በቅሬታ አቀራረብ መስተንግዶ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እንዴት እየታረሙ ነው?

የአስተዳደር ሕግ የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት በፍታዊነትና የሕግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ እንዲሰጡ ለማስቻል በአዋጅ ቁጥር 1183/12 ጸድቆ በሥራ ላይ ከዋለ የተያዘውን ዓመት ሳይጨምር አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት 30 የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ላይ ክትትል ተደርጓል፡፡

አዋጁ በዋናነት የተቋማት መመሪያ አወጣጥና እና አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሲሆን፤ ሰሞኑን በ2014 ዓ.ም ክትትል በማድረግ ምክረሀሳብ የተሰጣቸው ሰባት ተቋማት ላይ ዳግም ክትትል ተደርጎባቸው የተሰጠውን ምክረሀሳብ ምን ያክል እንደፈጸሙ የሚያሳይ የግምገማ ሪፖርት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ይፋ ተደርጓል፡፡

ክትትሉ የተደረገባቸው የመንግሥት ተቋማት ገንዘብ ሚኒስቴር፥ ትምህርት ሚኒስቴር፥ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፥ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን ናቸው፡፡

በወቅቱ የፍትህ ሚኒስትር ወይዘሮ ሐና አርአያስላሴ እንደገለጹት፤ ብዙ ግዜ ስለፍትህ ሲታሰብ የፍትሐብሄር እና የወንጀል ሕጎች ይታሰባሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ሰዎች ከመንግስት አስተዳደር ተቋማት ጋር ባላቸው ግንኙነት አካታች የሆነ የሕግ ሥርዓት መኖሩ ለፍትህ መረጋገጥ ፋይዳ ያለው ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የመንግሥት አስተዳደር ሕግ፤ ተቋማት በእኩልነት፣ ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ስልጣንና ተግባራቸውን እንዲያስፈጽሙ የሚያስችል የሕግ ማሕቀፍ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ አንድ ሕዝባዊ የመንግሥት አስተዳደር የፍትህን ማስፈን ተገቢነት በመገንዛብ የአስተዳደር ሕግ አዋጅ በ2012 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።

ቀድመው በተሰሩ የክትትል ሥራዎች የተገኙ ግኝቶች የተቋማትን ጠንካራ እና ደካማ ጎን አጉልቶ ማሳየት ብቻ ሳይሆን ተቋማት ለአስተዳዳር ፍትህ እና ለሕግ የበላይነት መስፈን ላላቸው ቁርጠኝነት ትልቅ ዓላማ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተሰራው ግምገማ ከዚህ በፊት ከነበረው ግብረ መልስ በኋላ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ተቋማት በመመሪያ አወጣጥ ሂደት ላይ የነበረባቸውን ክፍተት ፈተው፤ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ላይ ብዙ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ውስንነቶች ታይተዋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የሕጎች ተፈጻሚነትን መከታተል አንዱ የፍትህ ሚኒስቴር ተግባር እንደመሆኑ፤ በቀጣይ እነዚህ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቋማትን በማካተት የአስተዳደር ሕጉ ምን ያህል እየተፈጸመ ነው የሚለው በቋሚነት የሚታይ ይሆናል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

የተገኘውን የአፈጻጸም ግምገማ ውጤት የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት ለመልካም አስተዳደር ቁርጠኝነት እንዲያውሉት ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና የፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢፋ ቦሩ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አዋጁ የተዘጋጀበት ዓላማ እውን እንዲሆን እና እንዲሳካ አስፈጻሚ የመንግሥት አካላት ለአዋጁ ተገዢ በመሆን በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጽሙት ይጠበቃል፡፡

የአዋጁን አፈጻጸም በተመለከተ በተለያዩ ተቋማት የመጀመሪያና ዳግም ክትትል በማድረግ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ምክረሀሳቦች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ይፋ የተደረገው ሪፖርትም የዚህ አንድ አካል ሲሆን፤ ውጤቱ ተቋማት በላቀ አፈጻጸማቸው እውቅና እንዲያገኙ እና ክፍተት ባሳዩት ተግባር ተጠያቂ ኢንዲሆኑ የሚያስችል ነው ይላሉ፡፡

የአዋጁ አፈጻጸም በመንግሥት ቁርጠኛ አቋም የተወሰደበት መሆኑ ታውቆ፤ የመንግሥት አስተዳደር ተቋማት በአዋጁ መሰረት ቁርጠኛ አመራር ሊሰጡና ተገቢ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ሕጎች ተፈጻ ሚነት መከታተል ዳይሬክተር ሀወኒ ታደሰ እንደገለጹት፤ ተቋማት ላይ ክትትል ሲደረግ የሕግ ዳሰሳ፣ቃለመጠይቅ፣ የመስክ ምልከታ እና የሪርፖቶች ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ ናሙና አወሳሰድ በተመለከተ በተቋማቱ ጉዳይ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ቃለመጠይቅ ተደርጓል፡፡

የአስተዳደር ውሳኔ እና ቅሬታ አፈታትን በተመለከተ ዘፈቀዳዊ በሆነ መልኩ መረጃ ለመውሰድ ተችሏል፡፡ የተገኘው መረጃ ከሕጉ ጋር እና ቀድሞ ከተሰጡት ምክረሀሳቦች በማገናዘብ መተንተኑን ያስረዳሉ፡፡

የመመሪያ አወጣጥና ሕጋዊ ሂደት በተመለከተ ገንዘብ ሚኒስቴር ከ2014 ዓ.ም በኋላ ለተዘጋጁ ሁሉም አዋጆች መስሪያ ቤቱ የጽሁፍ ማብራሪያ ማዘጋጀት መቻሉ እና ለሚመለከታቸው አካላት ለአስተያየት መላኩ እንደጥንካሬ መወሰዱን ይናገራሉ፡፡

የመጀመሪያው ክትትል ከተደረገ በኋላ መስሪያ ቤቱ ስምንት አዳዲስ መመሪያዎችን በሥራ ላይ አውሏል፡፡ መመሪያዎቹን አይቶ ማንኛውም ሰው አስተያት መስጠት እንዲቻል ጋዜጣ ላይ ማስታወቂያ ማውጣት ተገቢ መሆኑ ቢቀመጥም መስሪያ ቤቱ ይህን አለማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

ሌላው ተቋሙ ለስምንቱም መመሪያዎች መዝገብ አለማደራጀቱ፣ አሳታፊ የውይይት መድረክ አለማዘጋጀት፣ ሁለት መመሪያዎች ስልጣን ሰጪ ሕግ ሳይኖር መውጣታቸው እና ነባር አዋጆችን አለማስመዝገብ በክትትሉ የታየ ክፍተት መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በዳግም ክትትሉ ግዜ የወጡ መመሪያዎች በስልጣን ሰጪ አካል ስልጣን የሚሰጣቸው ሕግ መኖሩ ተረጋግጦ መውጣቱ እና አዲስ መመሪያ የማስመዝገብ ሂደቱ የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን በቅድመ መመሪያ አወጣጥ ግዜ የተቀመጡ ስርዓቶች አለመሟላታቸውን አብራርተዋል፡፡

በባለድርሻ አካላት ለሚሰጡ አስተያየቶች ተቋሙ ማብራሪያ አላዘጋጀም፡፡ በተጨማሪም በረቂቅ ደረጃ በቀረበው መመሪያ እና በጸደቀው መመሪያ መካከል ስላለው ልዩነት የጽሁፍ ማብራሪያ አለማዘጋጀት፣ መመሪያዎቹን በሁለት ቋንቋ አለመዘጋጀት እና ነባር መመሪያዎች በተቋሙ ድረገጽ ላይ አለመጫናቸው እንደ ክፍተት መታየታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ሀወኒ እንደሚሉት፤ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል እንደጥንካሬ የተወሰደው፤ መመሪያን በተሰጠ ስልጣን ስር ማውጣት፣ ለፍትህ ሚኒስቴር እና ለሚመለከታቸው አካላት ለአስተያየት ማቅረብ፣ አስተያየቶችን በጽሁፍ መቀበል እና ማብራሪያዎችን ማዘጋጀት ነው፡፡

