‹‹በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ ሆነን መቆም አለብን›› – ኡስታዝ ጀማል በሽር የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ መሥራች

ኡስታዝ ጀማል በሽር አሕመድ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ተጠቃሚነት እና ባለቤትነት እንዲሁም በዓባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በማሳወቅ ይታወቃሉ። በበርካታ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብና የራሳቸውን “ኪንግስ ኦፍ ዓባይ” ሚዲያ በማቋቋም በአረብኛ ቋንቋ በአረብ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ላይ በመሞገት ይታወቃሉ። በዚህም ሥራቸው የዓባይ ተሟጋች የሚል እውቅናን አግኝተዋል።

ኡስታዝ ጀማል በሽር ከሳዑዲ አረቢያ መዲና ኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሊሎጂ እና የታሪክ የትምህርት ክፍል ወስደዋል። ኡስታዝ ጀማል ከሚሠሯቸው ሥራዎች ባለፈ የሃይማኖት መምህር፤ የሙስሊም አሜሪካን ሶሳዩቲ ምክትል ኢማም በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። የዛሬው እንግዳችን አድርገናቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- ስለሀገር ያልዎት አመለካከት ምን ይመስላል ?

ኡስታዝ ጀማል፡- ሀገርን መውደድ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪ ነው። መወለድ፣ አብሮ መኖር ለሀገር የሚኖረን ስሜት ይገነባል። ትልቁም ሥራም ያንን ጠብቆ ማቆየት። ሰው ሀገሬ ብሎ በሚኖርበት ቦታ ላይ ሌላ ባዕድ ፖለቲካም ይሁን ሌላ ጠላት ገብቶ እንዳያጠፋው መጠበቅ ይገባል። ብዙ ጊዜ ሀገራቸውን እንደማይወዱ የሚናገሩ ሰዎች ምናልባት የሆነ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ አመለካከት እንዲኖረን በማድረግና በመወያየት መፍታት ይቻላል።

በየትኛውም ሀገር ቢሆን የማይጎረብጥ ነገር የለም። ቤታችንም ቢሆን የማይመች ነገር ይኖረዋል። ግን ቤታችን ብለን ከሚመቸው ጋር ራሳችንን አስማምተን እንኖራለን። በሀገር ደረጃ ደግሞ ስንመጣ ያሉብንን ችግሮች እንዴት እንደምንፈታ እየተነጋገርን የምንኖርባት ናት።

በእኛ ጊዜ ቴክኖሎጂ ብዙም የተስፋፋበት ስላልነበር አሁን ላይ የምንመለከታቸው በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች እና ማህበራዊ ገጾች ሳንወጠር በነፃነት ነበር ያደግነው ማለት እችላለሁ። ሌላኛው በመጠኑም ቢሆን ከሱስ የጸዳ ጊዜ ነበረን። ምክንያቱም ሰፊ መጫወቻ ሜዳዎች ለልጆች የሚሆኑ ምቹ ሥፍራዎችም ነበሩ።

እነዚህ የአስተዳደግ ሥርዓቶች የሰው ልጅ ማንነትን ለመቅረጽ በሚደረገው ሂደት ውስጥ እንደ ግብዓት በማገልገል ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው። ቤተሰብም ሆነ ጎረቤት የልጆችን ባህሪ በመቅረጽ ያለው ሚና ቸል ሊባል የሚገባው አይደለም።

ሰልጥነናል በሚሉ ሀገራት በትምህርት ተቋማትም ሆነ በቤተሰብ ሊያወርዱ የሚፈልጉት ሥርዓት ስላለ ሌላ ተቀናቃኝ እንዲኖር አይፈልጉም። ቤተሰብም ጭምር የልጆችን ባህሪ በመቅረጽ ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው እና ጫና እንዳያሳድር ያደርጋሉ።

ይህ ሥርዓት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እመኛለሁ። ያለን ማህበራዊ መስተጋብር በመተባበር እና በመተጋገዝ ላይ አንዱ አንዱን በማረቅ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ማህበረሰብም ሆነ ወላጅ ልጆችን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ ውስጥ ያለውን ቦታ ማስቀጠል ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ምን ለየት ያደርጋታል ብለው ያስባሉ?

