የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከትላንት በስትያ የ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫና የታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ድልድል ይፋ ማድረግ ችሏል። ካፍ በግብፅ ካይሮ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ባካሄዳው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) እና ሁለቱ የታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸውን ማወቅ ችለዋል።
የ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለአስራ አምስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን 38 የአሕጉሪቱ ሀገራት በመድረኩ ለመሳተፍ የተለያዩ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ። 12 ሀገራት የሚወዳደሩበት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ሲጠበቅ ሉሲዎቹም ዕድሉን ለመጠቀም የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። ሞሮኮ የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ስታስተናግድ ይሄ ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ሲገለጽ፣ ለአሕጉሪቱ ሴቶች እግር ኳስ እድገት የበኩሏን ሚና መጫወቷም ተመላክቷል።
ለውድድሩ ለማለፍ በሚደረገው ጉዞ ሀገራቱ በሁለት ዙሮች የማጣሪያ ጨዋታቸውን በሜዳና ከሜዳ ውጪ የሚያደርጉ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ከየካቲት 10-19/2017 ዓ.ም እንዲሁም የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ከጥቅምት 10-18/2018 ዓ.ም ይካሄዳሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹም) ለውድድሩ ለማለፍ የሁለት ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎችን በሜዳውና ከሜዳ ውጪ ያካሂዳሉ። በዚህም መሠረት ሉሲዎቹ የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን የዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳቸው ውጪ በመግጠም ይጀምራሉ። በደርሶ መልስ ጨዋታ ሁለቱን ጨዋታዎች አሸንፎ ወደ ሁለተኛ ዙር የሚያልፉ ከሆነ ደግሞ፣ ከታንዛኒያና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ለውድድሩ ለማለፍ ይጫወታሉ።
የመድረኩ አሸናፊ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ናይጄሪያና ካሜሮን ባላቸው የፊፋ ደረጃ መሠረት በመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የማይሳተፉ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የአንደኛ ዙር አሸናፊ ከሚሆኑት ሀገራት ጋር ይጫወታሉ። እነዚህ የአሕጉሪቱ ትላልቅና ጠንካራ ሀገራት ለውድድሩ ለማለፍም በሁለተኛው ዙር ከባድ ትንቅንቅን እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ውድድር እአአ በ1998 መካሄድ የጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያ በ2002 ናይጄሪያ ባስተናገደችው ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎን ማድረግ ችላለች። በወቅቱም በመድረኩም ባካሄደቻቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ተሸንፋ በአንድ አቻ ወጥታ በአንድ ነጥብ ከምድቡ ተሰናብታለች። በ2004 በደቡብ አፍሪካ በተሰናዳው ውድድርም ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በማሳተፍ በአራት ነጥቦች ከምድቧ ማለፍ ብትችልም በግማሽ ፍጻሜ በናይጄሪያ እንዲሁም ለደረጃ በተካሄደ ጨዋታ በጋና ተሸንፋ አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ለሦስት ተከታታይ የመድረኩ ውድድሮች ከተሳትፎ ርቀው የነበሩት ሉሲዎቹ በ 2012 ለሦስተኛ ጊዜ ተሳትፎን አድርገው ከምድብ ሳያልፉ ቀርተዋል። ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ መከሰት ምክንያት ሳይካሄድ የቀረውን የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ጨምሮ በ5ቱ ላይ ሳትሳተፍ ቀርታለች። ዘንድሮ በሁለት ዙሮች በምታካሄዳቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች ለአራተኛ ጊዜ ተሳታፊ ለመሆን ጠንካራ ፉክክርን ታደርጋለች ተብሎም ይጠበቃል።
በካፍ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት የተካሄደው ሌላው ውድድር የአፍሪካ ዞን ከ20 እና 17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ነው። በ2026 ፖላንድ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ የሚሳተፉ አራት ሀገራትን ለመለየት አራት ዙሮችን የሚፈጅ የማጣሪያ ውድድር ይካሄዳል። ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤት ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ሀገራት በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ውድድርን ያካሄዳሉ። በመጀመሪያ ዙር ከሚሳተፉት 12 ቡድኖች የሚያልፉ ስድስት ቡድኖችና በመጀመሪያው ዙር ያልተሳተፉት 26 ቡድኖች በድምሩ 32 ቡድኖች 16ቱን ለመቀላቀል ይጫወታሉ። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድንም በሁለተኛው ዙር ኬንያን ይገጥማል። 16 ቡድኖች በጥሎ ማለፍ አራተኛና የመጨረሻውን ዙር ለመቀላቀል በሚፋለሙበት የሦስተኛ ዙር ጨዋታ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያና አንጎላ አሸናፊ ትጫወታለች። ይሄን አሸንፋ አራተኛ ዙርና ስምንት ቡድኖች የሚያደርጉትን የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ ከተቀላቀለች ደግሞ ለውድድሩ ለማለፍ ከሚደርሳት ሀገር ጋር ትፋለማለች። የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ውድድሮች ከመስከረም 9 እስከ 18/2018 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳሉ።
የዓለም ከ 17 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ እንዲሁ ለመጀመሪያ ጊዜ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 7 እስከ 29/2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከአፍሪካ አዘጋጅ ሀገርን ጨምሮ አምስት ሀገራት ይሳተፋሉ። በውድድሩ የሚሳተፉትን ሀገራት ለመለየትም በ28 ሀገራት መካከል የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ለዚህም በሁለት ዙር የሚጠናቀቅ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች የሚያካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር ከዛምቢያ ትጫወታለች። የመጀመሪያውን ዙር አሸንፋ የምታልፍ ከሆነ ደግሞ በሁለተኛ ዙር ለጥሎ ማለፉ ውድድር ለመብቃት ከግብፅና ካሜሮን አሸናፊ ትጋጠማለች። የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ከጥር 2 እስከ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ሲካሄዱ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች እንዲሁ ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 8/2017 ዓ.ም የሚካሄዱ ይሆናል። በውድድሩ 24 የዓለም ሀገራት ዋንጫውን ለማሸነፍ ይፎካከራሉ።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም