የመግባቢያ ሰነዱ የንግዱን ዘርፍ ማነቆዎች በመፍታት ሰው ተኮር ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፡የመግባቢያ ሰነዱ በንግዱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ሰው ተኮር ልማትንና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ፡፡ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠየቀ ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚኖርን ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ትናንትና ተፈራርመዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሐኪም ሙሉ (ዶ/ር) በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ያለውን ሁሉን አቀፍ ምክክር በማጠናከር እየተሠራ ያለውን ሰው ተኮር ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገትን እውን ለማድረግ የሚረዳ ነው፡፡

ስምምነቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚኖርን ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ ለማጠናከር በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል፡፡

መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት ለግሉ ዘርፍ ምቹ የሥራ ምሕዳር በመፍጠር፤ ትኩረትና ድጋፍ በማድረግ የሀገሪቱ ኢኮኖሚን እያሳደገ ይገኛል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢኮኖሚውን ይበልጥ ለማሳደግና እየተሠራ ያለውን ሰው ተኮር ልማት እውን ለማድረግ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን ግንኙነት እያጠናከረ ነው ብለዋል፡፡

የተፈረመው ስምምነት በንግዱ ዘርፍ አካታችነት እንዲስፋፋ፤ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃና ተደራሽነት እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው ሲሉም ገልጸዋል። ቀልጣፋና ፈጣን የኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲመዘገብ፤ በንግዱ ዘርፍ እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ ለማድረግ፤ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡

በንግዱን ዘርፍ እያጋጠሙ ላሉ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት፤ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፤ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንዲሻሻሉ በማድረግ፤ ሰው ተኮር ልማትንና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት በማጠናከር እየተሠራ ያለውን ሰው ተኮር ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል።

መንግሥት የግሉን ዘርፍ የሚያበረታቱና ምቹ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ሕጎችና ፖሊሲዎችን በማሻሻል፣ የተሻሻሉ ሕግና ፖሊሲዎች አፈፃፀማቸውን በመከታተል አስተማማኝ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር ያለውን የምክክር መድረክ በማጠናከር መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጥ፤ የግሉ ዘርፍም በኢኮኖሚው እድገት ያለውን ሚና እንዲወጣ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመልክተዋል፡፡ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You