ሰሜን ሸዋ፡– በሰሜን ሸዋ ደጋማ አካባቢዎች በብዛት በውርጭ የመጠቃትና ውሃ የመያዝ ችግር ስላለባቸው ችግኞቹ ውርጩን መቋቋም የሚያስችላቸውን መንገድ በቴክኖሎጂ የማገዝ ምርምር እየተሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ብርሃኑ ከትናንት በስቲያ በወረዳው በተደረገ የችግኝ ተከላ ወቅት እንዳሉት፣ የምርምር ማእከሉ በተለይም ከውጭ የሚገቡና ለዚህ ሀገር የሚሆኑ ዛፎችን በማምጣትና በማላመድ ለአካባቢው ተስማሚ ችግኞች እያቀረበ ይገኛል።
አካባቢው ደጋማ በመሆኑ ምክንያት ችግኞቹ የመፅደቅ ችግር አለባቸው ያሉት ዶክተር አብዮት፣ ያንንም ችግር ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የምርምር ሂደት በመጠቀም እንክብካቤውን በሳይንስ በመደገፍ ለመስራት አቅዷል ብለዋል።
ችግኝ ተከላው የ4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ እቅዱ አካል መሆኑን ያወሱት ዶክተር አብዮት፣ ቢያንስ ከታቀደው የ4 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ ማፅደቅ እንኳን ከተቻለ የሀገሪቷን የደን ሽፋን በ1 በመቶ ማሳደግ ይችላል፤ ለዚህም ማህበረሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባሱና ወረና ወረዳ አስተዳዳሪ ታጠቅ ገድለ አማኑኤል በበኩላቸው የችግኝ ተከላ ፕሮጀክትን በተመለከተ የምርምር ማእከሉ የሚሰራቸው ስራዎች እንዳሉ ገልፀው፣ ከስራዎቹም መካከል አንዱ በእለቱ የምርምር ማእከሉ ሙሉ ሰራተኞቹን በማሰባሰብ በአካባቢው ላይ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ማካሄዱን ለአብነት ገልፀዋል።
አካባቢው ደጋ የሆነ የአየር ንብረት ያለው እና በጣም ቅዝቃዜ የሚያጠቃው ቦታ መሆኑን የገለፁት አቶ ታጠቅ፣ ለዚህ አካባቢና አየር ንብረት ተስማሚ የሆነ አገር በቀል የሆኑ ችግኞች እንዲዘጋጁ ከማድረግ አኳያ የምርምር ማእከሉ ፕሮግራም ይዞ እየሰራና ወረዳውንም እየደገፈ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ዳግማዊት ግርማ