በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ ሰሞኑን በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ አምስተኛ የስራ ዘመን አራተኛ ዓመት 10ኛ ጉባኤ ላይ የመንገድ፣ የውሃ የኤሌክትሪክ፣ የጤና እና በሌሎችም አገልግሎቶች ላይ የአቅርቦት ችግሮች መኖራቸውንና መስተካከል እንዳለባቸው የጨፌው አባላት በስፋት አንስተዋል።
የሰላም ጉዳይ ደግሞ ከሁሉም በላይ እንደሆነና አሁን የክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ ያለው ሰላም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጥያቄም አስተያየትም በአባላቱ ቀርቧል። ቅድሚያ በተሰጠው የሰላም ዙሪያና ከእያንዳንዱ የጨፌው አባላት ምን እንደሚጠበቅ እንዲሁም አጠቃላይ ጉባኤውን በተመለከተ አንዳንድ የጨፌውን አባላት አነጋግረናል።
የኦሮሚያ ውሃና ልማት ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ አሰፋ በሰጡት አስተያየት የጨፌው አባላት በመንግሥትና በአመራሩ በኩል የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችና በሌሎችም ጠንካራ አስተያየት ሲሰጡ ነበር። ከተነሱት ሃሳቦችም አንዳንዶቹ አግባብነት እንዳላቸው ጠቁመው፣ በክልሉ አራት ዞኖች ውስጥ በነበረው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ለመሰረተ ልማት አገልግሎት ሥራ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እርሳቸው እንዳሉት መንግሥት የህግ የበላይነት እንዲከበር በግልጽ አስቀምጧል። በመሆኑም እያንዳንዱ የምክር ቤት አባላት ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነትም እንዲከበር አካባቢያቸው ላይ በመስራት ውክልናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ፀጥታ በማስከበር
የራስን ኃላፊነት ሳይወጡና ውጫዊ በማድረግ መንግሥት ሰላም አላስከበረም የሚለው አካሄድ አግባብነት እንደሌለው አስረድተዋል። መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ እያደረገ ያለው ጥረት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየተወሰደ መሆኑንና ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሰላምን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረትና ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብታቸው እንዲረጋገጥ ለሚከናወኑ ተግባራት የፀጥታ መዋቅሩ ዝግጁ እንዲሆን፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርም በጉባኤው ላይ ማንሳታቸውንም አስታውሰዋል።
ከምዕራብ አርሲ ዞን ነሰቦ ወረዳ የተወከሉት የጨፌ አባል አቶ ሙስጠፋ ከድር ሀገሪቷ በምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በተለይም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በክልሉ መንግሥት የተያዘው አቅጣጫ አግባብ እንደሆነ ይናገራሉ። መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ካልተወጣ በሌሎች ሀገሮች የሚስተዋሉ ችግሮች ኢትዮጵያም ውስጥ እንዳያጋጥም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የጨፌ አባላት የመንግሥትም የህዝብም አደራ ይዘው እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙስጠፋ ፣ አባላቱ በልማትና በፖለቲካ ቀደም ሲል በተወከሉበት አካባቢ የሚሰሯቸውን ሥራዎች ከማጠናከር ጎን ለጎን ሀገሪቷ ባጋጠማት የፀጥታ ችግር ላይም በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ከጥፋት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለው መገንዘብ እንዳለበት፣ ከህግም በላይ መሆን እንደማይቻል፣ በጨፌው የተላለፉትን መልዕክቶችን መሰረት አድርገው የአካባቢያቸው ህዝብ ለሰላም ዘብ እንዲቆም በውክልናቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በአካባቢያቸው በተለይም የውሃ አቅርቦት፣ ዞንን ከወረዳ፣ወረዳን ከቀበሌ እንዲሁም ከከተሞች ጋር የሚያገናኝ መንገድ አለመኖሩንና ችግሩም ከፍተኛ መሆኑን ለጨፌው ማስረዳታቸውን የገለጹት ሌላዋ ከሐረርጌ ዶባ ወረዳ የተወከሉት የጨፌው አባል ወይዘሮ ሀሊማ መሐመድ ናቸው።
የአካባቢያቸውን ችግር እንዲህ ቢያስረዱም ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ሰላም የሁሉም መሰረት እንደሆነና ለዚህም ከእርሳቸው ጀምሮ ሁሉም ለሰላም እንዲቆም በአካባቢያቸው ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በጨፌው አባላት በፀጥታ ዙሪያ የተነሳው ስጋት አግባብነት ቢኖረውም በክልሉ አልፎ አልፎ በተወሰኑ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር አሳሳቢ ሁኔታ አለመኖሩን የኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት የክልሉ ነዋሪ ከጸጥታ ችግር ወጥቶ ፊቱን ወደልማት አዙሯል።
በህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን በማዘዋወር፣ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር በህዝቦች መካከል ግጭቶች በመፍጠርና የሀገሪቷን ለውጥ ወደኋላ ለመመለስ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውንና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከህዝቡ ጋር በመሆን ችግር ፈጣሪዎችን ለማስወገድ እየሰራ ይገኛል።
የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ተቋሙን በጥራትና በብዛት የሰው ኃይሉን በመገንባት፣ በማጠናከርና መልሶ በማደራጀት፣ ቀድሞ ወንጀልን በመከላከል በተለይም በመረጃ አስተዳደር ሥርዓት፤ በህዝብ ውስጥ የተፈጠረውን ሰላም የማስከበር ፍላጎት ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ፣ ደቡብ ኦሮሚያ ቦረና ጉጂ አካባቢዎች ትጥቅን እንደ አንድ ዓላማ ማሳኪያ አድርጎ የማየት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር ቀነአ፣ እነዚህ በህዝብ ድጋፍ እንደሌላቸውና እየታገላቸውም እንደሆነ አመልክተዋል።
በሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን መግለጽ የማይፈልግ ህገመንግሥታዊ እንዳልሆነም ጠቁመዋል። ህገወጥ መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በሀገር ደረጃ የተዘጋጀው አዋጅ በሥራ ላይ ከዋለ ጦር ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጉዳይ መፍትሄ እንደሚያገኝ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፣ጨፌው በርካታ ነገሮችን አንስቶ በመወያየት ማጠናቀቁን አስታውሰው፣ ህዝቡ ከመልካም አስተዳደር እና ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጋር በተያየዘ ያነሳቸውን እንዲሁም የህዝብና የመንግሥት ንብረት የሆኑትን ግልጽነት ባለው መንገድ ከመደበኛ የክትትልና ግምገማ በተለየ ሁኔታ በቀጣይ በጀት አመት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የተያዙ እቅዶችን ለማስፈጸምም ሆነ ክትትልና ግምገማ ለማድረግ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነና የጨፌው አባላት ከላይ እስከታች በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ለምለም መንግሥቱ