በሁለተኛው የኮሪደር ልማት ከካዛንቺስ ለተነሱ ነዋሪዎች የተከተመ መንደር ነው። የዚህ ገላን ጉራ የተሰኘው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባ አዲስ መንደር ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤቶች ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው ከተማ አስተዳደሩን ጠይቀው እንደነበር ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።
የከተማ አስተዳደሩም ቃልን በተግባር እንዲሉ ምላሹን ሲያስገነባቸው የቆየውን የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ሰሞኑን በመመረቅ አስረክቧል። በዚህም የመንደሩ ማህበረሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ከተገነቡት መሠረተ ልማቶች መካከል ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል። ትምህርት ቤቶቹም የየራሳቸው ገቢ ያላቸው ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የገላን ጉራ ቁጥር ሁለት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምድር ወለል እና ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃ ነው። 18 መማሪያ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን፣ 720 ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የመማሪያ እና የሕጻናት የመኝታ ክፍሎችም አሉት። የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ፣ መፀዳጃ ቤት፣ አጥርና አስፈላጊ የመጫወቻ ሥፍራዎችም ተሟልተውለታል። ትምህርት ቤቱ በግምት 20 ሺህ ካሬ ቦታ ላይ ያረፈና ደረጃውን ያሟላም ነው።
ተማሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት በአርተፊሻል ሳር የተዘጋጀ ሜዳ ዝግጁ ተገንብቶለታል። ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች እንዲሁም የአካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉ የህንጻ መግቢያዎች ተሟልተውለት በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል።
በገላን ጉራ ቁጥር ሁለት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ተማሪ ኢምራን መሀመድ ካዛንቺስ አካባቢ ምስራቅ ጎህ ትምህርት ቤት ይማር ነበር፤ ቤተሰቦቹ በኮሪደር ልማቱ ከአካባቢው ሲነሱ ከአንድ ወር በፊት ወደ ገላን ጉራ አዲስ መንደር መምጣቱን ይገልጻል። ወደ አካባቢው እንደመጡም ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው በጊዜያዊነት በተዘጋጁ የመማሪያ ክፍሎች እንደነበር አስታውሶ፣ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ ወደተገነባው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤትም መዛወራቸውን ይገልፃል።
ተማሪ ኢምራን እንደሚለው፤ የካዛንቺሱ ምስራቅ ጎህ ትምህርት ቤት በዚህ መልኩ ደረጃውን የጠበቀና ሰፊ አልነበረም፤ የኳስ መጫወቻ ሜዳውም አቧራ ነበር። በገላን ጉራ ደረጃውን የጠበቀ የኳስ መጨዋቻ ሜዳ ማግኘታቸውን ገልጿል ። የቀድሞ ትምህርት ቤቱ የቅርጫት ኳስ መጫወጫ ሜዳም ምቹ እንዳልነበረ ጠቅሶ፣ በገላን ጉራ የተገነባው ግን የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ መሆኑን አስታውቋል።
መማሪያ ክፍሎቹ ፀጥ ያሉና አየሩም ነፋሻማ መሆኑን ጠቅሶ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ቤተመጻህፍትና ላቦራቶሪ በስተቀር በቅርቡ ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች መሟላታቸውን ገልጿል። ቤተመጻህፍቱና ላቦራቶሪው ደግሞ በቅርቡ እንደሚሟላ ከትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መስማታቸውን ተናግሯል።
መምህር ቢኒያም ደምሴ የገላን ጉራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ናቸው። መንደሩ ከካዛንቺስ፣ ጉላሌ እና ከመሳሰሉት አካባቢዎች በልማት የተነሱ ነዋሪዎች የሚኖሩበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በርካታ መሠረተ ልማቶች በተሟሉበት ሁኔታ ወደ አካባቢው መምጣታቸውን ገልጸዋል። ይህ በመሆኑም አካባቢውን ለመላመድ ጊዜ አልወሰደባቸውም ሲሉ ይናገራሉ።
እሳቸው እንደተናገሩት፤ የመጀመሪያው ጉዳይ መኖሪያ ወይም ማረፊያ ነው። ሁለተኛው በማረፊያ ህንፃው የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች መሟላት ነው። በመንደሩ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት አለ፤ በየሶስት ቀኑ ውሃ ያገኛል። ይህ ሁሉ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።
የልማት ተነሺዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለከተማ አስተዳደሩ ያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፣ ከእነዚህ መካከልም የትምህርት ቤት ህንጻ እንዲገነባ የሚለው አንዱ ነበር ይላሉ። ከተማ አስተዳደሩ ይህን እውን ቃል ገብቶ እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህንንም እውን በማድረግ ቃልን በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