መመሪያ ከመውጣቱ በፊት መደረግ የነበረባቸው አንዳንድ ስርዓቶች አለመደረጋቸው እንዳለ ሆኖ፤ በንግድ ሕጉ መሰረት አንድ ሰው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚያቋቁምበትን ስርዓት የሚደነግግ መመሪያ ማዘጋጀት በአስገዳጅነት መቀመጡን ያነሳሉ።

ነገር ግን በተቀመጠው የሶስት ወር የግዜ ገደብ ውስጥ መመሪያው ሳይወጣ መቅረቱ ዜጎች ለሚያቀርቡት ጥያቄ አገልግሎት ላለመስጠት ምክንያት መሆኑ እና መመሪያዎችን በተቋሙ ድረገጽ ተደራሽ አለማድረግ እንደ ድክምት መታየቱን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በዳግም ክትትል ግዜ ውስጥ ምንም አይነት መመሪያ አላወጣም፡፡ ነገር ግን አንድ የአሰራር ስርዓት ሰነድተገኝቷል፡፡ የአስተዳደር ስርዓት አዋጁ ሰነዶች ከሚሰየሙት ስያሜ ጋር ጉዳይ የለውም፡፡

ስለዚህ የትኛውም ለአሰራር ስርዓት የተዘጋጀ መመሪያ በተገልጋዩ ዘንድ ውጤት ካመጣ እንደመመሪያ እንደሚቆጠር እና የመመሪያን ቅድመ ስርዓት ተከትሎ መውጣት እንዳለባቸው አዋጁ ይደነግጋል፡፡ ተቋሙ በተገልጋዮች መብትና ጥቅም ላይ በመመሪያ ደረጃ ባልወጣ ሰነድ መወሰኑ እንደክፍተት ተወስዷል ይላሉ፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር በክትትል ግዜ ውስጥ አምስት መመሪያዎችን ያወጣ ሲሆን፤ ለፍትህ ሚኒስቴር ለአስተያያት መላካቸው፣ በሶስቱ መመሪያ ላይ የማብራሪያ ጽሁፍ መዘጋጀቱ እና አብዛኞቹ መመሪያዎች ከመመሪያ ቅርጽና ይዘት አንጻር የተሟሉ መሆናቸው በጥንካሬ መወሰዱን ይናገራሉ፡፡

መዝገብ አለማደረጀት፣ ማስታወቂያ በድረ ገጽ ወይም በጋዜጣ አለማውጣት፣ ማንኛውም አካል ሊሳተፍበት የሚችል የውይይት መድረክ አለማዘጋጀት፣ ለባለድርሻ አካላት ረቂቁን ለአስተያየት አለመላክ እና የመመሪያዎችን ቅጂ በእንግሊዘኛ ቋናቋ አለማዘጋጀት በደካማ ጎን ተወስዷል ይላሉ፡፡

ሀወኒ እንደሚሉት፤ ጤና ሚኒስቴር በክትትል ግዚያት ውስጥ ያጸደቀው መመሪያ ባይኖርም፤ አራት እረቂቅ መመሪያዎችን አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ ክትትሉ የሚደረገው ረቂቁ እስከደረሰበት ደረጃ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር በረቂቅ መመሪያዎቹ ላይ በድረገጽ አስተያየት መስጠት እንደሚቻል መታወጁ እንደ ጥንካሬ ተወስዷል፡፡ እስካሁንም ባለው ሂደት መመሪያዎቹ ተገቢውን ይዘው ቀጥለዋል፡፡ መዝገብ አለማዘጃት፣ በጋዜጣ ማስታወቂያ አለማውጣት፣ ለባለድርሻ አካላት አለመላኩ እና የሕዝብ ውይይት አለማድረግ እንደክፍተት ይጠቅሳሉ፡፡

