የጨቅላ ሕፃናት የዓይን በሽታ እልባት ካልተሰጠው በሀገሪቱ የዓይነ ስውራን ቁጥር ይጨምራል

– በሁለት ሆስፒታሎች ህክምና ካገኙ ህፃናት መካከል 48 በመቶ የችግሩ ሰለባ ናቸው

አዲስ አበባ፦ በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚከሰተው የዓይን ብርሃን ተቀባይ የደም ስሮች መቀንጨር በሽታ በጊዜ እልባት ካላገኘ በቀጣይ ዓመታት በሀገሪቱ የዓይነ ሥውራን ቁጥር በእጅጉ እንደሚጨምር ተገለጸ። በሁለት ሆስፒታሎች ሙቀት ክፍል ተኝተው ህክምና ሲያገኙ ከነበሩ ህፃናት መካከል 48 በመቶ የችግሩ ሰለባ መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ህክምና ትምህርት ቤት በዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የአዋቂና የህፃናት ዓይን ህክምና ልዩ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሳዲቅ ታጁ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት መሻሻል ጋር ተያይዞ መወለድ ከሚገባቸው ጊዜ ቀደም ብለው የሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናትን ሕይወት ከመታደግ አኳያ አመርቂ ውጤት ቢመዘገብም፤ በዓይን ብርሃን ተቀባይ የደም ስሮች መቀንጨር በሽታ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን  የሚያጡ ጨቅላ ህፃናት ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ነው።

እ.ኤ.አ ከ1920-30ዎቹ የዓለም የጤና አብዮት ማበቡን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእናቶችና ህፃናትን ሕይወት መታደግ መቻሉን ዶክተሩ ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ ሕይወታቸው ተርፎ የዓይን ብርሃናቸውን በሚያጡ ጨቅላ ህፃናት ሳቢያ ያደጉ ሀገራት በ1950ዎቹ በዓይነ ስውራን ተጥለቅልቀው እንደነበር አውስተዋል።

“ይህ ችግር በኛ ሀገርም እንዳይከሰት ስጋት አለኝ” ያሉት ዶክተር ሳዲቅ፤ ለችግሩ በጊዜ እልባት ካልተሰጠው በሚቀጥሉት አምስት እና 10 ዓመታት ውስጥ በዚህ በሽታ ብቻ በሀገሪቱ 20 ሺህና 30 ሺህ ዜጎች ዓይነ ስውር እንደሚሆኑ ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል።

በሀገሪቱ አሁን ባለው ሁኔታ ህክምናው በጥቁር አንበሳ፣ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች እና በተወሰኑ የግል ጤና ተቋማት ብቻ እንደሚሰጥ ያመለከቱት ዶክተር ሳዲቅ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በተደረገ ጥናት በጥቁር አንበሳና ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች የጨቅላ ህፃናት ማቆያ ሙቀት ክፍል ተኝተው ህክምና ሲያገኙ ከነበሩ ጨቅላ ህፃናት መካከል 48 በመቶ (መጠኑ ቢለያይም) የችግሩ ሰለባ ሆነው መገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በሁለቱ ተቋማት ብቻ ይህን ያህል የበሽታው ተጠቂ ህፃናትን ማግኘት ማለት በሀገር አቀፍ ደረጃ ችግሩ ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው ያሉት ዶክተሩ፤ እነዚህ ህፃናት በጊዜው በመታየታቸው ብርሃናቸውን መታደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ዶክተር ሳዲቅ፤ ችግሩ ቀድሞ ከተደረሰበት የህፃናትን የዓይን ብርሃን መታደግ እንደሚቻል አስረድተው፤ ሕጻናቱ ከተወለዱ በሁለትና ሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ያለባቸው መሆኑ ተለይቶ ህክምናውን ካላገኙ፤ የዓይናቸውን ብርሃን መመለስ እንደማይቻል ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ህፃናት የዓይን ብርሃናቸውን ባጡ በዓመቱ 60 በመቶዎቹ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጥናቶች ያሳያሉ ያሉት ዶክተሩ፤ ስለበሽታው በቂ እውቀትና ግንዛቤ ባለመኖሩ ምክንያት ሕይወታቸው ተርፎ የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡ ጨቅላ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው። እነዚህ ህፃናት ደግሞ በሕይወት የመኖር ተስፋቸው የመነመነ ነው ብለዋል።

ያደጉ ሀገራት ካጋጠማቸው የህፃናት ዓይነ ስውርነት ማዕበል በኋላ በሙቀት ክፍሎቻቸው ከሚሰጠው የጨቅላ ህክምና ጋር ተያይዞ የዓይን ብርሃን ተቀባይ የደም ስሮች መቀንጨር ልየታና የዓይን ምርመራ እንደ አንድ የህክምና ክፍል አድርገው እየሠሩበት እንደሚገኙ አመላክተው፤ በዚህም ችግሩን መከላከል መቻላቸውን ያስረዳሉ።

ዶክተሩ፤ ከሌሎች ሀገራት ትምህርት በመውሰድ ተመሳሳይ ርምጃ በመውሰድና ለችግሩ ትኩረት በመስጠት የህፃናትን ሞት የመቀነስ ግብ የህፃናት ዓይን ብርሃን መታደግን ታሳቢ ካላደረገ በቀጣዩ ትውልድ እንዲሁም በሀገር ትልቅ ችግር መፍጠሩ እንደማይቀር አሳስበዋል።

ይህ እንዳይከሰት ትምህርት ክፍሉ በበኩሉ ችግሩን ቀድሞ መለየትና መከላከል የሚቻልበት የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በህፃናት ሙቀት ማቆያ ክፍል የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ችግሩን መለየት እንዲችሉ የማሠልጠን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ችግሩን የመለየት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 11 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You