ኡስታዝ ጀማል፡- ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከሌሎች ሀገራት የተለየች ናት ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ሌሎች በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ባሕላቸውም ሥርዓታቸው በብዙ መንገድ ተቀይጧል። ለምሳሌ ግብጽን ብናነሳ ከስምንት ጊዜ በላይ በቅኝ ግዛት ውስጥ የነበረች ሀገር ናት። ግብጾች በእነዚህ ጊዜያት አረብ ናቸው አይደሉም የሚል ክርክር እስከሚነሳበት ድረስ ባሕላቸው እና ማንነታቸው ተቀይጧል። በግብጽ ውስጥም አረብ አይደለንም ብለው የሚያምኑ ዜጎች ተፈጥረዋል።

ኢትዮጵያ ጋር ስንመጣ ግን የሰው መገኛ ነን ነው የምንለው፤ የራሳችንን ፊደል ያለን፣ ቋንቋችን የተጠበቀ ነው። የውጭ ወራሪን በአንድነት ታግሎ በማሸነፍ የምንታወቅና አስደናቂ የሆነ ተፈጥሯዊ ሀብት ያለን ሕዝቦች ነን። በርካታ ሀገራትን ተዘዋውሬ ለማየት እንደቻልኩት ለመኖር ምቹ የሆነ ወቅቶች በጣም ጥቂት ናቸው። እኛ ሀገር ግን ሁሉም ወራት ምቹ ናቸው። በጣም ምቹ የአየር ሁኔታ ነው ያለን፤ ከሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ዜጎችም የሚቆዩበትን ጊዜ እስከማራዘም የሚደርሱትም ለዚህ ነው።

እንደ ሀገር በቅኝ ያልተገዛን እንደመሆናችን ግሎባላይዜሽን በምንለው እሳቤ አልተዋጥንም። ያለንን ባሕል እና እሴት ጠብቀን እንድንቆይ ረድቶናል። ይህም በአሁን ሰዓት በለጸጉ በምንላቸው ሀገራት ላይ ያሉ የባሕል ወረራዎች ወደሀገራችን እንዳይገቡ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንደ ሀገር እነዚህን እሴቶቻችንን ጠብቀን በቴክኖሎጂ ዘምነን ሀገራችንን ማሳደግ እንችላለን።

የተለያዩ ትርክቶችን ፈጥሮ እርስ በእርስ የማጣላት ግጭቶች ውስጥ እንድንገባ የሚያደርግ፤ ሥልጣንን በምርጫ ሳይሆን በጠመንጃ ለማምጣት የሚያስቡ አካሄዶች ታርመው ሌሎች ልማቶች ላይ ማተኮር ይገባናል።

አዲስ ዘመን፡- የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ ለውጭው ዓለም ለማሳወቅ እንዴት ተነሳሱ?

ኡስታዝ ጀማል፡- ብዙዎቻችን ለአረቦች ያለን አመለካከት ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነው። ሃይማኖት ደግሞ በፖለቲካ በኩል ያሉ ሃሳቦችን እንድናይ አያደርገንም። በመዲና ኢስላሚክ ዩኒቨርሲቲ በምማርበት ወቅት አንድ ግብጻዊ የዓባይ ልጅ እያለ ሲተዋወቀኝ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። ምክንያቱም ስለ ዓባይ እውቀት አልነበረኝም። ቢኖረኝም ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞራል፣ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው የሚሉ የወቀሳ ተረትና ምሳሌዎችን እንጂ ዓባይን ተጠቅሜ እና ባለቤት ነኝ የሚል ቁርኝት አልነበረኝም። ከዚህ ቀደም ከዓባይ ጋር በተያያዘ የተሠራውን ሥራ በጂኦ ፖለቲካዊ መንገድ የማይበት መነጽር እምብዛም አልነበረም። እንደ ሀገር በዚህ ጉዳይ ላይ በትምህርት ሥርዓታችን ላይ ምንም አልሠራንም።

