አዲስ አበባ፡- በክልሉ በበጋ የመስኖ ልማት 59ሺ ሄክታር መሬት በማልማት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ፤ በክልሉ በበጋ የመስኖ ልማት 59ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከዚህም 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
እስካሁንም ወደ 20 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በመስኖ ለምቷል የሚሉት አቶ ባበክር፤ በክልሉ ከፍተኛ የሽንኩርት ፍላጎት በመኖሩ 10 ሺህ ሄክታር መሬት በሽንኩርት መሸፈኑን ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በበጋ መስኖ ልማት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እስካሁን ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የአትክልት ምርት ተሰብስቦ ለገበያ ቀርቧል።
አንድ ሺህ 60 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት አቶ ባበክር፤ እስካሁን 112 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ተሸፍኗል። ሌሎቹ በሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በክልሉ እስካሁን 40 ሺህ ሄክታሩን ማልማት ያልተቻለው ለመስኖ የሚውሉት ቦታዎች ውሃ የተኛባቸው በመሆኑ ውሃ የማንጣፈፍ ሥራ እየተሠራና ውሃ እስኪቀንስ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን አመልክተው፤ በአሁኑ ወቅት ማሳዎቹ ላይ ውሃ ተኝቶባቸው የነበሩ አብዛኛው ወረዳዎች ላይ ከ60 በመቶ በላይ የመስኖ ልማት ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በበጋ መስኖ ሁለት ዙር ለማልማት እቅድ ተይዟል። በክልሉ ተፈላጊ የሆኑና ቶሎ የሚደርሱ አትክልቶችን በመጀመሪያ ዙር ይለማሉ። ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቆስጣ፣ ጎመን፣ ጥቅል ጎመንና ካሮት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው። በመጀመሪያ ዙር የተተከሉት አትክልቶች ከተሰበሰቡ በኋላ 59 ሺ ሄክታር መሬት ሁለተኛ ዙር በበቆሎ የሚሸፈን ይሆናል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም