አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ውጤቶችን ቢያስመዘግብም አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በዓመቱ በርካታ ሥራዎች ቢከናወኑን አሁንም በአፋጣኝ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
አቶ ዘላለም አያሌው በሰጡት አስተያየት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በዚህ አንድ ዓመት በርካታ መልካም ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው፣ ለበርካታ ዓመታት በሕገወጥ መንገድ በተለያዩ አካላት ተይዘው የነበሩ መሬቶች ወደ መንግሥት መመለሳቸውን አንስተዋል።
እነዚህ ልማት ላይ ያልዋሉ በከተማዋ ያሉ መሬቶች መመለሳቸው ለከተማዋ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የተናገሩት አቶ ዘላለም፣ በከተማዋ ሰላምን ለማምጣት የተሰሩ ሥራዎችም አበረታች ውጤት ነበሩ ብለዋል።
የከተማዋን ንፅህና ከመጠበቅና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ አንፃር የተሰራው ሥራ እንዲሁም አሁን በቋሚነት እየተከናወነ ያለው ወርሀዊ የፅዳት ዘመቻ እንዲሁም ከተሽከርካሪ ነፃ ቀንን በማወጅ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተሰጠው ትኩረት በስኬትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የሚካተቱ እንደሆኑም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዘላለም አስተያየት የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በከተማዋ ያሉ ክፍት ቦታዎችን ወደ ልማት ማስገባት፣ የግንባታ ሥራዎች ሲሰሩ ለዛፎች መትከያ ስፍራ እንዲኖራቸው አስገዳጅ ሕግ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ፣ ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን መገንባት፣ በከተማዋ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ እና ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ክፍተት ስላለበት ይህንንና ሌሎችም ችግሮችን ተመልክቶ ወደፊት ቢሰራ መልካም መሆኑን ገልፀው፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጭነት መኪናዎች ላይ የተጣለው የመንቀሳቀሻ ሰዓት ገደብ ሀገሪቱን ለአላስፈላጊ ወጪ ስለሚዳርግና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ስለሚያስነሳ እንደገና ቢታይ ተገቢ ነው ብለዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ የመኪና ግብር ለመክፈል ተራ ሲጠብቁ ያገኘናቸው አቶ እንዳለ ደረጀ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ በለውጡ ሂደት በአካባቢ ፅዳት፣ በጎ አድራጎት ሥራዎች እና መሰል ተግባራት ላይ ውጤት ቢያስመዘግብም በገቢ አሰባሰብ ላይ ሰፊ ክፍተት እንደነበረበት ለዚህም በክፍለ ከተሞች ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች የሠራተኞች ቁጥር አናሳ መሆኑን የየካ ክፍለ ከተማን ለአብነት በማንሳት ተናግረዋል።
መብራት፣ ውሃ፣ መንገድና ሌሎችም መሠረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ለነዋሪዎች ከማቅረብ አንፃር በዓመቱ ክፍተት እንደነበር የተናገሩት አቶ እንዳለ፣ ያልተጠኑ ውሳኔዎችም ሌሎቹ ችግሮች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
በደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የሰዓት ገደብ ሳይጠና የተተገበረ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ለመንግሥት ግብር ለመክፈልና ሰርቶ ለመለወጥ የሚደረግ ጥረትን የሚያደናቅፍ ከመሆኑም ባሻገር በዘርፉ በተሰማሩ ባለሀብቶች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ እንደገና ሊፈተሽና ሊስተካከል ይገባዋልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ሥራዎችን መስራቱን የተናገረችው ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ለኢላ አብደላ፣ ለአብነትም በበጎ አድራጎት ሥራዎች ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ትልቅ ሥራ ተሰርቷል ብላለች።
አሁንም በከተማዋ ለሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የደንብ ልብስ ለማሟላት የተጀመረው እንቅስቃሴ ትልቅ ስኬት ነው ያለችው ወጣት ለኢላ፣ በከተማዋ ሰላም እንዲሰፍን የተሰራው ሥራም አበረታች እንደነበር ጠቁማለች።
በከተማዋ እየጨመረ የመጣው ሕገወጥ ንግድ እና የስርቆት ወንጀል እንዲሁም ከጊዜ ወደጊዜ እያሻቀበ ያለው የኑሮ ውድነት ላይ አስተዳደሩ በትኩረት እንዳልሰራ የተናገረችው ወጣት ለኢላ፣ ይህ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ወደፊት በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብላለች።
በከተማዋ ሕገወጥ ተግባራት በስፋት ይታያሉ ለዚህ ደግሞ ሰዎች መብትና ግዴታቸውን ማወቅ አልቻሉም። ከዚህ ጋር በተያያዘ በከተማዋ በሞተር ሳይክል ስርቆት ተስፋፍቶ ነበር አሁን ላይ እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉ ጥሩ ሆኖ ሳለ ለመልካም ተግባር የሚጠቀሙበት አካላት ተደራጅተው ቢሰሩ ሥራ አጥነትን ይቀንሳሉ።
አስተያየት ሰጪዎቹ በከተማዋ አስተዳደሩ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ቢኖሩም፣ ቅሬታ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ዜጋ የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣና አስተዳደሩን እንዲያግዝ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ድልነሳ ምንውየለት እና ሃይማኖት ከበደ