ትኩረት የሚፈልገው የጎማ ዛፍ ልማት

ዜና ትንታኔ

የጎማ ዛፍ ልማት በቀላሉ ወደ ገንዘብ መቀየር የሚችል (ካሽ ክሮፕ) የግብርና ምርት ነው። የጎማ ዛፍ፤ የአየር ንብረትን ከመጠበቅ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት ከመሆን፣ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር፣ ከውጭ የሚመጣውን ምርት ከማስቀረትና ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከማስገኘት አንጻር ሲታይ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ከሚባለውም በላይ ነው ይላሉ። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና እና የዓልሙናይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን።

‹‹ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብሯ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዘርፎች አንዱ የግብርና ዘርፍ ነው፤ ግብርናው ለተኪ ምርቶች ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን የውጭ ምንዛሪን ግኝትን ማሳደግ የሚቻልበት ነው። ጎማን እና የጎማ ዛፍ ውጤቶችን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ በሀገር ውስጥ ማምረት ቢቻል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ይጠቅማል›› የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) ናቸው።

ኢትዮጵያ ያሏትን ፀጋዎች በአግባቡ ባለማልማቷና ወደ ኢኮኖሚው መመንዘር ባለመቻሏ ለዘመናት በድህነት ኖራለች። ተስማሚ የአየር ፀባይ፣ የሰጡትን መቀበል የሚችል መሬት፣ ለተለያየ ልማት የሚሆን በቂ የውሃ ሀብት እና ከፍተኛ የሰው ሀብት እያላት እነዚህን አጣጥማ ለውጤት ማብቃት ባለመቻሏ እያላት እንደሌላት ሆና በድህነት የኖርንባቸው ጊዜዎች የሚያስቆጩ ናቸው። ግብርናችን አሁን ከቁጭት እንድንወጣ የሚያደርጉ አዳዲስ የሥራ ባሕሎችን እያስተዋወቀን መሆኑ ሳይረሳ ማለት ነው።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ ዐሻራ እና ሰው ሠራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበሩ ጠና እንደሚገልጹት፤ ኢትዮጵያ የተለያየ የአየር ፀባይና የተለያየ አግሮ ኢኮሎጂ ያላት ሀገር ነች፤ ለአካባቢ ጥበቃ ከሚሰጡት ጥቅም ባሻገር በቀላሉ ወደ ኢኮኖሚ ሊመነዘሩ የሚችሉ እንደ ዕጣን፣ ሙጫ፣ ቀርከሐ እና የጎማ ዛፍን የመሳሰሉ ዕፅዋት ይበቅሉባታል። የእነዚህን ዕፅዋት አዋጭነት እያጠኑ ኢኮኖሚውን በሚያግዝ መልኩ ማልማትም ያስፈልጋል ይላሉ።

ኢትዮጵያ የጎማ ዛፍን ማብቀል የሚያስችሉ ቦታዎች አሏት ያሉት አቶ አበሩ፤ በተለይም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የጎማ ዛፍን ለማምረት የሚያስችል ሰፊ ቦታ እንዳለ ለአብነት ጠቅሰው፤ ከክልሉ የተገኘው ነው ባሉት መረጃ በአካባቢው ብቻ የጎማ ዛፍን ማልማት የሚያስችል 48 ሺህ ሄክታር መሬት በጥናት መለየቱን ያስረዳሉ።

ከዚህ በፊት በአካባቢው የጎማ ዛፍን እያመረቱ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ለማቅረብ የተደራጁ ማኅበራት እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ምርቱን የሚቀበሉ ኢንዱስትሪዎች አለመስፋፋትን ተከትሎ ተደራጅተው የሚያመርቱ ማኅበራት ሥራቸውን በትጋት እንዳይሠሩ ተግዳሮት ሆኗል ይላሉ።

ፍሬዘር ጥላሁን የጎማ ዛፍ ኢትዮጵያ እየተጓዘች ያለችበትን ኢንዱስትራላይዜሽን ከመደገፍና እና የትራንስፖርት ዘርፉን ከማሳለጥ አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ አለው ይላሉ። ነዳጅን በኤሌክትሪክ ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንዳለ ሁሉ የተሽከርካሪ አንድ ግብዓት የሆነውን ጎማን በሀገር ውስጥ ምርት መተካትም አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳሉ። የጎማ ዛፍን በመትከል ጥሬ ምርቱን ለኢንዱስትሪ በማቅረብ ለተሽከርካሪ የሚሆን ጎማና ሌሎች ምርቶችን ማምረት ቢቻል ለዚህ ተብሎ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት እንደሚቻልም ይጠቅሳሉ።

ግብርናችን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንዲሆን ያልተለመዱ ምርቶችንም እያመረቱ አቅሙን ማሳደግ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ፍሬዘር፤ በአረንጓዴው ዐሻራ መርሐ-ግብር የሚተከሉት ችግኞች የአየር ንብረትን የሚጠብቁ፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ። ከዚህ አንጻር የጎማ ዛፍ ልማት በተለይም ከኢትዮጵያ እድገትና መዳረሻ አንጻር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ይጠቁማሉ።

ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ የመገጣጠሙ ሥራ እየተከናወነ እንዳለ ሁሉ ነገ ተሽከርካሪን ማምረት የሚችሉ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችም ሊገነቡ ይችላሉ። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለተሽከርካሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶች ላይ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። የጎማ ዛፍን ማልማትና ጎማ ማምረት አንዱ ሊሆን ቢችልም እንደ ብረት እና ነዳጅን ሊተካ የሚችለው የኤሌክትሪክ ሀብት በእጃችን ያሉ ሀብቶቻችንን በተገቢው መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከተሽከርካሪ ጋር ተያይዞ የሚወጣውን ከፍተኛ ምንዛሪ መቀነስ የሚቻለውም የጎማ ዛፍን በማልማትና ጎማን በማምረት ነው ይላሉ። የጎማ ዛፍን ከመትከል ጎማ እስከ ማምረት ባለው ሂደትም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል፤ በተለይም ወጣቶችን አደራጅቶ፣ አሠልጥኖና ቴከኖሎጂውን አስታጥቆ ወደ ሥራ ማስገባት ቢቻል ዘርፈ ብዙ ትርፍ ይገኛል፤ ጅምር ሥራ አለ፤ ጅምሩን ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ ሳያደርጉ በዘርፉ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችንም ጭምር በማሳተፍ የጎማ ዛፍን በስፋት በማምረትና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር አዲስ የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ ዐሻራ እና ሰው ሠራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበሩ ጠና ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአሁኑ ጊዜ በሦስት ሺህ 884 ሄክታር መሬት ላይ የጎማ ዛፍን እያለማ ለሆራይዘን ጎማ ግብዓት እንደሚያውል አስረድተው፤ የጎማ ዛፍ ልማት ከአረንጓዴ ዐሻራ አንጻርም ይሁን ከኢንዱስትሪ ግብዓትነት አንጻር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው በመሆኑ ወደፊት በትኩረት የሚሠራበት እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም

Recommended For You