ሌላኛው በአዋጁ ላይ የተቀመጠው፤ አስተዳደራዊ ውሳኔ ሰጭነትን እና ሕጋዊ አፈጻጸምን በተመለከተ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር አስተዳደራዊ ውሳኔ ጥያቄን በአካልና በኤሌክትሮኒክስ መንገድ በጽሁፍ ሊቀርብ የሚችልበትን መንገድ ዘርግቷል፡፡ እንዲሁም የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የሚሰማበት አግባብ መኖሩ እንደጥንካሬ መታየቱን ይገልጻሉ፡፡

ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ በተቋሙ ቅሬታ ማስተናገጃ መቋቋሙ የሚደነቅ ቢሆንም፤ በቂ በሆነ በሰው ኃይል ያልተደራጀ መሆኑ እንደውስንነት ታይቷል፡፡ አንድ ሰው አቤቱታ ሲያቀርብ አቤቱታ እንዳቀረብ ማረጋገጫ ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም ገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ስድስቱም መስሪያ ቤቶች ይህን አላደረጉም፡፡

ዜጎች አቤቱታ ሲያቀርቡ ተቋሙ አቤቱታውን መቀበሉ የሚያረጋግጥ ማብራሪያ መስጠቱ ብዙ ምልከታ አለው፡፡ ቅሬታ አቅራቢው በወቅቱ ውሳኔ አልተሰጠኝም ቢል እንኳን እንደግዜ ማጠቀሻነት ለማቅረብ ያግዛል፤ ተቋማት በግዜ ገደብ ውስጥ ሥራቸውን እየሰሩ ነው የሚለውን ለመለካት ያግዛል ይላሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄዎችን በጽሁፍ፣ በኦንላይን እና በአካል የሚቀርብበትን አሰራር ዘርግቷል፤ ዜጎች የሚያቀርቡትን ማስረጃ የመመርመር እና ውሳኔ የመስጠት ሥራዎችን ሲሰጥ እንደጥንካሬ ተወስዷል። ውሳኔ ሲስጥ ዋናው ፍሬ ነገሩ ምንድነው የሚለው ተተንትኖ እንዲቀርብ አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን በተቋሙ የሚሰጡ ውሳኔዎች ትንተና የማይካሄድባቸው መሆኑ፣ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል እስካሁን አለመቋቋሙ እንደድክመት መወሰዱን ያስረዳሉ፡፡

ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አቤቱታ የመቀበል እና ውሳኔ አሰጣጥን ዲጂታላይዝድ ከማድረግ አንጻር፣ ውሳኔዎች ገላጭ በሆነ መልኩ በጽሁፍ መሰጠታቸው፤ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት አግባብነት ያለው ማስረጃን ከአቤቱታ አቅራቢዎች መስማቱ በጥንካሬ ታይቷል፡፡ አልፎ አልፎ ቅሬታዎች በቃል መቅረባቸው እና የተቋሙ ቅሬታ ሰሚ አካል የውሳኔ ሀሳቦችን ለመስሪያ ቤቱ የበላይ አካል አለማቅረቡ በድክመት መወሰዱን ይገልጻሉ፡፡

ሀወኒ እንደሚናገሩት፤ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቅሬታ ሰሚ አካል አቋቁሟል፤ ጉዳዩን በአግባብ ሰምቶ ውሳኔ መስጠት እና አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዴት እንደሚሰጥ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ለሰራተኞች ስልጠና መስጠቱ በጥንካሬ ተወስዷል፡፡

