማደራደርም የተሻለ ሰላም እንዲመጣና ግጭቶች እንዲቆሙ ለማድረግ ጥረት እንደምታደርግ የተናገሩት ዳርእስከዳር (ዶ/ር)፤ ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ተብሎ አይሠራም፤ የራስ ሥራም ይሠራል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ኢትዮጵያ በሰላም ጉዳይ ላይም ሆነ በሌሎች የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 14 ቀን 2017 ዓ.ም