
ከእለታት በአንዱ ቀን ነው፤ ግን ሩቅ ያልሆነ፣ ባሳለፍነው ወርሃ ሕዳር መገባደጃ ላይ የሆነ፡፡ አንዲት የማስፈጽማት ጉዳይ ስለነበረችኝ አራት እና አምስት ተቋማትን፤ ያውም በክልልም፤ በፌዴራልም ደረጃ ያሉትን የመንግሥት ተቋማት ደጅ የመርገጥ እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ጉዳዬን ላስፈጽም ግን የየተቋማቱን ደጃፍ ከአንድ ጊዜ በላይ መድረስ ነበረብኝ፡፡ በተለይ በሁለቱ ተቋማት የነበረኝ የጉዳይ የማስጨረስ ሂደት ነገሮችን ቆም ብሎ ማሰብ፤ የጉዳይ መግደያ (ማሳለጫ) አማራጮችን መመልከትም ግድ የሚሉ ነበሩ፡፡
“ወፍ እንደ ሀገሯ ትጮኻለች” እንዲሉ፤ እኔም ጉዳዬን ተመላልሼ ማስጨረሱ ጊዜም፣ ጉልበትም፣ ገንዘብም ማባከን መሆኑን ስረዳ፤ እንደየከባቢው አሰራር መራመድ፣ በተለምዶው ‘ጉዳይ ገዳይ’ እየተባሉ የሚጠሩ ግለሰቦችን ማማተር ጀመርኩ። ለነገሩ እነርሱስ መች እስካማትር ጠብቀው፤ ቀድሞውኑ አግባብተው ነግረውና አስረድተውኝ ነበርና ወደነሱው ፊቴን አዞርኩ፡፡
በቃ ከዚህ በኋላ ሁለትና ሦስት ቀናት የተመላለስኩበት ጉዳይ ሁለትና ሦስት ሰዓትን እንድጠብቅ እንኳን አላደረገኝም፡፡ እንዴት ቢባል፤ የእኔም መልስ አላውቅም ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ ያወራሁት እና ጉዳዬን የጨረስኩት ከእነዚህ በተቋማት አካባቢ በማይጠፉት “ጉዳይ ገዳይ” ግለሰቦች አማካኝነት ነው፡፡
እነርሱ ደግሞ እኔ በሁለትና ሦስት ቀን ሊደርሰኝ ያልቻለውን ጉዳይ ፈጻሚዬጋ የመድረስ መንገድ ማፋጠኛ (በእነሱ አጠራር የወረፋ/የተራ) ክፍያ ነው የጠየቁት፡፡ እኔ የተራ ያሉትን ክፍያ ፈጸምኩ፤ እነሱም ጉዳዬን ፈጸሙልኝ ወይም አስፈጸሙልኝ። ይሄ ቀለል ያለው፣ እኔም ከመመላለሱ ይልቅ የተሻለ አዋጪ ይሆናል ብዬ ድካሜን ለመቀነስ ስል ያደረኩት ነው፡፡ መቼም ሲቸግር ከመጥፎም የተሻለውን መጥፎ ይመርጡ የለ፡፡ እንደዛ ነው የሆነው፡፡
ክስተቱ አያሌ ጥያቄዎችን በውስጤ እንዲ መላለሱ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም፣ ምን ያህል ተገልጋይ በዚህ መልኩ አልፎ ጉዳዩን አስፈጽሟል? ምን ያህሉስ ይሄን መንገድ ማለፍ ሳይችል ተንገላቷል? ምን ያህሉስ በጉዳዩ ላይ ቅሬታውን አሰምቶ መፍትሄ አግኝቷል? ወይስ አቤቱታው በዝምታ ታልፏል? በዚህ መልኩ ከመጥፎ መካከል የተሻለው መጥፎ እንዲመረጥ የሚያደርግ የተቋማት ከባቢ ለምን ተፈጠረ? ችግሩስ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አይታወቅምን? ከታወቀስ ለምን ተገቢው እርምትና እርምጃ ሊወሰድ አልቻለም?… የሚሉ መልስ አልባ ጥያቄዎች አዕምሮዬን እረፍት ነሱት፡፡
እኔም ለጊዜው ማለፍ የሌለበት ጉዳዬን በጉዳይ ገዳዮች በኩል ብፈጽምም፤ እነዚህ ረፍት የነሱኝና ያልተፈጸሙ ጥያቄዎቼን ይዤ ማብሰልሰል አላቆምኩም፡፡ አካባቢውን ማጤን ጀመርኩ፣ በጉዳይ ገዳይነት የተሰማሩት አካላትን መለየት ጀመርኩ፡፡ በየተቋማት አካባቢ በሊስትሮ ስም፣ በፓርኪንክ ሰራተኛ ስም፣ በደላላ ስም፣ አለፍ ሲልም በየተቋማቱ ደመወዝ ተከፋይ በሆኑ ሰራተኞች ለምሳሌ በጥበቃ ሰራተኛ ስም፣… በነጻነት ያለ ፍርሃትና መሳቀቅ የሚምነሸነሹ ግለሰቦች መሆናቸውን ተገነዘብኩ፡፡
በተለያየ አጋጣሚ እንደሰማሁትም፤ በየሚዲያው እንዳደመጥኩትና እንዳነበብኩትም፤ እነዚህ ጉዳይ ገዳይ ግለሰቦች፤ ከበር መግቢያ ወረፋ/ሰልፍ መጠበቂያ ካርድ ጀምሮ እስከ ቢሮ ውስጥ ጉዳይ የማስጨረስ ሚናን የሚወጡ ናቸው። የወረፋ ካርድ ይዘው የሻይ እያተረፉ ከሚሸጡት፤ የውስጥ ጉዳይ ገድለው በኮሚሽን እስከሚሰሩት የተሳሰሩም ናቸው፡፡
ደረጃቸው ሊለያይ ይችል ይሆናል እንጂ፣ ይሄን መሰል አሰራር በቀበሌዎች፣ በወረዳዎች፣ በክፍለ ከተማና ዞኖች፣ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች፣ በቢሮዎች እና ፌዴራል ተቋማት በሁሉም ቦታና ሥፍራ እንደ አሸን የፈሉ ናቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል ‘ዜጎች መታወቂያን ከማውጣት ጀምሮ ወደ መንግሥት ተቋማት በሚኖራቸው ጉዳይ ሁሉ እጅ እጃቸው የሚታይበት፤ እጃቸው ካልተፈታም ጉዳያቸው የሚታሽበት አሰራር “በሕግ የተፈቀደ” አስመስሎታል’ የሚል ሀሳብ ከብዙዎች መደመጡ፡፡
አንዳንዴም በወሳኝ ኩነት አገልግሎት መስጫዎች፤ በመንጃ ፈቃድ እና ተያያዥ አገልግሎት ማግኛ ቦታዎች፤ በሆስፒታሎች፤ በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ባሉ አገልግሎቶች፤ ከንግድ እና ገቢ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች፤ በትራንስፖርት እና ሌሎችም የአገልግሎት አካባቢዎች ዜጎች በብዛት ቅሬታም፣ ምሬትም የሚያሰሙባቸው ስለመሆኑም በተደጋጋሚ በየሚዲያዎች ይገለጻል፡፡
በአዲስ ዘመን ጋዜጣም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ የአገልግሎት ችግሮችን፤ በየተቋማቱ የተሰማሩ ጉዳይ ገዳይ አካላትን፤ የዜጎችን ቅሬታና ምሬትን፤ የየተቋማቱን አሰራርና ችግሮችን፤… ደርሶ ሲዘግብ፤ የመፍትሄው አካል ለመሆን ከፍ ያለ ኃላፊነቱን ሲወጣ እንደቆየም በየጊዜው ከጋዜጣው ያነበብኳቸው ዜናዎች፣ ኤዲቶሪያሎች፣ ነጻ ሃሳቦችና አርቲክሎች ጭምር ሕያው ማሳያ ናቸው፡፡
ከዜጎች የቅሬታ ድምጾች እና ከዜና ዘገባዎች ባሻገርም፣ በተለያየ ሁኔታ እና የመድረክ አጋጣሚዎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ስለ ችግሩ ሲናገሩ፤ ችግሩን ለመፍታት ቃል ሲገቡም፤ የችግሩ ተዋናዮችን ሲያስጠነቅቁም፤ ዜጎች ችግሩን ከመፍታት አኳያ ተባባሪነታቸውን በተግባር እንዲገልጡ ሲማጸኑም መስማት የተለመደ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከትናን ዛሬ የችግሩ አይነት እና ስፋት ከፍ እያለ፤ የዜጎች አገልግሎት የማግኘት እድልም “በተፈታ እጅ ልክ እየተመነዘረ” የመጓዝ አዝማሚያው ልምምድ እየሆነ፤ አገልግሎትን በገንዘብ የመግዛት ልምምዱም በሕግ የተፈቀደ እስኪመስል የአደባባይ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡
አንድ ዜጋ የቀበሌ መታወቂያ ወይም የዜግነት መገለጫውን ፓስፖርት ለማውጣት ቀበሌም ሆነ ኢምግሬሽን ሲሄድ፤ ከእሱ የሚጠበቀውን ነገር እስካሟላ ድረስ ጉዳይ ገዳይም ሆነ እጅ መንሻ ከፊቱ ቆመው የይለፍ ፈቃድ ሰጪዎች ሊሆኑበት አይገባም፡፡ አንድ ግለሰብ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅም ሆነ ሃብት ንብረትን ይዞ የሚንቀሳቀስበትን የመንጃ ፈቃድ ማስረጃ ለማግኘት የሚጠበቅበትን እስካሟላ፤ እውቀት፣ አቅምና ክህሎቱን እስከጨበጠ ድረስ የግድ ጉቦ መክፈል አይጠበቅበትም፡፡
አሁን አሁን ግን እንዲህ አይነቶቹም ሆኑ ሌሎች የመንግስታዊ አገልግሎቶች አንድም በጉዳይ ገዳይ ስም በተሰየሙ ግለሰቦች፤ ካልሆነም በቀጥታ ለጉዳይ ፈጻሚዎች በሚለገስ የእጅ መንሻ ላይ ተመስርተው የሚፈጸሙ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ሕዝብ እና መንግስት መካከል ያለውን ትምምን የሚሸረሽር፤ ሕዝብ በመንግስት ተቋማት ላይ ያለውን የባለቤትነትና የተገልጋይነት መንፈስ የሚያዳክም ስለመሆኑ እማኝ መጥቀስ አያሻውም።
በዚህ ረገድ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወነ የዳሰሳ ምልከታ በየተቋማቱ እንዲህ አይነት ችግሮች ስለመታየታቸው በክብርት ከንቲባዋ አንደበት ሲነገር ሰምተናል፡፡ ከንቲባዋ ይሄን ችግር ባሳወቁበት ወቅት የየተቋማት ኃላፊዎችን አስጠንቅቀዋል፤ ኃላፊነታቸውን መወጣት ካልቻሉና ሕዝቡን ለማገልገል ቁርጠኝነቱን ካጡ በራሳቸው ጊዜ የኃላፊነት ወንበራቸውን እንዲለቁ መክረው፤ ይሄን ማድረግ ባልቻሉና በሕዝብ ላይ የሚቆምሩ ሲገኙም ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበውም ነበር፡፡
እንደ ኃላፊዎች ሁሉ በየቦታው ሕዝብን እንዲያገለግሉ የተቀመጡ ምንደኛ ሰራተኛና ባለሙያዎችም፣ በሕዝብ ገንዘብ እየኖሩ መልሰው ሕዝብን ለመበዝበዝና ለማማረር የሚታትሩበትን አካሄድ ሊያርሙ፤ ካልሆነም አስፈላጊው እርምትና ማስተካከያ እንዲሁም እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡
ምክንያቱም በዚህ መልኩ ራሳቸውን በገንዘብ የሚለኩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ክፉ ምግባር፤ በብዙ መልኩ ለሕዝቦች አገልግሎት ራሳቸውን ሰጥተው የሚሰሩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ስምና ገጽታም የሚያቆሽሽ ነው፡፡ በመሆኑም ይሄን አይነት አስቀያሚም፣ አስነዋሪም ተግባር በመንግስት ተቋማት ሊኖር፤ የሕዝብን እምነትና የተገልጋይነት ስሜትም እንዲሸረሽር እድል ሊሰጥ አይገባም፡፡
በዚህ ረገድ እንደ ከተማ አስተዳደር ችግሩን ከመፍታት አኳያም ጅምር ሥራዎች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጅምር ሥራው ከችግሩ ስፋትና አይነት እንዲሁም ተለዋዋጭነት አኳያ ብዙ የሚቀረው እና ከፍ ያለ ቁርጠኝነትንም የሚጠይቅ ነው፡፡ እናም እንደ ከተማ አስተዳደር ያለው ጅምር ለሌሎችም ዓርዓያ ሊሆን በሚያስችለው መልኩ ሊጠናከር፤ አስተማሪም ሆኖ የከተማዋን ሕዝብ ከአስተዳደሩ ጋር ያለውን ትምምን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆን ይጠበቅበታል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ከተማ ያለውን በማሳያነት ለመጥቀስ ሞከርኩ እንጂ፣ ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት ችግሩ ደረጃው ቢለያይም በሁሉም አካባቢዎች፣ በሁሉም እርከኖችና ተቋማት የሚታይ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር በመንግሥታዊ አገልግሎቶች ላይ ስብራትን የሚፈጥር፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱም ላይ አሉታዊ ጫናን የሚያሳድር መሆኑ እሙን ነው፡፡
የብልፅግና ፓርቲም፣ በትረ መንግሥቱን ጨብጦ ሀገር እንደሚመራ መንግስት ችግሩን ተገንዝቦታል፡፡ በቅርቡም በተለያዩ አካባቢዎችና ተቋማት ላይ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የፈተሸበትን የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡ በዚህ የዳሰሳ ጥናት መሰረትም በተለይ በተቋማት ለሚታዩ የአሰራር ችግሮችና የሙስና ጉዳዮች መበራከት አቅም የሆኑ “ምስለ ተገልጋይ” ግለሰቦች በእጅጉ መበራከታቸውን መለየት ችሏል፡፡
ይሄ ደግሞ ዜጎች በተቋማት አገልግሎትን ፈልገው ሲሄዱ፣ አገልግሎት የሚያገኙት አገልግሎቱ ስለሚገባቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለአገልግሎቱ በሚሰጡት ጉቦ ወይም እጅ መንሻ ልክ ስለመሆኑ፤ ለዚህም ጉዳይ የሚያሳልጡ ምስለ ተገልጋዮች ስለመኖራቸው ደርሶበታል፡፡ እንደ ፓርቲም በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍ ያለ ውይይት ተደርጎ ችግሮቹን ማረምና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ማጥራት በሚያስችሉ አሰራሮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ይሄ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ፣ ሀገርን ከሚመራ መንግስትና ፓርቲ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ እንደ ሀገር ቀደም ሲል የነበሩ ከፍ ያሉ (ግራንድ የሚባሉ) የሙስና ተግባራት ሀገርን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉ ይታወቃል፡፡ አሁን ላይ በዛ ልክ የሚጠቀስ የሙስና ተግባር አለ የሚል መረጃ ባይኖርም፤ በምስለ ተገልጋይ አንጻር እየተስፋፉ የመጡ ጥቃቅን የሙስና ልምምዶች እያደጉ መሄዳቸው፤ ድምር ውጤታቸውም የዜጎችን ምሬት ወልዶ ወደ ሌላ ችግር ማምራታቸው አይቀሬ መሆኑንም የተገነዘበም ነው፡፡