በግብጽ ሕገ-መንግሥት ላይ አንድ መንግሥት በሚሾምበት ወቅት ያለ ምንም ድርድር ሊያስከብራቸው ከሚገቡ የብሔራዊ ደህንነቶች አንዱ ዓባይ ነው። አንድ ህጻን ግብጻዊ ስለ ዓባይ ጠንቅቆ ያውቃል። እያንዳንዱ ግብጻዊም ከዓባይ ጋር ያለው ቁርኝት የጠበቀ እንዲሆን ለረጅም ዘመን ሰርተዋል። እኛ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ጠልቀን በማናውቅበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ይፋ ሆነ። ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚስፈልገው ገንዘብ በትክክል ለተባለው ዓላማ ይውላል የሚለው ጥያቄ የሆነባቸው ኢትዮጵያውያን ነበሩ። አንዳንዶች ደግሞ ጉዳዩ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን በመገንዘብ ከግድቡ ጎን የቆሙ ነበሩ።

ለውጡ ከመጣ በኋላ የሕዳሴ ግድብ የአንደኛ ውሃ ሙሌት ሊከናወን ሲል ጋዜጠኛ መሐመድ አልአሩሲ በአንድ አልሸርቅ የሚባል ሚዲያ ላይ ውይይት ሲያደርግ ግብጾች ያነሱት የነበረው ሃሳብ እይታዬን ቀይሮታል። የአረቡን ማህበረሰብ በራሳቸው ጎን ለማሰለፍ ኢትዮጵያ ለአረብ እና ለክርስቲያኖች ጠላት እንደሆነች ሲያነሱ ተመለከትሁ። አረብኛ ቋንቋን ከሃይማኖት ጋር በማገናኘት የነበሩ ጥቂት ክፍተቶችን በማግነን ለራሳቸው ግብዓት እንደ ትርክት ተጠቅመውበታል። እውነት የሚመስሉ መረጃዎችን ለውሸት ፈጠራ በመጠቀም አረብኛ ቋንቋ የሚሰሙ የሙስሊሙን ዓለም ለመያዝ እኛን የሙስሊሙ ጠላት አድርገው መፈረጅ አንዱ መንገድ ነበር።

ሌላኛው መንገድ የነበረው በእኛ እንቅስቃሴ ውስጥ እስራኤል እንደምትደግፈን ያነሱ ነበር። ይህም በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል ያለውን ሃይማኖታዊ ልዩነት በመጠቀምና ልዩነቱን ማስፋት የአረቡን ዓለም ከፍልስጤም ጎን እኛን ደግሞ ከእስራኤል ጎን አድርገውታል። ነገር ግን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው እነሱ ናቸው።

ሌላኛው የዓባይ ውሃ ሙሉ ለሙሉ የራሳቸው ውሃ እንደሆነ አድርገው ነበር በውይይቱ ላይ ሲያወሩ የነበሩት። የሃሳባቸው መነሻ በራሱ ውሃው የግብጽ ነው የሚል ነበር። የተለያዩ ታሪኮችን በምናነብበት ወቅት የዓባይ ውሃ ምንጭን ለመያዝ እንደ ጉንደንት እና ጉራ ያሉ ጦርነቶች መደረጋቸውን ማንሳት እንችላለን። በጦርነት ማድረግ ያልቻሉትን ደግሞ ውስጥ ለውስጥ ያለውን ሰላማችንን በማተራመስ፤ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠሩ ነበር።

ኢትዮጵያ በለጸገች ሲባል የአንድን ግብጻዊ ውሃ የጠጣች ስለሚመስላቸው ያላቸው እድል እቺን ሀገር በቻሉት አቅም ሁሉ ማቆርቆዝ ነው። ይህንን ስመለከት የመጀመሪያው ሥራ መሆን ያለበት ኢትዮጵያዊያን ስለ ዓባይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ነበር። ይህ ማለት ለአረብ ጥላቻ ይኑረን ሳይሆን ያለውን የፖለቲካ ሂደት ማወቅ እና ምክንያታዊ መሆን ይገባናል የሚል ነው።

ግብጾች የሚለቁት የተሳሳተ መረጃ ዓለም ስለኢትዮጵያ ያለው እይታ የተሳሳተ እንዲሆን አድርጎታል። ግብጾች የሚለቋቸው መረጃዎች ከእውነት የራቁ እና አብዛኛውን ሰው ለማደናገር ተብለው የሚሠሩ በመሆናቸው ትክክለኛውን እውነታ ለማሳወቅ መረጃዎችን እየተረጎምኩ ማቅረብ ጀመርኩ። ይህንንም ሥራዬን የተመለከቱ ሚዲያዎች ለቃለ መጠይቅ ጋበዙኝ። በኋላም እንደ አልጀዚራ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ለቃለ መጠይቅ እና ውይይት ጥያቄ አቀረቡልኝ። የአረብኛ ቋንቋን በመናገርም ሆነ በመረዳት ችሎታ ካላቸው ኡስታዝ መሐመድ አልአሩሲ እና ሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በመሆን በስፋት ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ መታየት ጀመርን።

ግብጻዊያን በዓባይ ጉዳይ ላይ ከራሳቸው መገናኛ ብዙሃን አልፈው ሌሎች ሚዲያዎችን ተጠቅመው ሃሳባቸውን ይገልጻሉ። ለአብነት ሳዑዲ የሚገኘው አሸርቅ ጣቢያ አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ግብጻዊያን ናቸው። የሳዑዲ ፖለቲካ ከእነርሱ ጋር ባይሄድ እንኳን እንደምንም ሸራርፈው የራሳቸውን ሃሳብ ማንጸባረቅ ይፈልጋሉ። ሌላኛዋ ኳታር ስትሆን ከእኛ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ሀገር ናት። ነገር ግን በዚያ ያሉት የአልጀዚራ ሚዲያ አብዛኞቹ ግብጻዊያን በመሆናቸው የእነሱ ሃሳብ ጎልቶ እንዲታይ ሆኗል።

በግብጻዊያን እይታ አረብኛ ቋንቋን መናገር የሚችሉ ሞጋች ባለሙያዎች የሉም የሚል ድምዳሜ ነበራቸው። በራሳቸው የአረብኛ ቋንቋ የሚሞግታቸውን ቅዱስ ቁርዓን ላይ የተቀመጡ አንቀጾችን እየጠቀሰ የሚሞግታቸው ሰው ማግኘታቸው ብዙዎችን አስገርሞ ነበር። ለዚህም ማሳያው ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ በምንሠራበት ወቅት የሃሳባችን ደጋፊ የነበሩ አረቦች ተሳታፊ ሆነው አግኝተናል። በምንሠራቸው ፕሮግራሞችም የኢትዮጵያን አቋም ተረድተው የደገፉን ግብጻዊያን ነበሩ።

አዲስ ዘመን፡- ግብጽ የዓባይን ውሃ በተመለከተ የምታነሳቸው የባለቤትነት ጥያቄዎች፣ ኢትዮጵያን መብት እስከ ማሳጣት ድረስ የሚሄዱ ናቸው። ይህ ከምን የመጣ ነው ብለው ያምናሉ?

ኡስታዝ ጀማል፡- አንድን ንብረት በውሰት ለሰዎች ከሰጠን በኋላ አንዳንድ ሰዎች ብዙ ጊዜ እነርሱ ጋር ሲቆይ የራሳቸው ይመስላቸዋል። ወይም ሲቆይ የእናንተ እንዳይመስላችሁ እንላቸዋለን። ግብጾች የዓባይ ውሃ ላይ ያላቸውን የባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ በታሪክ አጋጣሚ ለረጅም ጊዜ የዓባይን ውሃ መጠቀማቸውን በማንሳት እንደ ታሪካዊ መብት አድርገው ይቆጥሩታል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ስምምነቶችንም እንደ ማስረጃ ያነሳሉ።

በዚያን ወቅት የነበሩ ስምምነቶችም ቢሆኑ ሕጋዊ  አልነበሩም። የመጀመሪያው ስምምነት እ.አ.አ በ1902 ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን የተደረገ ስምምነት ነው። ንጉሱ በስምምነቱ ላይ ሙሉ በሙሉ አልዘጋውም ነው ያሉት። ሁለተኛው ስምምነት በ1929 የተደረገ ነው፤ በቅኝ ገዢዎች የተፈረመ ስምምነት ነው። ጣልያን ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ አፍሪካን በቅኝ ግዛት በሚይዟቸው ሀገራት ላይ የጥቅም ክፍፍል አድርገዋል። ከተስማሙባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው የዓባይ ውሃ ነበር። እንግሊዝ በወቅቱ በሱዳን እና በግብጽ በስፋት ጥጥ ያመርቱ ስለነበር የዓባይ ውሃ ላይ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ግብጽ የበላይነት እንዲኖራት አድርገዋል። ነገር ግን ይህ ውሳኔ በቀኝ ገዢዎች የተፈረመ እና ኢትዮጵያንም ሆነ ግብጽን ያገለለ በመሆኑ ተቀባይት የለውም።

ሌላኛው ስምምነት ሀገራት ነፃነታቸውን ካወጁ በኋላ በ1959 በግብጽ እና በሱዳን መካከል የተደረገ ስምምነት ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ስምምነቱ ላይ ለመካተት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አልነበረውም። በስምምነቱም ግብጽ 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ፤ ሱዳን 18 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ክፍፍል ሲያደርጉ ሌላውን 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይትነን በሚል የውሃው ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን አግልለዋል። የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግም ታሪካዊ መብት የሚለውን እንደማለሳለሻ ቢጠቀመውም እንደ ሕግ የተቀመጠ ግን አይደለም፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ሕጋዊ ናት።

በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል የተፈጠሩ ክስተቶች በሌሎች ሀገራት መካከል የተፈጠሩ ናቸው። እንደ ምሳሌ የሌሴቶና የደቡብ አፍሪካን ስምምነት ነው። ሌሴቶ ለደቡብ አፍሪካ ውሃ ታቀርብላታለች። የባለቤትነት ጥያቄ ላይ ሙግት በሚጀመርበት ወቅት ደቡብ አፍሪካ ለምታገኘው ውሃ በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ እንድትከፍል ተደርጓል። እነዚህን ተሞክሮዎች መውሰድ እና የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል። ግብጽ ውሃው እንደሚስፈልጋት እኛም የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙ ዜጎች አሉን። አማራጭ የልውውጥ መንገዶችን ማሰብ ያስፈልጋል። እነሱ በሶላር የሚጠቀሟቸው ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት አላቸው። እሱን ሸጠው ለእኛ መክፈል ይችላሉ። እኛ ባሕር የለንም እነርሱ ግን አላቸው። ስለዚህም ውሃ ስንሰጥ በምትኩ የምናገኘው ነገር መኖር አለበት።

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ግብጻዊያን የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የሆነ በጋራ የመልማት እና የማደግ ጥያቄ እየተረዱ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ግብጽ ጦርዋን በማስጠጋት ጭምር ከአንዳንድ ሀገራት ጋር ስምምነት በመፍጠር ላይ ትገኛለች። ይህንን እንዴት ያዩታል ?

ኡስታዝ ጀማል፡- ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ እንዳትጠቀም ብትጠቀም እንኳን ከኃይል አቅርቦት የዘለለ እንዳይሆን ለእርሻ እና ለሌሎች አገልግሎቶች እንዳንጠቀም ስጋት እንዳላቸው በተለያየ ጊዜ ያነሳሉ። የዓባይን ወንዝ ለመጠቀም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንዳይጀመር፣ ከተጀመረ በኋላም የውሃ ሙሌቶች እንዳይደረግ የማደናቀፍ ሂደቶችም ነበሩ። አሁን ላይ ደግሞ ከውሃው መጠቀም ያለብንን ያህል እንዳንጠቀም ይፈልጋሉ። ይህንን ማሳየት የሚቻለው በሥራ ነው፤ ከውሃው መጠቀም ያለብንን ተጠቅመን ማሳየት ስንችል ነው፤ ያኔ የአብረን እንሥራ ጥያቄው ይመጣል።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን የውሃ ሀብት አጠቃቀም እንዴት ይመለከቱታል ?

ኡስታዝ ጀማል፡- በተለያዩ ጊዜያት የውሃ ሀብት እንዳለን ይገለጻል፤ ስማችን በውሃ ሀብት በጣም የገነነ ነው። እኛ ግን በአብዛኛው ዝናብ ላይ ብቻ ተንተርሰን ነው ያለነው። በትክክል ውሃ አለን ወይ የሚለው በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። በቁጥጥር ውስጥ ያልሆነ በቴክኖሎጂ ያልታሰረን ሀብት አለን ማለት ይከብዳል። ለተወሰኑ ዓመታት ዝናብ ባይዘንብ ኢትዮጵያ ውሃ አይኖራትም። ግብጻዊያን ግን በዓለም ትልቁ በሆነው ሀይቅ ላይ 168 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዘዋል። ይህ ሀይቅ ያለምንም ዝናብ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት መኖር ያስችላቸዋል።

እኛ ያለን የውሃ ሀብት ግን ጥቂት ነው፤ እሱንም ወደሌሎች አካባቢዎች ማምጣት ከባድ ነው። የግድብ አስፈላጊነቱ የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። ሀገርን እንደ ሀገር ታላቅ የሚያሰኛት ያላት የውሃ ሀብት አልያም የግድብ ብዛት ነው። አሜሪካን ብናነሳ በትንሹ እስከ 90 ሺህ ግድቦች አሏት። የውሃ ሀብትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ስጋት የለባቸውም፤ የበለጸጉ ሀገራት መገለጫም ነው። ውሃን በተገቢው መንገድ ከትሮ የራስ ማድረግ፤ ምን ያህል ጊዜ የምንጠቀምበት ውሃ አለን የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል። አንዳንድ ጥናቶች የከርሰ ምድር ውሃችን አደጋ ላይ መሆኑን ያሳያሉ። በድሮው ጊዜ ከዝናብ የምናገኘውን ውሃ እንኳን በማጠራቀም መልሰን ጥቅም ላይ የምናውልበት ልምድ አሁን ላይ እየቀነሰ መጥቷል። በመሆኑም የውሃ አያያዝ ሥርዓታችንን ማስተካከል ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች ተጠቅማ ያሉባትን ችግሮች ለመቅረፍ እና ለማደግ ምን ማድረግ ይገባታል ?

ኡስታዝ ጀማል፡- ግብጽ በአብዮት ያለፈች ሀገር ናት። በተለያዩ ጊዜያት ላይ በርካታ መሪዎችን አስተናግዳለች። ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የግብርና ምርቶቿን አታቆምም። በእርሻ አንደኛ ናቸው። የእኛን ውሃ እና አፈር እየተጠቀሙ ወደሌሎች ሀገራት ምርቶቻቸውን ይልካሉ። ሳዑዲ እና ኢማራቶችን ማባበያ ሊሆን የሚችል የፖለቲካ ጫና ሊያሳድር የሚችል የመመገብ ሥራ ይሠራሉ። የሚዘሩት ሩዝ አውሮፓ ድረስ ይላካል። ግብጻዊያን ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በተመለከተ የሚያነሱት ብዙ ዝናብ ይዘንብላችኋል፤ ብዙ ወንዝም አላችሁ ነው። በእኛ እና በግብጻዊያን መካከል ያለው ልዩነት ወደ ሀገራቸው የሚገባውን እያንዳንዱን የውሃ ሀብታቸውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ማወቃቸው ነው።

ወንዝ አለን ነገር ግን ቤታችን ውስጥ ውሃ የለም። ይህንን ቀይረን እንዴት የውሃ ባለቤት መሆን እንችላለን የሚለው ላይ መሥራት አለብን። ያሉንን የውሃ ሀብቶች ወደ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መቀየር ላይ መሥራት አለብን። ለዚህም እንያንዳንዱ ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ባለቡት የሥራ ዘርፍ ላይ በሀቅ በማገልገል ከሙስና እና ብልሹ አሠራር የጸዳ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፤ ይህንን ማድረግ ከቻልን ሌሎች ሀገራት የደረሱበት የኑሮ ደረጃ ላይ የማንደርስበት ምክንያት የለም ።

አዲስ ዘመን፡- ኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል?