በከተማዋ ከንቲባ አማካይነት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ድረስ ራሳቸውን የቻሉ ሶስት የተሟሉ ሶስት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት ወደ መስጠት ተሸጋግረዋል። ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ የተገነቡ ናቸው።
ትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊዎቹ አገልግሎት መስጫዎችም ተገንብተውላቸዋል። የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ መመገቢያ አዳራሽ፣ መኝታ ክፍል ፣ የቀይ መስቀል አገልግሎት መስጫ፣ በየወለሉ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች ተሟልተውለታል።
እኛም ይህን የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት ተዘዋውረን ጎብኝተናል። ምድረ ጊቢውም ንጹህ፣ የመመገቢያ እቃዎቹም ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው አግኝተናቸዋል።
ሌላው ተዘዋውረን የጎበኘነው በመንደሩ ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባውን የአንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ትምህርት ቤቱ የራሱ ጊቢና ህንፃዎች አሉት፤ ሁለገብ መጫወቻዎች ያሉት የስፖርት ሜዳም እንዳለው ተመልክተናል። ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት የሚያገኙበት ደረጃውን የጠበቀ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ለሴቶች እና ለወንዶች የተለዩ መፀዳጃ ቤቶች ተገንብተውለታል።
መምህር ቢኒያም እንዳሉት፤ ከቦሌ ኮሙኒቲ ቀጥሎ በከተማ ደረጃ ሁለተኛው የተባለ አርተፊሻል ሳር ያለው የስፖርት ሜዳ የተሟላለት ነው። ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓታቸው ውጪ ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር ጊዜያቸውን የሚያሳለፉበት ሜዳ አለው።
መምህር ቢንያም፤ ህብረተሰቡ ለከተማው አስተዳደር ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል በአካባቢው ለእናቶች የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው የቀረበው ጥያቄ ይጠቀሳል። አስተዳደሩም ለእዚህ ጥያቄም በመንደሩ እናቶች ተደራጅተው እንጀራ እና ዳቦ በመጋገር ሥራ እንዲሠማሩ ማድረግ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ተገንብተዋል። የኮንቴይነር ሱቆችም ተገንብተዋል፤ አንዳንዶቹ አገልግሎት መጀመራቸውን እኛም ተመልክተናል።
እነዚህ መሠረተ ልማቶች ሲሠሩ ከከተማዋ ከንቲባ ጀምሮ መርህ ተደርጎ በተጨባጭ የታየው ትልቁ ጉዳይ “ቃልን በተግባር” የሚለው ነው ያለው መምህር ቢኒያም፣ ትናንት ቃል ነበር፤ ዛሬ ደግሞ በተግባር ህንፃዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ሲል ገልጻል። ይህም እውን እንዲሆን ፕሮጀክቱን በመምራት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉት ለከንቲባ አዳነች አቶ ቢኒያም በግላቸው ያላቸውን ምስጋናም አቅርበዋል።
ተማሪዎች ቀደም ብሎ በጊዜያዊነት በተዘጋጁ መማሪያ ክፍሎች ሲማሩ እንደነበር አስታውሰው፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ በሳምንት አንድ ጊዜ መምህራኑንና ተማሪዎቹን ‹‹ነገ ሌላ ቀን ነው›› እያሉ ሲያበረታቱ እንደነበርም አስታውሰዋል። ሌሎች የከተማዋና የክፍለ ከተማ አስተዳደሮችም እንዲሁ ለዚህ እውን መሆን የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
መንደሩ አዲስ ከመሆኑ አኳያ ሌሎች መሟላት የሚገባቸው መሠረተ ልማቶች አንዳሉም መምህር ቢንያም ጠቁመዋል። በመንደሩ የከነማ መድሃኒት ቤት እንዳለ ጠቅሰው፣ አገልግሎቱ አሁንም መስፋት አለበት ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአካባቢው ከስድስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። ለነዋሪዎቹ ጤና ጣቢያዎች ያስፈልጋሉ፤ የባንክ አገልግሎትም ሊኖር ይገባል። ለእዚህም የመንግሥት እና የግል ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን እንዲከፍቱም ጥሪ አቅርበዋል። በተለይ ንግድ ባንክን የመሳሰሉ መንግሥታዊ ባንኮች በአስቸኳይ መቋቋም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው የወጣት ማዕከላት እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል። ወጣቶች በቀድሞው መንደራቸው ይሠሯቸው የነበሩ ሥራዎች በአዲሱ መንደር እንደማይኖሩ ጠቅሰው፣ ሥራ አጦቹን በመለየትና በማደራጀት የተለያዩ የሥራ እድሎች እንደሚቻቹላቸውም ጠይቀዋል። የአካባቢው በርካታ ፋብሪካዎች ለወጣቶቹ የሥራ እድል እንዲፈጥሩላቸውም ጠይቀዋል።
የገላን ጉራ ቁጥር ሁለት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አስቻለው ኃይሉ እንዳስታወቁት፤ ከሁለት ወራት በፊት የልማት ተነሺዎቹ ወደ አካባቢው ሲመጡ ቦታው ተስተካከሎ በጊዜያዊነት በቆርቆሮ በተሰሩ ቤቶች ያለውን ግብአት በማብቃቃት ነበር ትምህርት መሰጠት የተጀመረው። የከተማ አስተዳደሩ በወሰደው ፈጣን ምላሽ በ60 ቀናት ትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቆ በዚህ ሳምንት በአዲሱ ህንጻ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል።