ይሄ ጅምር ደግሞ ችግርን ከመለየት የተነሳ እንደመሆኑ፣ የችግሩን ሃምሳ በመቶ እንደመፍታት የሚቆጠር ይሆናል፡፡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡም ሌላ የችግሩ ማቃለያ አቅም ነው። ይሁን እንጂ ችግርን መለየት እና አቅጣጫ ማስቀመጥ ብቻውን ከችግር አያወጣም፡፡ በጥናት የተለዩ ችግሮች ተለቅመው መፍትሄ እንዲያገኙ፣ በተግባር የሚገለጥ ርምጃ ያስፈልጋል፡፡
ምክንያቱም ዛሬን በምስለ ተገልጋይ ገጽ ውስጥ የጀመረ የሙስና ልምምድ፣ ነገ ከፍ ወዳለው እና ሀገርን ዋጋ ወደሚያስከፍለው ትልቁ የሙስና እና የኮንትሮባንድ መስመር መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡ “ምነው በእንቁላሉ ጊዜ…” እንዲሉ፤ ከወዲሁ መሰል እንቅስቃሴና ተግባራትን መቅጨት ካልተቻለ፤ ዛሬ ላይ የዜጎችን እጅና ኪስ በመመልከት የተጀመረ ልምምድ፣ ነገ ከፍ ወዳለው የመንግሥት ካዝና ማማተሩና እጅ መስደዱ አይቀሬ ነው፡፡
አሁን ላይ እየተነገራቸው የማይሰሙ፤ የሕዝብ ቅሬታና ብሶት የማያዳምጡ፤ የአገልጋይነት መንፈስን ሳይሆን የእጅ መንሻ ፍላጎትን ያዳበሩ፤… ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እዚህም እዚያም መበራከት፤ ነገ የፓርቲውን ሕልውና በጥቅም የሚለውጡ ግለሰቦች ወደመሆን ላለመሸጋገራቸው ዋስትና አይኖርም፡፡ በመሆኑም ብልፅግና እንደ መንግሥትም፣ እንደ ፓርቲም የጀመረውን ከፍ ያለ የለውጥ እና የብልፅግና ጉዞ፣ ጥቃቅን ጥላሸት ከሚያንኳኩበት ግለሰብና አንጃዎች ራሱን ሊያጠራ፤ በጥናት የለየውንም የመልካም አስተዳደር ችግር፤ የጥቃቅን ሙስናና ሙሰኝነት ልምምዶችን ከወዲሁ ፈር ሊያስይዝ ይገባዋል፡፡
ይሄን ማድረግ ደግሞ የተጀመረውን እና ከፍ ብሎ እየተጓዘ ያለውን ሀገርን የማጽናት እና ለሁለንተናዊ ብልፅግና የማብቃት መንገድን እውን የማድረግ ብቻም ሳይሆን፤ ለሕዝብ የገቡትንም ቃል መፈጸም ነው፡፡ ምክንያቱም፣ እንደ ፓርቲ ለመንግሥትነት በመወዳደር ሂደት ውስጥ ብልፅግና እንደ ፓርቲ አንዱ ለሕዝብ የተገባው ቃል፡-
“ፓርቲያችን የሕዝብ አስተዳደር ወይም ሲቪል ሰርቪስ ቅልጥፍናና ብቃት በየጊዜው እየጨመረ እንዲሄድ ያልተማከለ እና የተቋማቱን ባህሪያት ያገናዘበ፣ በጥናትና በእውቀት የሚመራ የለውጥ መርሃ ግብር በየተቋማቱ እንዲተገበር በማድረግ በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዜጎች ያላቸው እርካታና መተማመን እንዲጨምር በቁርጠኝነት እንሰራለን” የሚል ነው፡፡
በመሆኑም እንደ መንግስት በየደረጃው ያለውን ሲቪል ሰርቪስ ወይም የሕዝብ አስተዳደር እየፈተሸ ማረም፤ በተለይም እንደ ፓርቲ በቅርቡ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ያመላከታቸውን ዘርፈ ብዙ እና መልከ ብዙ የሙስና ተግባራት በእንጭጩ እንዲገቱ የማድረግ ቆራጥ ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በዚህም በልማትና ሌሎችም መስኮች የተገኙ ከፍ ያሉ ውጤቶች በላቀ መልኩ ሰው ተኮር ሆነው እንዲዘልቁና ለውጤት እንዲበቁ፤ ከፍ ያለ የሕዝብ እምነትና ተሳትፎዎችን እንዲያረጋግጡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2017 ዓ.ም