ኡስታዝ ጀማል፡- ትልቁ ነገር በቅድሚያ የራሳችን ዜጎች ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ነው። የነበረውን የተዛባ አመለካከት ከማስተካከል አንጻር ጥሩ ውጤት ማምጣት ችለናል። ሁለተኛው በአረቡ ዓለም ላለው ማህበረሰብ በራሳቸው የመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በራሳችን ጣቢያ ላይ የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ማሳወቅ ችለናል ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ማሳያው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር በጥቂት ቀናት ውስጥ ለሕዳሴ ግድብ መሰብሰብ ተችሏል። ከዚህ ውጭ በሌሎች ሀገራት የሚኖሩ ኢንቨስተሮች በቁጭት ወደ ሀገራቸው ገብተው እንዲሠሩ አነሳስቷቸዋል። አሁን ላይ በሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያ አጀንዳው ለኢትዮጵያውያን እንዲቀርብ ማድረግ ችለናል።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የተደረገው የአሜሪካ ምርጫ የኢትዮጵያ እና የግብጽ ጂኦ ፖለቲካል ስምምነት ላይ የሚፈጥረው አዲስ ነገር ይኖራል ብለው ያምናሉ?

ኡስታዝ ጀማል፡- አሁን ላይ ያለው የእስራኤል እና የፍልስጤም ችግር ጎልቶ ወጥቷል። በርካታ የፖለቲካ ለውጦች አሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ የግብጽን ሚና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ፈተናዎች እየገጠሙት ነው። በመሆኑም ግብጽ ያለባትን ጫና ለማመዛዘን በምትሄድበት ወቅት ለአሜሪካ ከዚህ ቀደም የነበራትን ቦታ ይዛ ትቆያለች የሚል እምነት የለኝም።

አሜሪካ ተቋማዊ የሆነ አሠራር የምትከተል ሀገር ናት። በግለሰብ የምትመራ አይደለችም፤ በመሆኑም ወደ ሥልጣን የመጡት ትራምፕም ቢሆኑ የተናገሩትንም ሆነ የገቡትን ቃል ላያከብሩ ይችላሉ። አሁን ላይ የሁቲ እንቅስቃሴ በጣም በበዛበት፣ ቀይባሕር ላይ ያለው ውጥረት እና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ላይ ባለው እንቅስቃሴ እንደ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ማጣት አይፈልጉም። በመሆኑም እምብዛም ለውጥ አይኖረውም የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የአረብ ሊግን ለመቀላቀል ጥያቄዎችን ስታቀርብ ቆይታለች። በአረብ ሊግ በኩል ያለውን እንቅስቃሴ እንዴት ይመለከቱታል?

ኡስታዝ ጀማል፡- አረብ ሊግ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው። ለእውነት የተቋቋመ ድርጅት ቢሆን ባለው ቅርበት ሊቢያን፣ ሶሪያን፣ የመንን መርዳት ይችል ነበር። ሌላኛው በአረብ ሊግ ውስጥ ያሉ ከኢትዮጵያ ጋር በወዳጅነት የሚሠሩ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በሀገራችን የሚያከናውኑ ሀገራት ይገኙበታል። የአረብ ሊግን አሠራር ብዙውን ጊዜ ላይስማሙ የተስማሙ ሲሉ አረቦች ይገልጿቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የአረብ ሊግ ውስጥ የእንግባ ጠንከር ያለ ጥያቄን አንስተዋል። ምክንያቱም በርካታ ከአረብ ሀገራት ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት የሌላቸው እንደ ብራዚል፣ ኒውዚላንድ፣ ግሪክ ያሉ ሀገራት በቅርበት እየሠሩ ነው።

ሌሎችም ከአረብ ሀገራት ጋር በቋንቋም ጭምር ግንኙነት የሌላቸውን ሶማሊያን እና ጅቡቲን አረብ ናችሁ ብለው የሊጉ አባል አድርገዋቸዋል። እኛ ግን እንደ ሀገር በርካታ ዜጎቻችንን በዚያ ሄደው ይሠራሉ እና ይህንን በተመለከተ መጠየቅ የምንችልበት መድረክ ሊኖረን ይችላል። ነገር ግን የአረብ ሊግ ግብጽ በማንኛውም ጊዜ የምትስበው ካርድ ቢሆንም በመሀከላቸው ስምምነት የለም ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሊወስኑበት የሚችሉበት ጉዳይ አይኖርም ።

አዲስ ዘመን፡- በሥራዎ ያመጡትን ውጤት ሲመለከቱ ባለፉት ጊዜያት ቢደረግ ብለው ቁጭት ውስጥ የሚከቶት ነገር ምንድነው?

ኡስታዝ ጀማል፡- ቀድመን አለመንቃታችን ይቆጨኛል። ከልጅነታችን ጀምሮ ስለ ዓባይ በቂ እውቀት ኖሮን አድገን ቢሆን እላለሁ። በተለይ በከተማ ስለ ውሃ ሀብት፣ እርሻ ያለን እውቀት አናሳ ነበር። አሁን ላይ ያለን እንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም ከንግግር የዘለለ መንግሥትም ትኩረት አድርጎበት በኢንስቲትዩት ደረጃ መቋቋም ይገባዋል። በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የአረብኛ ቋንቋ ቴሌቪዥን ሊኖረን ያስፈልጋል። ልምድ ያላቸው ፍላጎት ያላቸው በአረብኛ ቋንቋ መጻፍና ማንበብ የሚችሉ ባለሙያዎች ስላሉ የአረቡን ዓለም በአግባቡ ማሳወቅ እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት?

ኡስታዝ ጀማል፡- ግብጻዊያንን በምንመለከትበት ጊዜ በመሀከላቸው መከፋፈል ቢኖርም፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸው አንድነት ጠንካራ ነው። በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ፤ ወደ ሀገር እንዳይገቡ የተከለከሉ፤ በሌሉበት የእድሜ ልክ የተፈረደባቸው፣ ተቃዋሚ የሆኑት ጭምር በእስር የሚገኙ ዜጎቻቸው ጭምር ሀገራዊ የጋራ አጀንዳዎቻቸውን ያውቃሉ።

ወደ እኛ ስንመጣ የጋራ የሚያደርገንን አጀንዳ ለግል ፖለቲካ ስናውላቸው ይታያል። ይህንን አካሄድ መቀየር አለብን፤ በውስጥ ግጭቶችን እና ልዩነቶችን ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ የሆኑ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይገባናል። ኢትዮጵያውያን የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እና የግል የሆኑ አቋሞቻችንን መለየት ያስፈልጋል። እንደ ሕዝብ ብሔራዊ የሆኑ አጀንዳዎቻችን ላይ ሌሎች ጉዳዮቻችንን በማቆየት አንድ ሆነን መቆም ይገባል።

የዓባይን ውሃ ከዚህ ቀደም የነበሩ መሪዎች ጠላት እንዳይዘው በማስከበር አቆይተውታል። የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ ከአጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ የታሰበ እና በደርግ ወቅት ሙከራ ተደርጎበት ነበር። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን ላይ ባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠንካራ ሥራዎች ተሠርቷል። ስለዚህ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውም ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከዚህ በኋላ ደግሞ የዓባይ ግድብ እና የባሕር በር ጥያቄን ልናተኩርባቸው የሚገቡ ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ።

ኡስታዝ ጀማል ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You