ማረጋገጫ አለመስጠት፣ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን በጽሁፍ አለማሳወቅ፣የተሟላ ይዘት ያለው አስተዳደራዊ ውሳኔ አለመስጠት እና ቅሬታ ሰሚው ክፍል በተሟላ ባለሙያ አለማደራጀት እንደክፍተት ታይቷል ይላሉ፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር ቅሬታ አሰማም ስርዓት በተመለከተ በአዋጅ የተቀመጠ መመሪያ አለው፡፡ በዚህ አብዛኛው ቅሬታ የሚሰማበት አካሄድ የአስተዳደር አዋጁን ባከበረ መልኩ በመሆኑ ከአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ አንጻር መስሪያቤቱ የላቀ ውጤት አስመዝግቧል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ከድክመት አንጻር አሁንም በስልክና በቃል ቅሬታ እንዲቀርብ የሚፈቅድ መመሪያ መኖሩ ከ1183 አዋጅ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ አቤቱታ አጣሪ ጽህፈት ቤት ለማቋቋም ከወጣው መመሪያ አንጻር ተገቢውን የሙያ ስብጥር አለማሟላት እና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተገቢውን ሕግ አለመጥቀስ እንደ ክፍተት ተወስዷል ይላሉ፡፡

ከጤና ሚኒስቴር አንጻር አቤቱታዎችን በኤሌክትሮኒክስ እና በአካል ማቅረብ መቻል፤ በቃል የሚቀርቡ አቤቱታዎች እንዲቀሩ መደረጉ በጥንካሬ ታይቷል፡፡ የተቋሙ የቅሬታ ሰሚ አካል የተቋቋመ ቢሆንም፤ መቋቋሙ ለሕዝብ ግልጽ አለመደረጉ በክፍተት የታየ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

በክትትሉ ጉምሩክ ኮሚሽን ግምገማ የተደረገበት በአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ብቻ ነው፡፡ ጉምሩክ ኮሚሽን ቀድሞ የተሰጠውን የማስተካከያ ምክረሀሳብ አብዛኛውን ለመፈጸም ችሏል፡፡ ተቋሙ አቤቱታዎችን ሆነ ሌሎች ወደ ተቋሙ የሚላኩ ሰነዶች በኦንላይን እንዲላክ ማድረጉ፣ ዜጎች ያላቸውን አቤቱታ በአማርኛም በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲልኩና ከላኩም በኋላ የመከታተያ መለያ ቁጥር መሰጠቱ በጥንካሬ ተወስዷል ይላሉ፡፡

ከድክመት አንጻር በጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የቅሬታ አጣሪ ሥራ ክፍል መኖሩን የሚያነሱት ዳይሬክተሯ፤ የሥራ ክፍሉን አሰራር ለመወሰን የወጣ መመሪያ የአባላት ስብጥር ምን መሆን እንዳለበት አዋጁ ይደነግጋል፡፡ በዛ መሰረት የሕግ ክፍል የአቤቱታ አጣሪ አባል እንዲሆኑ በመመሪያው ቢቀመጥም፤ ሳይሆን መቅረቱ በድክመት ታይቷል በማለት ይገልጻሉ፡፡

ከመፍትሄ አንጻር፤ ተቋማት ስለአዋጁ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም፤ ወጥነት ባለው መልኩ ተቋማትን የማሰልጠን እና የማነቃቃት ሥራ አሁንም ሊሰራ ይገባል፡፡ በተቋማቱ ያሉ የቅሬታ ማስተናገጃ ክፍሎች በተገቢው የሰው ኃይል እንዲሟሉ መደረግ ይኖርበታል ሲሉ ያስረዳሉ።

ዳይሬክተሯ እደሚገልጹት፤ አዋጁ ያስቀመጣቸው ግዴታዎች እና ድንጋጌዎች በተገቢው መልኩ እንዲተገበሩ የበላይ አመራሩ በቂ ትኩረት በመስጠት የክትትል ስርዓቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ በታዩ ክፍተቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ተቋማት ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፡፡

ቅደመ ስነስርዓት ሳይፈጸሙ እና ከስልጣን ውጭ የወጡ መመሪያዎችን ዜጎች በፍርድቤት ሄደው እንዲሟገቱ ለማድረግ የሚቻለው ዜጎች ስለዚህ ሕግ ግንዛቤ ሲኖራቸው ስለሆነ፤ ለዜጎች ግንዛቤ መስጠት ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You