የአንደኛ ደረጃ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ ከጊዜያዊ ትምህርት መስጫዎቹ ወደ አዲስ የተገነቡት ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ተዛውረዋል። የትምህርት ቤቶቹ መገንባት ልጆቹን ቂሊንጦ ድረስ እየላከ ሲያስተምር ለቆየው ለገላን ጉራ ቁጥር ሁለት አካባቢ ማህበረሰብም ልጆቹ በአቅራቢያው እንዲማሩ በማስቻል እፎይታን ሰጥቷል።
የትምህርት ተቋማቱን ግንባታ የከተማ አስተዳደሩ እና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም የ90 ቀን እቅድ ተይዞለት የነበረውን ይህን ግንባታ በ60 ቀናት በጥሩ ሁኔታ ማጠናቀቅ ተችሏል። አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ 30 የመማሪያ ክፍሎች ያሉትና ተጨማሪ የግራውድ ፕላስ አራት ህንፃ እና የአስተዳደር ቢሮ ህንጻ ግንባታም በቅርቡ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
በእነዚህም ላቦራቶሪዎችን ጨምሮ ለትምህርት ቤት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች እንደሚሟሉም ተጠቁሟል። እስከዚያው የላቦራቶሪ አገልግሎት በሚገኝባቸው የአቅራቢያው ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በትራንስፖርት በማመላለስ አገልግሎቱን ለአንድ ወር እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዘጠኝ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ያሉት ተማሪዎች በአንድ ክፍል 16 እና 17 ሆነው እንደማሩ እየተደረገ ነው። የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች 15 ብቻ ናቸው። ለትምህርቱ ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችንም በአቅራቢያው ከሚገኙት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ትምህርት ቤቶች በማሰባሰብ እየተሠራ ነው።
በአካባቢው በመንግሥት ትምህርት ቤት ደረጃ ያማረ ሶስት ትምህርት ቤቶችን በነፋሻማ ሥፍራ በመገንባታቸው ተነሽዎቹና የአካባቢው ማህበረሰብ መታደሉን ጠቅሰው፣ የስፖርት ማዘውተሪያው፣ መፀዳጃ ቤቶቹ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የመመገቢያ ክፍሎቹ፣ የእግረኛ መንገዱ፣ የስፖርት ማዘውተሪያው የተገነቡበት መንገድ ለተማሪዎች፣ ለማህበረሰቡ፣ ለተመልካችም ማራኪ ነው።
በእያንዳንዱ ክፍል መግቢያ የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መግቢያዎች ስማርት ተደርገው ተሠርተዋል። ሙሉ የጊቢው ግንባታ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው። በዚህ አዲስ የትምህርት ቤት መሠረት እውን መሆን መደሰታቸውን ጠቅሰው፣ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንደያመጡ በሥራ ለማሳየት ርእሰ መምህሩ ቃል ገብተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርቡ በገላን ጉራ መንደር ለልማት ተነሺዎች የተገነባ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክትን ሰሞኑን በመረቁበት ወቅት እንደገለጹት ፤ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ እናደርጋለን ማለት መሠረተ ልማት ማሟላት፣ የከተማዋን ገጽታ መቀየር ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥንም ያካተተ ነው። በኮሪደር ልማቱ መልሶ ማልማት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስምንት ሺህ ያህል ቤቶች ተገንብተዋል።
በገላን ጉራ መንደር ብቻ አንድ ሺህ 200 ያህል የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ምንም ቤት ያልነበራቸውና በቀበሌ ቤቶች ላይ ተለጣፊ ቤቶችን ሠርተው ለመኖር ለተገደዱ መጠለያ በሚል የተገነቡ ቤቶችን በመጨመር አጠቃላይ አንድ ሺህ 500 የሚሆኑ ቤተሰቦችን በመንደሩ ለማስተናገድ ተችሏል።
ለልማት ተነሺዎቹ መልሶ ግንባታ ስምንት ሺህ ቤቶቹን ከነመሠረተ ልማቱ ለማሟላት አጠቃላይ 10 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። በግል ተነሺዎች ማዕቀፍ ውስጥ ለተያዙት ደግሞ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል።
ከ100 ሄክታር መሬት በላይ ለምትክ በማዘጋጀት ማስረከብ ተችሏል ሲሉም ከንቲባዋ ጠቅሰው፣ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቱን የያዙ ኮንትራክተሮች ግንባታውን በ57 ቀናት ማጠናቀቃቸውንም አስታውቀዋል። በጥራትም በዋጋም አስደናቂ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት።
በመንግሥት ያልተሸፈኑ ከፍተቶችን የሞሉ ባለሀብቶች ሀብታቸው ከነዋሪዎች የተለየ መሆኑ ትርጉም እንደሌለው በመገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በመጥቀስ ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ለተቀናጀ ልማቱ ሲባል የእርሻ ቦታቸውን ለለቀቁ አርሶ አደሮችም በተለያየ መልኩ ድጋፍ ላደረጉ ባለሀብቶች፣ ፕሮጀክቶችን ለተከታተሉ አመራሮችም እንዲሁ ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የልማት ተነሺዎች በርከት ብለው በገቡባቸው ሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም