አዲስ አበባ፡– በትግራይ ክልል በመጪው ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 12 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን ለመትከል እቅድ ተይዞ ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ሙዑዝ ሀይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በትግራይ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በተያዘው የክረምት ወቅት 80 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል እንክብካቤ ለማድረግ መታቀዱንና ወደስራ መገባቱን ተገልጿል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀምሌ 22 ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ ክልሉ የራሱን ድርሻ ለመወጣት በእለቱ 12 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ።
እያንዳንዱ ወረዳ የራሱን እቅድ በማዘጋጀትና የቦታ ልየታን ያጠናቀቀ ሲሆን በእለቱ በሚከናወነው የችግኝ ተከላም አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ የስፖርት ማህበራትና ክለቦች፣ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ስራው ወጥነት ባለው መልኩ በታቀደው ልክ ለመፈፀም ከሁሉም ወረዳዎች ጋር የአንድ ቀን ምክክር ተደርጎ የመተግበሪያ እቅዱ ወደታች እንዲወርድ የተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙዑዝ፣ ችግኞቹ የሚኖራቸውን ስነ ምህዳራዊጠቀሜታ ለህብረተሰቡ በማስገንዘብ በባለቤትነት እንክብካቤ እንዲደረግ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ችግኞችን መትከል ብቻም ሳይሆን እንዲፀድቁ አስፈላጊውን ሁሉ እንክባቤ እያደረግን ነው ያሉት አቶ ሙዑዝ ለዚህም ከዝናብና ውሃ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የውሃ ማቆር ስራዎችን በመስራት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በክልሉ የክረምት የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ የሚሆነው የሀምሌ 22ቱ ፕሮግራም ሲሆን የሚተከሉ ችግኞች ወደ ደን ሀብትነት ተቀይረው ለኢኮኖሚው እድገት የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ ህብረተሰቡ ችግኞቹን በበጋ ወራት ውሃ በማጠጣትና ከእንስሳት ንክኪ በማራቅ ለአካባቢያዊ እንክብካቤ ስራው የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ዳይሬክተሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በክረምቱ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ስራው እየተከናወነ ሲሆን በመጪው ሀምሌ 22 ቀን2011 ዓ.ም ደግሞ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ውጥን መያዙ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ድልነሳ ምንውየለት