‹‹መልካምነት›› በሰው ልጆች ውስጥ ያለ ተፈጥሯዊ ባህሪ ቢሆንም በሀይማኖታዊና በባህላዊ እሴቶቻችን ጎልብቶ በማህበራዊ ተራክቧችን ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ጸጋ ነው። ‹‹ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው፣ መልካምነት ለራስ ነው፣ ጽድቅና ኩነኔ ቢኖሩም ባይኖሩም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም ›› የሚሉትን የመሳሰሉ አባባሎቻችን የመልካምነትን በጎ ጎን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው። ሰው ለሆዱ ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለህሊናው እርካታም በጎ ስራን መስራት ሙሉ ጤናማ እንደሚያደርገው የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጀመረው የክረምት በጎ አድራጎት ፈቃድ ጥሪም ሰሞኑንን የአዲስ አበባ ወጣቶች በሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ታካሚዎችን ለመርዳት ተዘጋጅተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ከጤና ሚኒስትር ጋር በመተባበር በከተማዋ በሚገኙ 12 ሆስፒታሎች ውስጥ የክረምት ጊዜያቸውን የበጎ አድራጎት ሥራን በመስራት ለማሳለፍ ከተዘጋጁ ወጣቶች ጋር ውይይት አድርጓል።
የውይይቱ ዓላማ ወጣቶች ለማህበረሰቡ በይበልጥም ለታካሚዎች ያላቸውን አዛኝነት በተግባር ለመግለፅና በሚሰሩት መልካም ስራ የህሊና እርካታ ለማግኘት ያለመና ያለንን የመተዛዘንና የመረዳዳት እሴቶች ጥቅም ላይ በማዋል በገንዘብ የማይተመን መልካም ሥራ በመስራት አጋርነትን ማሳየት ነው።
በውይይቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይለሰማያት መረዓጥበብ ባስተላለፉት መልዕክ እንደተናገሩት በበጎ አድራጎት ስራ ተሳታፊ መሆን በህወታችን ከምናከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል። ስለዚህ በዚህ ስራ ላይ ለመሳተፍ የተዘጋጁ ወጣቶች ለነፍስም ለስጋም የሚሆን መልካምነትን አልመው የተነሱ በመሆኑ እድለኞች ናቸው ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በጎአድራጎት ስራ ለብዙ ሀገሮች ለውጥ መሰረት እንደጣለላቸው የተናገሩ ሲሆን በዓለም ላይ በርካታ የበጎ አድራጎት ስራ የሚሰሩ ታላላቅ ሰዎች ለሰው ልጅ ችግር ፈቺ የሆኑ አስገራሚ ስራዎችን እንደተከናወኑ ተናግረዋል።
ይህ በሆስፒታል አካባቢ የሚገኙ ስራዎችን በማቀላጠፍ ህመምተኞችን ለመርዳት የታሰበው የበጎፈቃድ አገልግሎት ለብዙ ታካሚዎች መድህን እንደሚሆንም ወይዘሮ ሊያ ተናግረዋል። ወጣቶች ዛሬ በሆስፒታል የሚሰጡት በጎአድራጎት አገልግሎት ነገ በሆስፒታሉ ለመስራት በር የሚከፍትላቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በአርአያነታቸው የሚታወቁትና በማይንድ ሴት ኮንሳልት ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት ደበበ በቦታው ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በጎነት የሕሊና ጉዳይ ፣ ፈቃድ የአዕምሮ ጉዳይ መሆኑና አገልግሎት የድርጊት የሚገለጽ መሆኑን አስረድተዋል። በጎነት ‹‹መልካምነት፣ ደግነት፣ ጥሩነት ›› የሚሉ እሳቤዎችን እንደሚይዝም አስረድተዋል። ዶክተር ምህረት ወጣቶች መልካም ነገርን በመስራት የሕሊናቸው ተገዢ እንዲሆኑም መክረዋል።
በኢትዮጵያ የተነቃቁ ወጣቶች ማህበር ስር እንደተደራጀች የምትናገረው ወጣት ሳሌም ገብረማርያም በአሁኑ ሰዓት በበጎፈቃድ ስራ ላይ እንደተሰማራች ትናገራለች። ቀደም ሲልም የጎዳና ተዳዳሪዎችንና አዛውንቶችን በመርዳት ተማሪዎችን በትምህርት በመደገፍና ችግኞችን በመትክል ላለፉት ስምንት ዓመታት መሥራቷን አስታውሳለች።
አሁንም በጎነት በሆስፒታል በሚለው ፕሮግራም በተጀመረው የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን ተናግራለች። ቅንነትና በጎ አድራጎት ለሀገራችን ሰላምና እድገት አስተዋጽኦ እንዳለውም ሀሳቧን ሰጥታለች።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011
ኢያሱ መሰለ